አብዱልከሪም ለኢትዮጵያ ቡና ፈርሟል

ኢትዮጵያ ቡና የአብዱልከሪም መሃመድን ዝውውር ዛሬ አጠናቋል፡፡ የመስመር ተከላካዩ ለቡና የ2 አመት ውልም ፈርሟል፡፡
ተጫዋቹ ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ተገኝቶ ከክለቡ ኃላፊዎች ጋር በፊርማ ገንዘቡ ጉዳይ ላይ ድርድር ሲያደርግ የነበረ ሲሆን ከጠየቀው 1.5 ሚልዮን ብር በ100ሺህ ብር ቀንሶ በ1.4 ሚልዮን ብር ከስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡ ቡናም ለተጫዋቹ በ2 አመት ውስጥ 1.4 ሚልዮን ብሩን ሊከፍልና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ሊያሟላ ተስማምቶ ዛሬ ፊርማውን በፌዴሬሽን ተገኝቶ አኑሯል፡፡
በደቡብ ፖሊስ የክለብ እግርኳስን የጀመረው አብዱልከሪም ብሩህ ተስፋ ከሚታይባቸው ወጣት የመስመር ተከላከዮች አንዱ ነው፡፡ በሁለቱም መስመሮች መጫወት የሚችለው አብዱልከሪም ዘንድሮ በሲዳማ ቡና ያሳየው ግሩም እንቅስቃሴም ለብሄራዊ ቡድን እንዲመረጥ አስችሎታል፡፡

ክለቡ ሮቤል ግርማን እንደሚያሰናብት የሚጠበቅ በመሆኑ አብዱልከሪም የግራ መስመሩን ስፍራ በቋሚነት ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቡና ከአብዱልከሪም በተጨማሪ ከሀዋሳ መልቀቁ አይቀርም የተባለለትን ተከላካዩ ግርማ በቀለን ለማስፈረምና በክለቡ የሚገኘው አስቻለው ግርማን ውል ለማደስ በድርድር ላይ ነው ተብሏል፡፡

ያጋሩ