በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ሊካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት ሳይካሄድ በቀሪ ጨዋታነት ቆይቶ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በውዝግቦች ታጅቦ ተካሂዶ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በሳምንቱ መጨረሻ ከወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ከነበረው ጨዋታ የሁለት ተጨዋቾች ቅያሪ ያደረገው ሲዳማ ቡና በ4-3-3 ቅርፅ በአጥቂዎቹ ፍጥነት እና ጉልበት ላይ ተመስርቶ ወደሜዳ ገብቷል። ከመከላከያው ጨዋታ በተለየ የ4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፍ በመጠቀም እና በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ አብዱሰላም ኑሩን በአስራት ቱንጆ በመተካት ጨዋታውን የጀመረው ኢትዮጵያ ቡናም መስዑድ መሀመድን ወደ ቋሚ አሰላለፉ አስገብቷል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በአመዛኙ በሲዳማ ቡና ሜዳ ላይ ያጋደለ ነበር። የዳይመንድ ቅርፅ ይዞ የታየው የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል ጫፍ ላይ የተሰለፈው ኤልያስ ማሞ በሲዳማ ቡና የተከላካይ መስመር ፊት ላይ እየተገኘ ኳሶችን በመቀበል እና በማሰራጨት የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመምራት በኩል ጥሩ ቢንቀሳቀስም ቡድኑ የፈጠራቸው የግብ ዕድሎች ጥርት ያሉ ነበሩ ለማለት አያስደፍርም። 6ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሀመድ ከርቀት የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር ኤልያስ ማሞ ከተመሳሳይ ርቀት ላይ ያደረገው ሙከራም በመሳይ አያኖ ተይዞበታል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ የሲዳማን የተከላካይ ክፍል ሰብሮ የገባባቸው አጋጣሚዎች ሁለት ነበሩ። በዚህም 20ኛው ደቂቃ ላይ ሳኑሚ ከኤልያስ የተቀበለውን ኳስ ሞክሮ የጎን መረብ ላይ ሲያርፍ 27ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑ በግራ መስመር ባደላ መጥቃት ጥሩ አጋጣሚ ቢፈጥርም ወደ ረባ ሙከራ መለወጥ ግን ሳይችል ቀርቷል።
አብዛኛውን ሰዐት ተጠንቅቀው በመጫወት ያሳለፉት ሲዳማዎች ኳስ ይዘው ማጥቃት በሚጀምሩበት ወቅት እንቅስቃሴያቸው በዋነኝነት የተመረኮዘው በመስመር አጥቂዎቻቸው አዲስ ግደይ እና አቡዱለጢፍ መሀመድ ላይ ነበር። ሆኖም 8ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ከቀኝ መስመር ላይ አክርሮ ሞክሮት ሀሪሰን ካወጣበት ኳስ ውጪ በመጀመሪያው አጋማሽ ሌላ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ቡድኑ ጥሩ የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ አጋጣሚዎች ቢፈጠሩለትም ወደ መስመር አጥቂዎቹ የሚላኩ ኳሶች የተመጠኑ ሊሆኑ አለመቻላቸው እና የአጥቂዎቹ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ መሆኑ ከሙከራ እንዲርቁ አድርጓቸዋል። ከዚህ ውጪ በመጀመርያው አጋማሽ አስገራሚ የነበረው 34ተኛው ደቂቃ ላይ ትርታዬ ደመቀ እና ሳሙኤል ሳኑሚ የፈጠሩትን ግብግብ ዳኛው ያለማስጠንቀቂያ ካርድ ማለፋቸው ነበር።
