​የእለቱ ዜናዎች | ማክሰኞ ህዳር 12 ቀን 2010

የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን

ለሴካፋ ዋንጫ ዝግጅት በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጥሪ ከተደረገላቸው 27 ተጫዋቾች መካከል አብዛኛዎቹ ዛሬ በካፒታል ሆቴል በመገኘት ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ነገ ጠዋት የመጀመርያ ልምምዳቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።


የትግራይ እጩዎች

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን ለመምራት በሚደረገው ቀጣይ ምርጫ ከትግራይ በስራ አስፈፃሚነት ይወክላሉ ተብለው የነበሩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ መነሳታቸውን ተከትሎ በምትካቸው የሚወክሉትን እጩ እስካሁን የክልሉ ፌዴሬሽን በይፋ ያሳወቀው ባይኖርም እንዲወዳደሩ ጥያቄ ቀርቦላቸው ፍቃደኛ መሆናቸው የገለፁት የደደቢት እግርኳስ ክለብ መስራች እና የቀድሞ ፕሬዝደንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ለስራ አስፈፃሚነት እና የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ም/ዳይሬክተር አቶ ወ/ገብርኤል መዝገቡ ለፕሬዝደንትነት እንደሚወክሉ ተሰምቷል።

በተያያዘ ዜና ሌሎች ክልሎች እስካሁን ከአንድ በላይ እጩ ተወካዮቻቸውን ያላሳወቁ ሲሆን እንደውም አንዳንድ ክልሎች ከአንድ በላይ እጩ ተወካይ እንደማያቀርቡ እየተነገረ ባለበት ሁኔታ ሁሉም የመጨረሻ እጩ ተወካዮቻቸውን እስከ ህዳር 15 ቀን መርጠው በማጠናቀቅ ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።


የአሰልጣኞች ወቅታዊ ጫና 

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ባልተሟላ መርሀግብር እስከ ሦስተኛ ሳምንት ድረስ በቀጠለበት በአሁኑ ሰአት ከወዲሁ ከውጤት መጥፋት እና ከደጋፊ የበረታ ተቃውሞ አንፃር አንዳንድ አሰልጣኞች ጫና ውስጥ እንደገቡ ተነግሯል። ምን አልባት የውጤት ቀውሱ በአራተኛ እና አምስተኛ ሳምንት የሚቀጥል ከሆነ በዘንድሮ የውድድር አመት የመጀመርያ ተሰናባች አሰልጣኝ የምንመለከትበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አንዳንድ ፍንጮች እየታዩ መሆናቸውን ለክለቦቹ ቅርበት ካላቸው አካላት ጥቆማ ደርሶናል።


የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን

ባሳለፍነው እሁድ በይፋ የተጀመረውና በ14 ቡድኖች መካከል የሚካሄደው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ከሰባት ጨዋታ ስድስቱ የተካሄዱ ሲሆን አዲስ መጪዎቹ ፋሲል ከተማ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ድል ቀንቷቸዋል። የክፍለ ከተማ ቡድኖች አብዛኛዎቹ ሽንፈትን ያስተናገዱበት ውጤትም ተመዝግቧል።


ጥረት ኮርፖሬት
3 – 1 ሻሸመኔ ከተማ

ወጣቶች አካዳሚ 0 – 2 ፋሲል ከተማ 

ቂርቆስ 2 – 1 አቃቂ

አአ ከተማ 2 – 1 ልደታ

አርባምንጭ ከተማ 2 – 1 ቦሌ

ጥሩነሽ ዲባባ 2 – 0 ንፋስ ስልክ ላፍቶ


ረቡዕ ህዳር 13 ቀን 2010


09:00
ኢትዮዽያ ቡና ከ ቅድስት ማርያም ዩ.

በሌላ ዜና እስከ ሁለተኛ ሳምንት ድረስ በጠንካራ ፉክክር እየተደረገ የሚገኘው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ዛሬ በወጣለት መርሐግብር መሰረት ይደረጋል ተብሎ የነበረው የኢትዮ ኤሌትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ የሴቶች ቡድን ለኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከ3 በላይ ተጨዋቾችን በማስመረጡ ምክንያት ሳይደረግ ቀርቷል።


ሙከራ

ፋሲል ከተማ ትውልደ ኢትዮዽያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነ ማርቲነስ ዊልያም ለተባለ ተጨዋች የሙከራ ጊዜ እየሰጠ ይገኛል። በእናቱ ኢትዮዽያዊ እንደሆነ የተነገረው ዊልያም ለአሜሪካ ሀ17 ብሔራዊ ቡድን እንደተጫወተና በሲዊዲን የተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ እንዳሳለፈ የተጠቆመ ሲሆን የሙከራው ጊዜ በተሳካ ሁኔታ የሚጠናቀቅ ከሆነ የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛው ዙር እንደተጠናቀቀ ለፋሲል ሊፈርም እንደሚችል የክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ መረጃውን አድርሷል።


የሴቶች 1ኛ ዲቪዚዮን ተቋረጠ

ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘው የኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ላልተወሰነ ቀናት መቋረጡን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው ማረጋገጫ ያሳያል። ለመቋረጡ እንደ ምክንያት የቀረበውም ከ17 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ እና የወዳጅነት ጨዋታዎች እንዲያገኝ በማሰብ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ተስተካካይ ጨዋታ እንዲኖረው ማድረጉ በውድድሩ ጉዞ ላይ ችግር እንዳይፈጥር በማሰብ በሦስተኛ ሳምንት ድሬደዋ ላይ እሁድ ድሬደዋ ከተማ ከ መከላከያ ከሚያደርጉት ጨዋታ በስተቀር ሌሎች ጨዋታዎች መቋረጣቸውን ሰምተናል።


ከ17 እና 20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ 

በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አወዳዳሪነት ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል ከ17 እና ከ20 አመት በታች የወንዶች ፕሪምየር ሊግ እስካሁን ተሳታፊ ቡድኖች ፣ ውድድሩ የሚጀምርበት ቀንና የምድብ ድልድል እስካሁን አልታወቀም። የMRI ምርመራ ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን አሁን የቀረው የመጨረሻ ውጤት ይፋ ከተደረገ በኋላ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ የዕጣ ማውጣት እና የውድድሩ መጀመርያ ቀን ይፋ ይደረጋል ተብሏል። በዚህ የእድሜ እርከን በሚደረገው ተዟዙሮ መጫወት በታዳጊዎቹ የነገ ህይወት ላይ ተፅዕኖ አለው በማለት ክለቦች በተደጋጋሚ የሚያቀርቡት ቅሬታ መልስ አግኝቶ ምን አልባት የውድድሩን ፎርማት በዞን ከፍሎ ለማጫወት የሚረዳው ሀሳብ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል ።


የቅዱስ ጊዮርጊስ አካዳሚ 

በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያነት ግንባታው ተጠናቆ ባሳለፍነው አመት መጋቢት ወር ላይ የተመረቀው አካዳሚው በበላይነት እንዲመሩት ስፔን ከሚገኘው ሶክስና የእግርኳስ ማእከል ጋር የውል ስምምነት መፈራረሙ ይታወቃል። አሁን ባለው ሁኔታ አካዳሚው በይፋ ስራውን ለመጀመር አንዳንድ ቅድመ ሆኔታዎችን እያከናወኑ ሲሆን ጥር ወር ላይ 50 ታዳጊዎችን በመቀበል ስራዉን በይፈ እንደሚጀምር ሰምተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *