ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ፡ ንግድ ባንክ እና ደደቢት ለፍፃሜ ደረሱ

በሁለት ምድቦች ተከፍሎ ሲካሄድ የከረመው የዘንድሮው የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በ8 ቡድኖች መካከል ወደሚደረግ የጥሎማለፍ ደረጃ ተሸጋግሮ አሁን ለመጨረሻው ምእራፍ የደረሱትን ቡድኖች ለይቷል፡፡

ዛሬ በሃዋሳ በተካሄዱት ሁለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች የአምናዎቹ የፍፃሜ ተፋላሚዎች ደደቢት እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ቀን 8፡00 ላይ ከምድብ ሀ በ9 ነጥቦች አንደኛ ሆኖ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የገባው ደደቢት ከምድብ ለ በ4 ነጥቦች በ2ኝነት ወደ ግማሽ ፍፃሜ ከተሸጋገረው ዳሽን ቢራ ጋር ባደረጉት ፍልሚያ መደበኛውን 90 ደቂቃ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ፈፅመዋል፡፡ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የፍፁም ቅጣት ምቶችም ደደቢት 11 ለ 9 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወደ ፍፃሜው ማለፉን አረጋግጧል፡፡

በ10፡00 ምድብ ‹ሀ› ን በ9 ነጥቦች በበላይነት ያጠናቀቀው የአምናው ቻምፒዮን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአስተናጋጇ ከተማ ክለብ የሆነው ሀዋሳ ከነማን በቀላሉ 4-0 አሸንፎ ለፍፃሜ አልፏል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የድል ግቦች ህይወት ደንጊሶ አንድ ስታስቆጠር ሽታዬ ሲሳይ ሶስት ግቦችን አስቆጥራ ሃት-ትሪክ ሰርታለች፡፡

የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ሽታዬ ሲሳይ በ36 ግቦች ስትመራ የሀዋሳ ከነማዋ ሎዛ አበራ በ30 ግቦች ትከተላለች፡፡ ሌሏዋ የንግድ ባንክ አጥቂ ረሂማ ዘርጋ በ27 ግቦች 3ኛ ደረጃን ይዛ ትከተላለች፡፡

የፍፃሜው ጨዋታ በአምናው ተፋላሚዎች ደደቢት እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል እሁድ በሃዋሳ ስታድየም ይደረጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *