​ፕሪምየር ሊግ 20ኛ አመት | የሊግ ውድድር በኢትዮጵያ [ክፍል 1]

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህ ወር የተጀመረበትን 20ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተንተራሱ ፅሁፎችን የምናቀርብላችሁ ይሆናል፡፡ ይህ ክፍልም የፕሪምየር ሊጉን ውልደት እና ቀደምት የኢትዮጵያ የሊግ ውድድሮችን መልክ ያስቃኛል፡፡

ፕሪምየር ሊጉ እውን አዲስ ፎርማት ነው …?

ስለ ፕሪምየር ሊጉ በተነሳ ቁጥር ‹‹ሊጉ ተዟዙሮ መጫወት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ›› የሚል ሀረግ በተደጋጋሚ እናስተውላለን፡፡ ሆኖም ተዟዙሮ የመጫወት ፅንሰ ሀሳብ ከ1990 በፊትም በተለያዩ ዘመናት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ታይቷል፡፡ የሊግ ውድድር በመመስረት በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም አሁን የነበረውን አይነት የሊግ አካሄድ የተከተለችባቸው ጊዜያት እንደነሩ ሶከር ኢትዮጵያ ይህን ፅሁፍ ለማዘጋጀት በሊጉ ላይ ባደረገችው መጠነኛ ጥናት ለመገንዘብ ችላለች፡፡ 

በ1936 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በሚል ስያሜ በ5 ቡድኖች የተጀመረው ውድድር መሰረታዊ የሊግ ባህርያትን ያሟላ ውድድር ነበር፡፡ ክለቦችም ጨዋታዎች አከናውነው በሚሰበሰበው ነጥብ አሸናፊው የሚለይበት ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ የነበሩት ክለቦች መሰረታቸው አዲስ አበባ በመሆኑ በመላ ሀገሪቱ ላይ ተዟዙረው አይጫወቱም ነበር፡፡ ውድድሩ ቀጥሎ ባሉት አመታት ባልታወቀ ምክንያት ሳይካሄድ ቆይቶ በ1940 በድጋሚ ሲጀመር የክለቦቹ መጠን ወደ 8 አድጎ እርከኑ ወደ ሁለት ከፍ ቢልም አሁንም የአዲስ አበባ ክለቦች ብቻ እየተሳተፉበት ዘልቋል፡፡ 

ውድድሩ በዚህ መልኩ ቀጥሎ በ1945 አዲስ ደንብ ወጣ፡፡ የሀረርጌ እና ኤርትራ ግዛቶች መምሪያ በፌዴሬሽኑ እውቅና በማግኘታቸው ኤርትራ እና ሀረርጌ ግዛቶች ወደ ውድድሩ መጡ፡፡ በ1929 የተመሰረተው ሀማሴን እና በ1930ዎቹ መጀመርያ የተቋቋመው ቀይ ባህርን የመሳሰሉ ጠንካራ ክለቦች የነበሩት የኤርትራ ክፍለ ሀገር እና ቀድሞውንም በውድድር የደረጀው አዲስ አበባ (ክልል 14) የውስጥ ውድድር በማድረግ ሀማሴን እና ጦር ሰራዊት (አሁን መከላከያ) ሲያሸንፉ ሀረርጌ የውድድር ባለማድረጉ አንድ ቡድን ወክሎ በሶስቱ ክለቦች መካከል አዲስ አበባ ላይ የመለያ ውድድር (playoff) ተደረገ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በተገኙበት የፍጻሜ ጨዋታም ጦር ሰራዊት 4-3 በማሸነፍ በአዲሱ ፎርማት የመጀመርያ ዋንጫ አነሳ፡፡ 

