ሴካፋ
ህዳር 24 ለሚጀምረው የሴካፋ ዋንጫ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ረፋድ ላይ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ልምምዱን አከናውኗል። ከምሳ በኋላ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት በክልል ከተሞች ላይ ለሚደረጉ ጨዋታዎች አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ዛሬ ወደ ክለቦቻቸው ያቀኑ ሲሆን አአ የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ የሚሰለፉ ተጫዋቾች በሆቴል እንደቀሩ እና ነገ ጠዋት ቀለል ያለ ልምምድ ሰርተው ወደ ክለቦቻቸው ለጨዋታ የሚያመሩ ይሆናል። የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድኑ 22 ተጫዋቾችን በመያዝ የፊታችን ዕሮብ ወደ ኬንያ የሚያቀና ይሆናል።
ሀ-17 ሴቶች ብሔራዊ ቡድን
ህዳር 24 በአአ ስታድየም ከናይጄሪያ ጋር የአለም ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 22 ተጫዋቾችን በመያዝ ማረፊያውን ኢትዮዽያ ሆቴል በማድረግ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። ትላንት ከንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጎ 3-0 በተሸነፈው ቡድን ዙርያ አሁን እየተሰማ ያለው አስገራሚ ዜና በ2008 ላይ በአሰልጣኝ አስራት አባተ በሚሰለጥነው ከ17 አመት የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ከነበሩት ተጨዋቾች መካከል የመከላከያዎቹ እመቤት አዲሱ እና ምስራች ላቀው በድጋሚ ከሁለት አመት በኋላ በአሰልጣኝ ሰላም ዘርይ ጥሪ መቅረቡ ነው። ተጫዋቾቹ እስከዛሬ ከቡድኑ ጋር ያልተቀላቀሉ ቢሆንም አሁን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር መቀላቀላቸውም ተሰምቷል። እነዚህ ሁለት ተጫዋቾች ባሳለፍነው ወር በአሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተው ኬንያን መግጠማቸው ይታወቃል። ከሁለት አመት በፊት ከ17 አመት በታች ፣ በዘንድሮ ከ20 አመት በታች ፣ አሁን ደግሞ እድሜያቸው ወደኋላ ተመልሶ ከ17 አመት በታች መጠራታቸው ጥሪውን አስገራሚ አድርጎታል።
የፌዴሬሽኑ ምርጫ
ትላንት በኢንተር-ኮንትኔታል አዲስ ሆቴል የተካሔደው የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ብዙ መተማመን በጎደለው ፣ የስብሰባ አካሄድ በሌለው መልኩ በመጨረሻው ሰአት 12 አስመራጭ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ መጠናቀቁ ይታወቃል። ዛሬ ከሰአት በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሁሉም አስመራጭ ኮሚቴዎች ተሟልተው በተገኙበት የመጀመርያ ስብሰባቸውን አካሂደዋል። ጤናማ ሆኖ በተጠናቀቀው ስብሰባቸው የመጨረሻውን የክልል እጩ ተመራጮች ስም ዝርዝር ከጽህፈት ቤቱ የተረከቡ ሲሆን ሰነዶቹንም በማሸግ ተፈራርመው ወጥተዋል። ከጥቂት ቀናት በኋላም ሰነዶቹን በመክፈት ለሚዲያ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንደ ኦሮምያ እና ትግራይ ያሉ ክልሎች ሙሉ ለሙሉ እጩ ተወካያቸውን ሲቀይሩ አማራ እና አአ ከተማ ተጨማሪ እጩ አቅርበዋል። አፋር ፣ ድሬደዋ ፣ ቤኒሻንጉል ፣ ሐረሪ ፣ ኢትዮ-ሱማሌ ፣ ደቡብ የእጩ ተወካይ ለውጥም ሆነ ተጨማሪ እጩ ያላቀረቡ ናቸው። አስገራሚ ውዝግብ እያስከተለ የሚገኘው እና በአስመራጭ ኮሚቴው ይዳኛል ተብሎ የሚጠበቀው ደግሞ የጋምቤላ ክልል እጩ ተወካይ ጉዳይ ነው።
የምርጫ ካርድ በገንዘብ
ታህሳስ 16 በአፋር ሰመራ ይካሄዳል ተብሎ ቀን የተቆረጠለት የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንታዊ እና በስራ አስፈፃሚነት የሚመሩት ግለሰቦች ተለይተው ታውቀዋል። ታዲያ ካሁኑ በርካታ ውዝግቦች እና የሴራ ንድፋ ሀሳቦች እየተሰሙ ሲሆን ለፕሬዝዳንትነት ከሚወዳደሩት እጩ ተመራጮች መካከል በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመጡ ተሳታፊዎችን በኢትዮዽያ ሆቴል በማሳረፍ የድምፅ ካርዳቸውን ለእነርሱ እንዲሰጡ የማግባባት ስራ እየተሰራ መሆኑን ታዝበናል። እግርኳሱ ብዙ መሰረታዊ ችግሮች በሚታዩበት በአሁኑ ወቅት ለእግርኳሱ ምንም በማይበጅ መልኩ የድምፅ ካርድን በገንዘብ ለመግዛት የሚደረገው መሯሯጥ ለምን ተፈለገ የሚለው የብዙ የስፖርት ቤተሰቦች መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው።
ቶክ ጀምስ
ባለፈው ዘገባችን ቶክ ጀምስ ወደ ኢራቅ በማቅናት የሙከራ እድል አግኝቶ ሳይሳካለት መመለሱን ጠቅሰን ነበር። ቶክ ጀምስ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ የሙከራ እድል እንዳላደረገ እና ብዙ አላስፈላጊ ነገሮች እንደተከሰተበት ተናግሯል ” አስቀድሜ ቅድመ ኮንትራት ፈርሜ ተስማምቼ የነበረው ኩረድ ለሚባል ክለብ ነበር። ሆኖም ከሄድኩ በኋላ ምክንያቱን በማላቀው ሁኔታ ባግዳድ ወደሚገኝ ሌላ ክለብ ወሰዱኝ። ለምንድነው ብዬ ብጠይቅ ወኪሎቼም ሆኖ ሌሎች አካላት መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ሙከራ ሳላደርግ ከሁለት ቀን የኢራቅ ቆይታ በኋላ ተመልሼ ወደ አአ ልመጣ ችያለው።” የሚለው ቶክ ብዙ ለሚዲያ የማይገልፃቸው ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች እንደገጠሙት ተናግሮ ወደ ኢራቅ የላኩት ወኪሎቹ እነማን እንደሆኑ ከመናገር ተቆጥቧል። በቀጣይም ከኢትዮዽያ ውጭ አልያም ሀገር ውስጥ ለአንዱ ክለብ ሊጨወት እንደሚችልም ለሶከር ኢትዮዽያ ፍንጭ ሰጥቷል ።
ጥቆማ
* የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፐርት ማህበር ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሰለሞን በቀለ በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ የሚያተኩር ከ60 ገፅ በላይ ያልበለጠ መፅሐፍ በቅርቡ ለንባብ እንደሚያበቁ ሰምተናል።
*የኢትዮዽያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኀበር ህዳር 23 የሁሉም የእግርኳስ ክለብ አመራሮች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ ሲምፖዚየም አዘጋጅቷለ።
* የኢትዮዽያ ዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ ለፕሪምየር ሊግ ዳኞች ብቻ የአካል ብቃት ፈተና ከህዳር 27 – 28 በአዲስ አበባ ስታድየም ይሰጣል። የ2010 የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ጅማሮ ላይ ሆኖ ከወዲሁ የዳኞች ጨዋታን የመቆጣጠር አቅምና የአካል ብቃት ጉዳይ ጥያቄ እያስነሳ ባለበት ሁኔታ ህዳር ወር መጨረሻ ላይ በሚሰጠው የአካል ብቃት ፈተና ላይ በትክክል ሊተገበር እንደሚገባ አስትያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።
*ግዙፍ የትጥቅ አምራች ኩባንያ የሆነው ማራቶን በሃገራችን ይፋዊ ቅርንጫፍ ከፍቷል። ጥራት ያላቸውን ትጥቆች በማቅረብ የሚታወቀውና መቀመጫውን በቱርክ ኢስታምቡል ያደረገው ይህ ትልቅ ኩባንያ ጉርድ ሾላ በሚገኘው ሴንቸሪ ሞል አንደኛ ፎቅ ላይ ቅርንጫፍ የከፈተ ሲሆን ነገ ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ በይፋ ቅርጫፍ መክፈቱን አስመልክቶ በሞናርክ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ይሆናል። ኩባንያው በኢትዮዽያ የሽያጭ ቅርንጫፍን እንዲከፍት ትልቁን አስተዋፆ ያደረገው የስፖርት ትጥቆች አቅርቦት ልምድ ያለው ጎ-ቴዲ ስፖርት መደብር ነው።
አሶሳ ከተማ እግርኳስ ክለብ
ከዚህ ቀደም የነበሩ መረጃዎችን ለማግኘት ብንቸገርም የወንዶች እግርኳስ ክለብን ሴት የቡድን መሪ በመሆን ሰትመራ አልተመለከትንም። ሆኖም ያለፉትን 3 አመታት በ1ኛ ሊግ ላይ በምድብ ሀ ተሳታፊ የሆነው የአሶሳ እግርኳስ ክለብ የቡድን መሪ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ወ/ሮ ይርጋለም ጌታሁን የወንዶች ክለብን በቡድን መሪነት የመሩ የመጀመርያው ሴት ሳይሆኑ አይቀርም። ወ/ሮ ይርጋለም ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ ሲናገሩ ” ስራው ከባድ ነው። ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ተዟዙሮ መጫወት ስለሆነና የቤተሰብ ኃላፊ ከመሆኔ ጋር ተደምሮ ስራው ቢከብድም ለተጫዋቾች እናት ሆነህ ከቀረብክ ስራው ቀላል ነው። ” ብለዋል።
የነገ መርሀ ግብሮች
ፕሪምየር ሊግ – 4ኛ ሳምንት
10:00 ድሬዳዋ ከተማ ከ ደደቢት (ድሬዳዋ)
11:30 መከላከያ ከ አዳማ ከተማ (አአ)
ከፍተኛ ሊግ – ምድብ ሀ
09:00 ኢከስኮ ከ ሽረ እንዳስላሴ (ለገጣፎ)
ምድብ ለ
09:00 ደቡብ ፖሊስ ከ ሀላባ ከተማ (ሀዋሳ)