ሁለተኛውን አጋማሽ ፈጠን ባለ ማጥቃት የጀመሩት ሲዳማዎች 46ኛው ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ መሀመድ ካደረገው የረጅም ርቀት ሙከራ 7 ደቂቃዎች በኃላ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ግቧም የመስመር አጥቂው አዲስ ግደይ የኤፍሬም ወንደሰንን ስህተት በመጠቀም ኳስ ነጥቆ ቶማስ ስምረቱን እና ሀሪሰንን በግሩም ሁኔታ በማለፍ ከመረብ ያገናኛት ነበረች። ከግቡ በኃላ ሲዳማዎች ወደኃላ ተስበው መከላከሉ ላይ ትኩረት ሲሰጡ ታይተዋል። ይሄን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና በደቂቃዎች ልዩነት በሳምሶን ጥላሁን እና ሳሙኤል ሳኑሚ አማካይነት ሙከራዎችን አድርጓል። የቡና ተጨዋቾች በሲዳማ ሳጥን ዙሪያ ያደርጉት የነበረው ተደጋጋሚ እንቅስቃሴም የፍፁም ቅጣት ምት እንዲያገኙ ያገዘ ነበር። ከኤልያስ ማሞ የተነሳውን ኳስ አበበ ጥላሁን በጁ በመንካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት 68ኛው ደቂቃ ላይ ራሱ ኤልያስ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ከዚህ በኃላ የነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ በተጨዋቾች የሜዳ ላይ ግጭት እና ጉዳትን ተከትሎ በሚሰጡ የህክምና ዕርዳታዎች የታጀበ ነበር። 74ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛሀኝ ከግራ መስመር ያሳለፈለትን ኳስ አዲስ ግደይ ሳይጠቀምበት ሲቀር እና ከደቂቃ በኃላ በረከት ይስሀቅ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ቺፕ አርጎ ለማስቆጠር ሲሞክር መሳይ ሲያወጣበት የታዩት እንቅስቃሴዎች ቡድኖቹ ለግብ የቀረቡባቸው ነበሩ። ከነዚህ ሙከራዎች ውጪ በሂደት በሽኩቻዎች የተሞላው ጨዋታ 88ኛው ደቂቃ ላይ የቀይ ካርድ አስተናግዷል። ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ሀይል ቀላቅሎ ሲጫወት የታየው ትርታዬ አስናቀ ሞገስን ከኳስ ውጪ በመማታቱ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
የስቴድየሙ ድባብ ሙሉ ለሙሉ የተቀየረውም ከዚህ በኃላ ነበር። ፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈራ ዘጠናው ደቂቃው ከተጠናቀቀ በኃላ የጨመሯቸው 5 ደቂቃዎች ለተፈጠረው ደስ የማይል ድባብ መጀመሪያ ነበሩ። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች የሲዳማ ቡና ተጨዋቾች በየጊዜው በሜዳ ላይ እየወደቁ ያባከኑት ደቂቃ ከጭማሪው በላይ ነው በሚል ከኮሚሽነሩ ጋር እሰጣገባ ውስጥ ገብተውም ታይተዋል። በተለይም ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በተደጋጋሚ እየወደቀ ያባከናቸው ደቂቃዎች በስቴድየሙ ለተፈጠረው ውጥረት ዋነኛ መንስኤ ነበሩ። የቡድኑ ወጌሻ አበባው በለጠ ዕርዳታ ለማድረግ ወደ ሜዳ ሲገባ ይወስዳቸው የነበሩት ዘለግ ያሉ ደቂቃዎችም ሁኔታውን አባብሰውታል።
በጭማሪዎቹ ደቂቃዎች ኤልያስ ማሞ ከግራ መስመር ያሻማውን ቅጣት ምት ሙጃይድ መሀመድ በግንባሩ ለማውጣት ሲሞክር ኳስ ወደግብ አምርታ የነበረ ሲሆን መሳይ ለጥቂት አውጥቷታል። ሜዳ ላይ ከዚህ እንቅስቃሴ ውጪ የታየ ነገር ባይኖርም ከሜዳ ውጪ የነበረው ሁኔታ ግን በጣም አሳዛኝ ነበር።
በጭማሪው ማነስ የተበሳጩት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በዳኛው ላይ ያሰሙት የነበረው ተቃውሞ በፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ላይ ቀጥሎ ሳንቲሞችን እና የውሀ ፕላስቲክ ጠርሙሶች እስከ መወርወር ደርሶ ነበር። አወዛጋቢ የዳኛ ውሳኔ የወለደው ይህ ተቃውሞም የጨዋታውን መንፈስ ሙሉ ለሙሉ ቀይሮት የእለቱ የስታድየም ዉሎ ተገባዷል።