ይህ አሰራር ለ11 አመታት ሳይቋረጥ መዝለቅ ችሎ ነበር፡፡ በ1955 የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በውድድሩ ላይ የደንብ ማሻሻያ በማድረግ አዲስ አሰራር ይፋ አደረገ፡፡ በቀድሞው ስርአት ሶስቱ ታላላቅ ግዛቶች የነበሩት ሸዋ ፣ ሀረርጌ እና ኤርትራን ያማከለ የደርሶ መልስ የዙር ውድድር መካሄድ ጀመረ፡፡ ከሶስቱ ክፍለሀገራት የተውጣጡ 8 ቡድኖች በአንደኛ ዲቪዝዮን ሲወዳደሩ ሌሎች 8 ቡድኖች ደግሞ በሁለተኛ ዲቪዝዮን መወዳደር ጀመሩ፡፡ ወደ ሶስቱ ክፍለ ሀገራት የሀገር ውስጥ በረራ የነበረ በመሆኑም ክለቦቹ በአውሮፕላን በመጓጓዝ የሜዳ ውጪ ጨዋታቸውን ያከናውኑ እንደነበር ይነገራል፡፡ በ1960ዎቹ በሀገሪቱ የክለቦች ቁጥር በብዙ እጥፍ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ በሶስቱ ክፍለ ሀገራት ብቻ ተገድቦ የነበረው ውድድር ሌሎቹንም እያሳተፈ መጣ፡፡ እስከ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት መውደቅ ድረስም የክለቦች መጠን በተለያዩ ግዛቶች እየጨመረ ቢመጣም በኢትዮጵያ ሻምፒዮናው የበላይ ሆነው የቆዩት ሶስቱ አብይ ጠቅላይ ግዛቶች እንደነበሩ ታሪክ ያስረዳል፡፡ 

የደርግ መንግስት ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ ባሉት አመታት የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ፎርማት ባለበት መልኩ ቢቀጥልም የደርሶ መልሱ ጨዋታ ቀርቶ የየግዛቶቹ አሸናፊዎች እና 2ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች አዲስ አበባ ላይ የማጠቃለያ ውድድር ማድረግ ጀመሩ፡፡ ደርግ በአዲስ የስፖርት ፖሊሲ 1975 ላይ ክለቦችን በፋብሪካዎች እና የመንግስት ተቋማት ስር እንዲቋቋሙ በማድረግ አደረጃጀታቸውን መቀየሩ ከሶስት ግዛት ክለቦች የበላይነት ይልቅ የአዲስ አበባ ክለቦችን የበላይነት ያወጀ ሆነ፡፡ በሀገሪቱ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት መስሪያ ቤቶች እና ፋብሪካዎች በአዲስ አበባ ይገኙ የነበረ መሆኑ ምናልባትም ለክለቦቹ የበላይነት እንደአንድ ምክንያት መጠቀስ ይችላል፡፡ 

ከደርግ ዘመን ውድቀት በኋላ ባሉት አመታት ውድድሩ መልኩን ሳይቀይር ቆይቶ ከ1985 በአዲሱ የክልሎች መዋቅር መሰረት ከየክልሉ በሚወከሉ ክለቦች መካከል ውድድሮች ቀጥለዋል፡፡ አዲስ አበባ ፣ ድሬዳዋ ፣ ሀረሪ ፣ ትግራይ ፣ አማራ ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በውስጥ ውድድር አሸንፈው የሚመጡ ክለቦች እንደክልሎቹ የእግርኳስ ደረጃ በሚሰጣቸው ኮታ ተውጣጥተው (በ1986 ከተደረገውና እንደቀድሞው በደርሶ መልስ ከተደረገው ‹‹ሱፐር ሊግ›› ውድድር ውጪ) አዲስ አበባ ላይ በሚደረግ የማጠቃለያ ውድድር አሸናፊው የሚለይበት አሰራር ተተክቷል፡፡ ውድድሩ ላይ ከኤርትራ አለመኖር እና ከአዲሱ የክልል መዋቅር በቀር የተለወጠ አካሄድም አልነበረም፡፡      

ይህ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ለሩብ ክፍለ ዘመን ሲሰራበት ቆይቶ በ1990 ወደ ደርሶ መልስ ፎርማት ተሸጋገረ፡፡  

