​ዛሬ በታሪክ ውስጥ |  አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ ሲታወሱ…

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ስማቸው በግምባር ቀደምትነት ከሚጠሩ አሰልጣኞች አንዱ የነበሩት ሐጎስ ደስታ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ልክ የዛሬ 17 አመት በዛሬው እለት ነበር። “ማስተር ቴክኒሻን” እየተባሉ በብዙዎች የሚሞካሹት አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ ከዚህ አለም በሞት የተለዩበትን 17ኛ አመት ምክንያት በማድረግ ስለ ታላቁ አሰልጣኝ አጭር ማስታወሻ አቅርበናል።

በ1938 በቀድሞው የኤርትራ ክፍለ ሀገር የተወዱት ሐጎስ ደስታ በተጫዋችነት ዘመናቸው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የነበሩ ሲሆን ለድሬዳዋ አየር ኃይል ፣ ኢትዮ ሴሜንት እና ድሬዳዋ ምርጥ ተጫውተዋል።

ሐጎስ በተጫዋችነት (ከተቀመጡት ከቀኝ ወደ ግራ 2ኛ) : ፎቶ ምንጭ – ካሳሁን ሀሰን

ሐጎስ ወደ አሰልጣኝት የገቡት በድሬዳዋ አየር ኃይል አሰልጣኝነት ነበር። ብዙም ሳይቆዩ በ1970ዎቹ አጋማሽ አየር ኃይልን በመረከብ ክለቡን ወደ ጠንካራ ተፎካካሪነት ቀይረውታል። የቢሾፍቱው ክለብንም በ1978 የጦር ኃይሎች ውድድር ሻምፒዮን ማድረግ ችለዋል። ከአየር ኃይል መልካም ጊዜያት በኋላ ለአሰልጣኝነት ትምህርት ወደ ጀርመን ያመሩት አሰልጣኝ ሐጎስ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ የአግሮ ኢንደስትሪ ቡድንን ማሰልጠን የቻሉ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳሰ ፌዴሬሽንም በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

አሰልጣኝ ሐገስ በ1986 ውጤታማው ኢትዮጵያ መድንን ከአሰልጣኝ ስዩም ተረክበው ክለቡ በካፍ ካፕ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ባደረገው ጉዞ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን ቡድኑ በውድድሩ ላይ ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች አራቱን በአሰልጣኝነት መምራት ችለው ነበር። ከመድን አሰልጣኝነታቸው በኋላ ደግሞ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድንን ለሁለት አመታት አሰልጥነዋል።

በ1989 ኢትዮ ኤሌክትሪክን (መብራት ኃይል) የተረከቡት አሰልጣኝ ሐጎስ በአዲስ ፎርማት ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በ1990 አሸናፊ በመሆን ኮኮብ አሰልጣኝ ተብለው ተመርጠዋል። በ1993 በወጣቶች የተዋቀረውና በሀገሪቱ የተዘጋጁ ዋንጫዎችን ጠራርጎ የወሰደው ዝነኛው ኤሌክትሪክን የገነቡት አሰልጣኝ ሐጎስ የስራቸውን ፍሬ ሳያዩ ልክ በዛሬዋ እለት ህዳር 7 ቀን 1993 ባደረባቸው ህመም በተወለዱ በ55 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። በአመቱ መጨረሻ ክለቡ የፕሪምየር ሊጉ እና ጥሎ ማለፉ እንዲሁም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከማንሳቱ በተጨማሪ ለአለም ወጣቶች ዋንጫ አልፎ በነበረው የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ቡድን በርካታ ቁልፍ ተጫዋቾች ከኤሌክትሪክ የተገኙ ሲሆን ለዚህ መሰረት የጣሉት አሰልጣኝ ሐጎስ እንደሆኑ ብዙዎች ይስማሙባቸዋል።

አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ 4 ሴት እና 1 ወንድ ልጆች ያፈሩ ሲሆን ብቸኛ ወንድ ልጃቸው የሆነው ደብሮም ሐጎሰ የአባቱን ፈለግ እየተከተለ ይገኛል። በ1990ዎቹ ለጉና ንግድ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ደብሮም በቅርብ ጊዜያት ወደ አሰልጣኝነት በመግባት በአሁኑ ወቅት የደደቢት ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል።

ደብሮም ስለ አባቱ ሲናገር ተግባቢነቱ እና የማሳመን ችሎታው የአሰልጣኝ ሐጎስ መለያዎች ናቸው ይላል። ” በአባቴ ስር የመሰልጠለን እድሉን ባላገኝም አሰልጣኝ ሐጎስ ከተጫዋቾቹ ጋር ቶሎ መግባባት እና እንደ ጓደኛ ማየት ይችላል። የተግባቢነቱን ያህልም ኃይለኛ ነበር። ነገሮችን ፊት ለፊት በመናገር የሚያምን ነበር። ከአየር ኃይል ጀምሮ ቡድኑን በወጣቶች በማዋቀር ነው የሚታወቀው። የክለቦችን ኃላፊዎች በማሳመን ቡድኑን በወጣቶች በመገንባት በርካታ ተጫዋቾችን ለትልቅ ደረጃ አብቅቷል። ”
___________________________

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የሚታወስ ስራ ሰርተው ያለፉ (በህይወት ያሉ እና የሌሉ) ግለሰቦችን የልደት ፣ ህልፈት እና አብይ ስራ ሰርተው ያለፉበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ሶከር ኢትዮጵያ በቀጣይነት የማስታወሻ ፅሁፎችን የምታቀርብ ይሆናል። እርስዎም መታወስ ያለባቸው ግለሰቦችን በስልክ ቁጥር 0922947765 አልያም በabgmariam21@gmail.com ቢጠቁሙን የምናስተናግድ መሆናችንን እንገልፃለን።


የመረጃ ምንጮች: ፈለገ ብርሀን መፅሄት ፣ ደብሮም ሐጎስ ፣ መድን ኢንተርናሽናል ልዩ እትም ፣ ሶከር ኢትዮጵያ 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *