የእለቱ ዜናዎች : ሰኞ ህዳር 11 ቀን 2010

​ብሔራዊ ቡድን

ለሴካፋ ዋንጫ ዝግጅት 27 ተጨዋቾችን በዛሬው እለት መጥራታቸው ይታወቃል። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በጠሯቸው ተጫዋቾች ዙርያ አንዳንድ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ ባለባቸው ወሳኝ ጨዋታ ምክንያት ተጨዋቾቻቸውን ለመላክ እንደሚቸገሩ እየገለፁ እንደሆነም ሰምተናል። ይህ የሚሆን ከሆነ ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሴካፋ ውድድር ከባድ ፈተና እንደሚሆንባቸውና ሌሎች ተጨዋቾችን በአማራጭነት ለመምረጥ ሊገደዱ ይችላሉ።

የጅማ አባጅፋር ቅጣት 

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ጨዋታ በጅማ አባ ጅፋር እና ሀዋሳ ከተማ መካከል በተካሄደው ጨዋታ ‹‹የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ተፈፅሟል፡፡ የዕለቱ ረዳት ዳኛ ከደጋፊዎች በተወረወረ ቁስ ተፈንክተዋል፡፡›› በሚል የፌዴሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ የ150 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና በሜዳው ማድረግ የሚገባውን ሁለት ጨዋታ ከከተማው 150 ኪሎ ሜትር በላይ በሚገኝ ሜዳ እንዲጫወት መወሰኑ ይታወቃል። ውሳኔውን ተከትሎ ጅማ አባ ጅፋር በወቅቱ የተከሰተውን ችግር መንስኤ እና ሌሎች ምክንያቶችን በመጥቀስ ሊያስቀጣ የሚያስችል ምክንያት የለም በማለት ለፌዴሬሽኑ ይግባኝ  ሰሚ ኮሚቴ አቤቱታውን ያቀረበ ሲሆን ሶከር ኢትዮዽያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንዳረጋገጠችው ከሆነ ጅማ አባ ጅፋር ላይ የተጣለው የቅጣት ውሳኔ በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውድቅ ተደርጎ ሊሻር እንደሚችል ነው።

የፋሲል ከተማ ቅሬታ

አክሊሉ አየነው አስቀድሞ የፈረመው በህጋዊ መንገድ ለፋሲል ከተማ ነው በማለት የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ንብረትነቱ የእኛ ነው ማለታቸውን ተከትሎ ዲሲፒሊን ኮሚቴ አክሊሉን ለፋሲል 6 መቶ ሺህ ብር እንዲከፍል ሲወስን አክሊሉ አያናው ቅሬታውን ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ባስገባው ደብዳቤ መሰረት ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የተጨዋቾች ዝውውር ደንብ መሰረት አድርጎ አክሊሉ አያናው ወደ የትኛውም ክለብ አምርቶ መጫወት እንደሚችል ውሳኔ በመስጠት ጉዳዩ እልባት ያገኘ ቢሆንም ፋሲል በውሳኔ ደስተኛ እንዳልሆነ በመግለፅ  ፌዴሬሽኑ ጉዳዮን በድጋሚ እንዲያጤነው አስገንዝቦ ይህ ካልሆነ ያሉትን ሰነዶችን በመያዝ ወደ ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንደሚያመራ ለሶከር ኢትዮዽያ ገልፀዋል።

ሀ17 ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 

በዩራጓይ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአለም ከ17 አመት በታች የሴቶች አለም ዋንጫ ማጣርያ ኬንያን በፎርፌ በማሸነፍ ለቀጣዩ ማጣርያ ጨዋታ ከናይጄሪያ ጋር የተመደበው የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቡድኑን አሰቀድመው ጥሪ ከተደረገላቸው ተጨዋቾች መካከል በተወሰኑት ላይ ማስተካከያ በማድረግ ባሳለፍነው ሳምንት ለ24 ተጨዋቾች ጥሪ ተደርጎላቸው በኢትዮዽያ ሆቴል በማረፍ እንዲሁም የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች በማድረግ ዝግጅታቸውን አጠናክረው እየሰሩ ይገኛሉ። ቡድኑ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ተበትኖ የጨዋታው ቀን ሲቃረብ በድጋሚ እንደሚጠሩ የተነገረ ቢሆንም ከጨዋታው ቀን መቅረብ ጋር ተያይዞ ቡድኑ እንደማይበተንና አብረው ዝግጅታቸውን እየሰሩ በሆቴል እንደሚቆዩ ሰምተናል። አሁን ባገኘነው መረጃ ደግሞ ከተጠሩት መካከል ሁለት የመከላከያ እና አንድ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ሳይመጡ በመቅረታቸው በአሁኑ ሰአት የሚገኙት ተጫዋቾች ቁጥር 22 መሆናቸው ታውቋል።

