ዓመታዊ የዳኞች እና ኮሚሽነሮች አበል እና ትራንስፖርት ክፍያን በወቅቱ የማይፈፅሙ የከፍተኛ ሊጉ ክለቦችን ከውድድር እንደሚሠርዝ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የከፍተኛ ሊጉ ክለቦች በውድድሩ ለመሳተፍ በየዓመቱ በፌዴሬሽኑ የተወሰነ ገንዘብ የሚከፍሉ ሲሆን ፌዴሬሽኑም ገንዘቡን ክለቦቹ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ የሚመደቡ ዳኞች እና ኮሚሽነሮችን ወጪ ለመሸፈን ይጠቀምበታል። ነገርግን ለዓመታት አንዳንድ ክለቦች በተገቢው ወቅት ክፍያውን መፈፀም ሲያቅታቸው የታየ ሲሆን ይህም ውድድሩ በታቀደለት ጊዜ እንዳይጀመር አንድ መሰናክል ሆኗል።
ፌዴሬሽኑ ዛሬ ክፍያውን ላልፈፀሙ የከፍተኛ ሊጉ ክለቦች በፃፈው ደብዳቤ እስከ ጥቅምት 03 ድረስ ክፍያቸውን እንዲያጠናቅቁ በማሳሰብ 3 ደብዳቤዎችን መፃፉን አስታውሷል። የፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አያይዞም ገንዘቡን ገቢ ያላደረጉ ክለቦች ቅዳሜ ህዳር 9 በሚጀምረው ውድድር የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚያልፋቸው ገልፆ ክፍያውን ለማጠናቀቅም እስከ ህዳር 9 ድረስ የመጨረሻ ቀነ ገደብ አስቀምጧል። ገንዘቡን እስከ ቀነ ገደቡ ድረስ የማያስገቡ ክለቦች ከውድድሩ ተሰርዘው በሌሎች ክለቦች እንደሚተኩም የፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ይገልፃል።
ከፌዴሬሽኑ ባገኘነው መረጃ ከምድብ ሀ 4 ክለቦች፣ ከምድብ ለ ደግሞ 11 ክለቦች ክፍያቸውን አልፈፀሙም። በውሳኔውም መሠረት የከፍተኛ ሊጉ የ2010 ዓ.ም. የውድድር ዘመን የፊታችን ቅዳሜ ሲጀምር በምድብ ሀ ክፍያቸውን ባጠናቀቁ ክለቦች መሀከል 4 ጨዋታዎች ብቻ የሚደረጉ ሲሆን በምድብ ለ ምንም ጨዋታዎች አይደረጉም።
ምድብ ሀ
ቅዳሜ ህዳር 09 2010 ዓ.ም.
ባህርዳር ከተማ ከ አክሱም ከተማ – 9፡00 – ባህርዳር
ሽረ እንዳስላሴ ከ ኢትዮጵያ መድን – 9፡00 – ሽረ
እሁድ ህዳር 10 2010 ዓ.ም.
አማራ ውሃ ስራ ከ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን – 10፡00 – ባህርዳር
የካ ክ/ከተማ ከ ሰበታ ከተማ – 9፡00 – አዲስ አበባ