በሁለተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ጅማሮውን ሲያደርግ መከላከያ መመራት ተነስቶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡
ንግድ ባንኮች ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አዳማ አቅንተው በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ አዳማን 3-2 በማሸነፍ የውድድር ዘመናቸውን በድል ሲጀምሩ በተመሳሳይ ወደ ይርጋለም ያቀኑት መከላከያዎች ሲዳማ ቡናን 6-2 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፈው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እየተመሩ ከቋሚ ተሰላፊዎቹ ግማሽ የሚሆኑትን በአዲስ መልኩ ለውጥ አድርገው በአዲስ መልክ ወደ ጨዋታው ሲቀርቡ በአንጻሩ መከላከያዎች ከአምናው የቡድን ስብስብ ውስጥ ከተደረጉ የተወሰኑ ለውጦች በስተቀር በተመሳሳይ የቡድን ስብስብ ወደ ጨዋታው ገብተዋል፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች መከላከያዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ኳስን መስርተው በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል መድረስ ችለዋል ፤ መዲና አወል ሁለት የንግድ ባንክ ተከላካዮችን አልፋ ያመከነቻት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ እንዲሁም ምስራች ላቀው ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የላከችውና ንግስቲ መአዛ የያዘችባት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡
በአንጻሩ ንግድ ባንኮች ረሂማ ዘርጋው ከመከላከያ የግብ ክልል ውጪ በቀጥታ አክርራ ሞክራ ወደ ውጪ የወጣባት ኳሶ በስተቀር ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡
በ24ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ረሂማ ዘርጋው አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሀዋሳ ከተማን ለቃ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የተቀላቀለችው አይናለም አሳምነው የመከላከያዋ ግብጠባቂ ማርታ በቀለን ስህተት ተጠቅማ ለአዲሱ ክለቧ የመጀመሪያውን ግብ ማስገኘት ችላለች፡፡
ከግቧ መቆጠር በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች የጨዋታውን የበላይነት በመውሰድ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለው ነበር ነገር ግን በ31ኛው ደቂቃ ሳይጠበቅ ኤልሳቤጥ ብርሃኑ ከረጅም ርቀት መከላከያን አቻ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት በአስገራሚ ሁኔታ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ይበልጥ አጥቅተው ለመጫወት በማሰብ ፅዮን እስጢፋኖስንና የካቲት መንግስቱን አስወጥተው ሀብታምነሽ ሲሳይንና ዙሊይካ ጁሃድን አስገብተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ 47ኛው ደቂቃ ላይ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን እጅግ ድንቅ ብቃትዋን ያሳየችው ምስራች ላቀው በግምት 27 ሜትር ከሚሆን ርቀት ማራኪ ግብ አስቆጥሯ ቡድኗን ዳግም መሪ ማድረግ ችላለች፡፡
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ እምብዛም ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ የግብ ሙከራዎችን አላስተናገደም፡፡
በ70ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታምነሽ ሲሳይ ከግራ መስመር ያሻማችውን ኳስ የመከላከያ ተጫዋቾች ለመከላከል ጥረት በሚያደርጉበት ቅፅበት ኳስ በእጅ በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ረሂማ ዘርጋው ብትመታም የመከላከያዋ ግብጠባቂ ማርታ በላይ ልታድንባት ችላለች፡፡
በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በቀጥተኛ አጨዋወት የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም መከላከያዎች ባሳዮት ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ጥረታቸው ሳይሰምር ቀርቷል፡፡
በጨዋታው ከቅድስተ ማርያም ዩኒቨርስቲ መከላከያን የተቀላቀለችው መዲና አወል ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ ችላለች፡፡
ጨዋታው በመከላከያ የ2-1 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ መከላከያ በ6 ነጥብና 5 ንፁህ ግብ ሊጉን መምራት ጀምረዋል፡፡