ሴካፋ

ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው በኬንያ አስተናጋጅነት ከህዳር 24 ጀምሮ በሚካሄደው የሴካፋ ዋንጫ ላይ ከኢትዮጵያ የተወከለ ብቸኛ ዳኛ በመሆን ወደ ኬንያ የሚያመራ ይሆናል፡፡

ከፍተኛ ሊግ

ቅዳሜ እና እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች በተጀመረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ክለቦች መክፈል የሚገባቸውን የዳኞች እና የታዛቢዎችን ክፍያ በወቅቱ ከፍለው ባለማጠናቀቃቸው ምክንያት በአንደኛ ሳምንት በሁለቱም ምድብ መካሄድ ከነበረበት 16 ጨዋታ የተካሄደው አራት ጨዋታ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ከፌዴሬሽኑ ባገኘነው መረጃ መሰረት ክፍያውን ያላጠናቀቁ ቡድኖች በሙሉ ክፍያቸውን ከፍለው በማጠናቀቃቸው ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ  የከፍተኛ ሊግ ውድድር ከሁለተኛው ሳምንት እንደሚደረግ እና የመጀመርያው ሳምንት ላይ ያልተካሄዱ ጨዋታዎች ወደ ፊት በሚገለፅ ቀን እንደሚደረጉ ታውቋል።

1ኛ ሊግ 

በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በወንዶች ፆታ ከሚካሄዱ ውድድሮች በሦስተኛ እርከን በ63 ቡድኖች እና በ5 ምድብ ተከፍሎ የሚደረገው የአንደኛ ሊግ ውድድር ህዳር 24 በወጣለት መርሀ ግብር መሰረት እንደሚጀመር ፌዴሬሽኑ አረጋግጧል። የዘንድሮ የአንደኛ ሊግ ውድድር ከአምናው በተለየ በአዲስ የውድድር አቀራረብ ከየምድባቸው ከ1-3ኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ እና ከሁሉም ምድብ አንድ ጥሩ አራተኛ ቡድን ጨምሮ በ16 ቡድኖች ወደፊት በሚገለፅ ቀንና ቦታ በሚደረገው የማጠቃለያ ውድድር ስድስት ቡድኖች ወደ ከፍተኛው ሊግ የሚያድጉ ይሆናል።

ቶክ ጀምስ 

የእግርኳስ ህይወቱን በክለብ ደረጃ በኢትዮዽያ ቡና የጀመረው ቶክ ጀምስ ከኢትዮዽያ ቡና ከተለያየ በኋላ ወልድያ በኋላም ለኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ሲጫወት ቆይቶ ባለፈው አመት ሁለተኛው ዙር ላይ ከክለቡ ጋር ከተለያየ በኋላ ክለብ አልባ በመሆን የውድድር አመቱን ቢያሳልፍም ዘንድሮ ከኢራቅ ክለብ የሙከራ እድል አግኝቶ የተወሰኑ ቀናት በሙከራ ቢቆይም ሙከራው ሳይሳካ ወደ ሀገር ቤት መመለሱን ሰምተናል። የዘንድሮ አመት የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከመዘጋቱ ጋር ተያይዞ ቀጣዩ የዝውውር መስኮት እስከሚከፈት ድረስ ቶክ ክለብ አልባ ሆኖ የሚቆይ ይሆናል፡፡

የፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ

የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ባለፈው አርብ ባደረገው ስብሰባ የአስመራጭ ኮሚቴ ለመምረጥ እና ሌሎች ተያይዥነት ባለቸው ጉዳዮች ዙርያ ለመነጋገር ህዳር 14 ቀን በኢንተርኮንትኔታል አዲስ ሆቴል አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ መደረጉ ይታወቃል። በጉባኤው ላይ የፊፋ ተወካዮች እንዲገኙ ጥሪ ተደረገ ሲሆን በጉባኤው ላይ ለሚገኙ ተሳታፊዎች በሙሉ ወጪያቸውን ፌዴሬሽኑ እንደሚሸፍንም ሰምተናል።

በተያያዘ ዜና የትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአቶ ተክለወይኒ አሰፋ ምትክ ነገ በፕሬዝደንት እና በስራ አስፈፃሚነት የሚወከሉትን ተወካዮች ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *