ኤሌክትሪክ ፍፁም ገ/ማርያምን የራምኬል ምትክ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል

ከትልልቅ ክለቦች ጋር ስሙ እየተያያዘ የሚገኘው ራምኬል ሎክ ኤሌክትሪክን የመልቀቁ ነገር እርግጥ ይመስላል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ አጥቂ በክለቡ የቀረበለትን የውል ማደስ ጥያቄ እንዳልተቀበለ የተነገረ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና አንዳቸውን ሊቀላቀል ይችላል ተብሏል፡፡ ቢንያም አሰፋን ያጣው ኢትዮጵያ ቡና ራምኬልን ዛሬ ለማስፈረም ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ራምኬል ሊገኝ ባለመቻሉ ለቡና ሳይፈርም ቀርቷል፡፡ አጥቂው ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ ሂሳብ የቀረበለት በመሆኑ ለቡና የመፈረም ሀሳቡን ሳይተው እንዳልቀረ ሲታወቅ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በገንዘብ ጉዳይ ከተስማማ ፈረሰኞቹን በቀጣይ ቀናት ሊቀላቀል ይችላል ተብሏል፡፡

በተያያዘ ዜና ኤሌክትሪክ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፍፁም ገብረማርያምን የራምኬል ሎክ ቀጥተኛ ተተኪ ሊያደርግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከክለቡ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የፍፁም እና ክለቡ ድርድር ፍሬ ካፈራ የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ አጥቂ ለእረፍት ከሄደበት ሲመለስ ለኤሌክትሪክ ፊርማውን ሊያኖር ይችላል ተብሏል፡፡ ኤሌክትሪክ ከፍፁም በተጨማሪ በቡና ከወራት በፊት የታገደውና ከክለቡ እንደሚሰናበት የሚጠበቀው ግብ ጠባቂው ሙሴ ገብረኪዳንን ለማስፈረም እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ሙሴ ከፈረመ ከአሰግድ አክሊሉ እና ውሉን ካደሰው ገመቹ በቀለ ጋር ለቁጥር አንድ ቦታው ይፎካከራል፡፡

ያጋሩ