​ሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የሚጀመርበት ቀን ተራዝሟል

በህዳር 16 በኬንያ አዘጋጅነት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ባልታወቀ ምክንያት መራዘሙን የዩጋንዳ እግርኳስ ፌድሬሽኖች ማህበር (ፉፋ) በይፋዊ ድረ-ገፁ የሴካፋውን ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙሶንዬን ዋቢ አድርጎ አስታውቋል፡፡ ውድድሩ አሁን ላይ ህዳር 24 እንዲጀመር ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ 

10 ሃገራት ተሳታፊ የሚሆኑበት ውድድር ከ2015 ኢትዮጵያ ካስተናገደች በኃላ ተደርጎ አያውቅም፡፡ ከውድድሩ ጅማሮ አስቀድሞ በህዳር 23 የሴካፋ ጠቅላላ ጉባኤ ባዘጋጇ ኬንያ የሚካሄድ ሲሆን ዩጋንዳ የአሁኑን የሴካፋ መሪ ሱዳናዊው ሙታሲም በክፍለ አህጉሩ አመርቂ ስራዎችን መስራት ባለመቻላቸው ስልጣን እንዲለቁ ጠይቃለች፡፡ ሙታሲም ከሱዳን እግርኳስ አመረራነታቸው በምርጫ ተሸንፈው ከወጡ በኃላ በሴካፋም ያላቸው ቀጣይ ቆይታ አጠራጣሪ ነው፡፡ የሴቶች እና ከ17 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫዎች በሩዋንዳ እና ቡሩንዲ ይስተናገዳሉ ቢባልም የመደረጋቸው ነገር አሁንም ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቷል፡፡

ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ዛንዚባር፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ቡሩንዲ እና ተጋባዦቹ ሊቢያ እና ዚምባቡዌ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና በቅርቡ ውጤት አልባ ብሄራዊ ቡድኗን ያፈረሰችው ጅቡቲ በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ አይሆኑም፡፡

ክፍለ አህጉሩ በእግርኳሱ ደካማ ሃገራት የሚገኙበት ሲሆን በውድድሩ ምክንያት ሃገራት የውስጥ ሊግ ውድድሮቻቸውን ሲያቋርጡ ይታያል፡፡ አሁን አሁን እንደዩጋንዳ ያሉ ሃገራት እምብዛም ለብሔራዊ ቡድን ተጫውተው የማያውቁ ተጫዋቾቻቸውን በውድድሩ ላይ በማሰለፍ ልምድ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *