ግርማ በቀለ በሀዋሳ መውጫ በር ላይ ሲቆም በረከት ይስሃቅ ወደ ቀድሞ ክለቡ ሊመለስ ይችላል

 

የሀዋሳ ከነማው ተከላካይ ግርማ በቀለ ከክለቡ ጋር የመቆየቱ ነገር ያበቃለት ይመስላል፡፡ ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ኮንትራቱን የማደስ ፍላጎቱ የተቀዛቀዘ ሲሆን ከክለቡ ወጥቶ አዲስ ፈተና መጋፈጥ እንደሚፈልግ ተነግሯል፡፡ ተከላካዩ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ድርድር እያደረገ ቢሆንም እስካሁን በሚከፈለው ገንዘብ ዙርያ ሊስማሙ እንዳልቻሉ ተጠቁሟል፡፡

ሀዋሳ ከነማ ግርማ በቀለን ከለቀቀ ከአዲስአለም ተስፋዬ በኋላ ክለቡን የለቀቀ 2ኛው ተከላካይ ይሆናል፡፡ አዲስአለም ለአዳማ ከነማ እና ሀዋሳ ከነማ ፊርማውን አኑሮ ውዝግብ ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የደደቢቱ አጥቂ በረከት ይስሃቅ ወደ ቀድሞ ክለቡ ሊመለስ እንደሚችል ተነግሯል፡፡ በረከት በደደቢት ቀሪ የአንድ አመት ኮንትራት ቢኖረውም በቤተሰብ ጉዳይ ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ሀዋሳ ከነማን ሊቀላቀል ይችላል ተብሏል፡፡

ከደደቢት ባገኘነው መረጃ መሰረትም ሀዋሳ ከነማ በረከትን በተመለከተ ለክለቡ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ደደቢት ጥያቄውን እንደሚያጤው ተነግሯል፡፡ ከሌሎች ክለቦች ተጫዋች ካላስፈረሙም ምናልባትም በረከትን ላይለቁት እንደሚችሉ ታወቋል፡፡

በረከት በ2005 ለኤሌክትሪክ ከመፈረሙ በፊት ለሀዋሳ ከነማ መጫወቱ የሚታወስ ነው፡፡

ያጋሩ