1990 – የመጨረሻ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ፍፃሜ እና የፕሪምየር ሊግ ውልደት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጀመረበት ሁኔታ አወዛጋቢ ነው፡፡ እንግሊዝን እንደመሳሰሉ ሀገራት ሊጉ የተመሰረተው በክለቦች አነሳሽነት እና መስራችነት ሳይሆን በፌዴሬሽኑ ትዕዛዝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውድድሩ አዋጪነት ተጠንቶና ለረጅም ጊዜ ታስቦበት ሳይሆን በድንገት የተጀመረ ነው፡፡ 

ፌዴሬሽኑ በወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ሀገር አቀፍ መልክ እንዲኖረውና የክልሎች ተሳትፎ እንዲጠናከር በማሰብ እንደተጀመረ ቢያሳውቅም ፕሪምየር ሊጉ የአአ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፉክክር የወለደው እንደሆነ ይነገራል፡፡ 

በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከዋናው (ማጠቃለያ) ውድድር በላይ ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት የአዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዝዮን በማጠቃለያው ውድድር 4 ክለቦችን የሚያሳትፍ ጠንካራ ውድድር ነበር፡፡ በወቅቱ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌደሬሽን እና በኢንጂነር ግዛው ተክለማርያም የሚመራው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መካከል የነበሩት ውዝግቦች ፌዴሬሽኑ በፉክክር ፣ በገቢ እና በህዝብ ትኩረት የተሻለ የነበረው የአዲስ አበባ እግርኳስን ለማዳከም ሆን ብሎ የወጠነው እቅድ እንደሆነ የሚገልፁ ወገኖች አሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ በተጨማሪም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የገባው ውዝግብ ሊጉን እንዲጀምር ምክንያት እንደሆነው የሚገልፁም አሉ፡፡ ለዚህ እንደማስረጃ የሚቀርበውም ስለ ሊጉ ምስረታ ለክለቦች የተነገረው የውስጥ ውድድሮች ከተጋመሱ በኋላ መሆኑ ፣ በ1989 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በሚመዘገብ ውጤት መሰረት ቡድኖች ወደ ሊጉ እንዲገቡ ከማድረግ ይልቅ ለኮታ ቅድሚያ መሰጠቱ የአዲስ አበባ እግርኳስን ለማዳከም ነው የሚል የሴራ ንድፈ ሀሳብ ይደመጣል፡፡  (ተጨማሪ መረጃዎች – ከኢንተር ስፖርት – ቁጥር 446 ሚያዝያ 5 ቀን 2000 እትም)       

20 ክለቦች በተሳተፉበት የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የማጠቃለያ ውድድር ላይ አዲስ አበባ 4 ኮታ የነበረው ቢሆንም ፌዴሬሽኑ በ1990 ለመጀመር ላሰበው ፕሪምየር ሊግ ባወጣው ደንብ መሰረት 8 ክለበች እንዲሳተፉ ሲደረግ አዲስ አበባ የሶስት ክለቦች ኮታ ተሰጠው፡፡ በዚህም ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያልፉ 4ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ባንኮች እንዲሁም 5ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዝዮን ቀሩ፡፡ ከሌሎች 5 ክልሎች/ከተማ አስተዳደሮች ደግሞ አንድ አንድ ኮታ ተሰጥቷቸው ሀዋሳ ከተማ (ደቡብ) ፣ ጉና ንግድ (ትግራይ) ፣ ኮምቦልቻ ጨጨ (አማራ) ፣ ድሬዳዋ ጨጨ (ድሬዳዋ) እና ፐልፕ እና ወረቀት (ኦሮሚያ) የየክልላቸውን የውስጥ ውድድር በአንደኝነት በመፈፀማቸው ወደ ሊጉ እንደሚያድጉ አረጋገጡ፡፡

የመጨረሻው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና መካሄድ የነበረበት በ1989 ቢሆንም ወደ መስከረም 1990 ተገፍቶ ተካሄደ፡፡ 20 ክለቦች የተሳተፉበት ውድድር በ5 ምድቦች ተከፍሎ ነበር የተካሄደው፡፡ 

ምድብ ሀ

መብራት ኃይል (ኤሌክትሪክ) ፣ ደብረብርሀን ብርድልብስ ፣ ኢትዮጵያ ባንኮች  ፣ ናዝሬት ከነማ (አዳማ ከተማ) ፣ ሀዋሳ ጨጨ

ምድብ ለ 

ኢትዮጵያ ቡና ፣ ምድር ባቡር ፣ ኮምቦልቻ ጨጨ ፣  ሙገር ሲሚንቶ ፣ ጉና ንግድ

ምድብ ሐ

ኢትዮጵያ መድን ፣ ድሬዳዋ ጨጨ ፣ መቐለ ከተማ ፣ ፐልፕ እና ወረቀት ፣ ሀዋሳ ከተማ 

በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ በተደረገው በዚህ የማጠቃለያ ውድድር በመጨረሻው አወዛጋቢ ጨዋታ በስዩም አባተ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮ ኤሌክትሪክን አሸንፎ ዋንጫውን ለመጀመርያ ጊዜ አነሳ፡፡ 

ከሻምፒዮናው መጠናቀቅ አንድ ወር በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ በሚል ስያሜ አዲሱ ውድድር ተጀመረ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት 8 ክለቦች የተሳተፉበት ውድድር ህዳር 7 ቀን 1990 በተደረጉ ጨዋታዎች ነበር የተጀመረው፡፡ በመጀመርያው ሳምንት የተመዘገቡ ውጤቶችም እነዚህን ይመስሉ ነበር፡፡


ህዳር 7 ቀን 1990

ጉና ንግድ 1-2 ኢትዮጵያ መድን (መቐለ)

ሀዋሳ ከተማ 3-2 ኢትዮ ኤሌክትሪክ (ሀዋሳ)

ኮምቦልቻ ጨጨ 2-2 ድሬዳዋ ከተማ (ደሴ)

ኢትዮጵያ ቡና 6-1 ፐልፕ እና ወረቀት (አዲስ አበባ)
56 ጨዋታ ብቻ በተደረገበት በመጀመርያው አመት በሶስቱ የአዲስ አበባ ክለቦች መካከል ከፍተኛ ትንቅንቅ ተደርጎ በመጨረሻም ኢትዮ ኤሌክትሪክ (በያኔው አጠራር መብራት ኃይል) በ32 ነጥቦች እና 21 ንፁህ ግብ ቻምፒዮን ሆኖ አጠናቀቀ፡፡ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብ በ2 የግብ ልዩነቶች ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ኢትዮጵያ ቡና በ29 ነጥቦች 3ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሎ ነበር፡፡

አጠቃላይ እውነታዎች

የተደረጉ ጨዋታዎች ብዛት – 56

የተቆጠሩ ጎሎች – 188 (በአማካይ 3.4 ጎል በጨዋታ)

አሸናፊ – ኤሌክትሪክ

ኮከብ አሰልጣኝ – ሐጎስ ደስታ

ኮከብ ተጫዋች – አንዋር ያሲን (ኤሌክትሪክ)

ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ – ሀሰን በሽር (ኢትዮጵያ መድን – 8 ጎሎች)

ወራጅ – ፐልፕ እና ወረቀት

አዳጊዎች – ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሙገር ሲሚንቶ እና ድሬዳዋ ምድር ባቡር

[ ይቀጥላል… ]

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን 20ኛ አመት በማስመልከት የምናቀርባቸው ፅሁፎች በቀጣይ ክፍሎችም በሊጉ ታሪክ እና ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይቀጥላል፡፡ በፅሁፎቹ ላይ ያላችሁን አስተያየት እና ዕርምትም ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡


–  ተጨማሪ የመረጃ ምንጮች: አዲስ ዘመን ፣ ሊብሮ ፣ አቴና ፣ ኢንተር ስፖርት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *