በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው ከምድብ ሀ ሽረ እንዳስላሴ ሲያሸንፍ በምድብ ለ ደቡብ ፖሊስ ከ ሀላባ ከተማ አቻ ተለያይተዋል።
ምድብ ሀ (በአምሀ ተስፋዬ)
ለገጣፎ ላይ ኢኮስኮ ሽረ እንዳስላሴን አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል። በፈጣን እንቅስቃሴ እና ከባድ ንፋስ ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ ሽረ የተሻለ የግብ ሙከራዎች አድርጓል። በ13ኛው ደቂቃ ላይ ፍስሃ ታፈሰ በግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ልደቱ ለማ ወደ ግብ አክርሮ ቢመታውም የኢኮሥኮ ግብ ጠባቂ አሰግድ ታምሬ ሲያድንበት በ32ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ዮሐንስ የመታውን ቅጣት ምት በድጋሚ የኢኮሥኮ ግብ ጠባቂ አድኖበታል፡፡ በ38ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በመስመር በኩል ጅላሎ ሻፊ እና ብሩክ ገ/አብ በአንድ ሁለት ቅብብል ያሳለፉት ኳስ ሣሙኤል ተስፋዬ ወደ ግብ ቢሞክራትም ተከላካይ ደርሶ አድኖበታል።
በኢኮሥኮ በኩል በ22ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ብሩክ ሀዱሽ ወደ ግብ መትቶ በግቡ አግዳሚ ለጥቂት የወጣበት እና በ41ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ አቤል ታሪኩ ከግብ ጠባቂው ተገናኝቶ በግቡ አናት ላይ የወጣበት ሙከራ ከባዱ ሙከራ ነበር፡፡
ከዕረፍት መልስ ኢኮሥኮ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም በ79ኛው ደቂቃ ላይ ጅላሎ ሻፊ ላይ በተሰራው ጠፋት የተገኘውን ቅጣት ምት ብሩክ ገብረአብ አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ግብነት ተለውጦ ሽረ እንዳስላሴን ከሜዳው ውጪ ወሳኝ 3 ነጥብ ይዞ እንዲመለስ አስችሎታል።
ምድብ ለ (በቴዎድሮስ ታከለ)
ሀዋሳ ከተማ ስታድየም (ሰው ሰራሽ ሳር) ላይ ደቡብ ፖሊስ ከ ሀላባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም ግብ ሳይቆጠር ቀርቷል። በተለይም ስንታየሁ መንግስቱ የግብ ጠባቂው መኳንንት አሸናፊን መውጣት አይቶ የሞከረው ኳስ በሀላባ በኩል ፤ አየለ ተስፋዬ ደግሞ በደቡብ ፓሊስ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ አድርገዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ 72ኛው ደቂቃ ላይ አበባየሁ ዮሀንስ ከቅጣት ምት ያሻማትን ኳስ አቤኔዘር አቱ አስቆጥሮ ደቡብ ፓሊስን ቀዳሚ አድርጎል። ከግቧ በኃላ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው የተጫወቱት ፖሊሶች የተከላካይ መስመራቸው ለመልሶ ማጥቃት በመጋለጡ በ82ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ተመስገን ይልማ ከቀኝ መስመር ያሻገራትን ኳስ የቀድሞው የድቻ አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱ ከመረብ አሳርፎ ሀላባ ከተማ ከሜዳው ውጭ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል ጫወታውም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