ሩሲያ በ2018 ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ፊፋ ጨዋታዎችን ሊመሩ የሚችሉ እጩ ዳኞችን ዛሬ ይፋ ሲያደርግ ኢትዮጵያዊው ባምላክ ተሰማ መካተት ችሏል።
ፊፋ በዝርዝሩ ውስጥ ከአፍሪካ ባምላክን ጨምሮ 5 የመሃል ዳኞችን ሲያካትት ከአውሮፓ 10፣ ከእስያ 6፣ ከሰሜን አሜሪካ 6፣ ከደቡብ አሜሪካ 6 እንዲሁም ከኦሽኒያ 2 የመሃል ዳኞች በመጀመርያው ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። ከህዳር 16-20 የመሰናዶ ሴሚናር ለእጩ ዳኞች የሚሰጥ ሲሆን ከዚህ ሴሚናር በኃላ ፊፋ የመጨረሻ ዝርዝሩን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
አመቱ ለባምላክ የተሳካ ነበር። የመሃል ዳኛው በአፍሪካ ዋንጫው ጨዋታዎችን መምራት የቻለ ሲሆን በቅርቡ የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በህንድ ሲያጫውት ከረጅም ግዜ በኃላ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ የመራ ኢትዮጵያዊ ለመሆን በቅቷል። ባምላክ በፊፋ ተመርጦ በውድድሩ ተሳታፊ ከሆነ ከ2006 በኃላ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ይሆናል። በ2006 ጀርመን ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ ላይ ልኡልሰገድ በጋሻው ረዳት ዳኛ እንደነበር ይታወቃል።
በዝርዝሩ ውስጥ የካፍ የአመቱ ምርጥ አርቢትር ተብሎ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት የተመረጠው ጋምቢያዊው ባካሪ ፓፓ ጋሳማ እና በእስያ ስሙ የገነነው የኡዝቤኪስታኑ ራቭሻን ኢርማቶቭ መካተት ችለዋል።