በአዲስ አባባ ስታድየም በብቸኝነት በተደረገው የሊጉ አራተኛ ሳምንት መርሀግብር ወልዋሎ ዓ.ዩ ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3-1 አሸንፏል።
የአሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ ቡድን አርባምንጭን ከሜዳው ውጪ ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ ኄኖክ ካሳሁንን በጥላሁን ወልዴ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል። ተጨዋቾችን አፈራርቆ የመጠቀም አካሄድ እየተከተለ ያለው ወልዋሎ በበኩሉ ከሲዳማ ቡና ጋር ያለግብ ከተለያየበት ጨዋታ የአምስት ተጨዋቾች ለውጥ ሲያደርግ በዝውውር መስኮቱ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያስፈረማቸው በረከት ተሰማ ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ሙላለም ጥላሁንን በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ አካቶ ነበር።
ጨዋታው በጀመረባቸው ደቂቃዎች ላይ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው ሜዳ የገቡት ወልዋሎዎች ተጭነው መጫወት ችለዋል። በርግጥ አራተኛ ደቂቃ ላይ ከድር ሳሊህ የኤሌክትሪኩን ግብ ጠባቂ ዮሀንስ በዛብህን አልፎ ከሳተው ኳስ ውጪ ቡድኑ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን አልፈጠረም። ሆኖም የቡድኑ ሁለተኛ አደገኛ ሙከራ በመስመር አጥቂው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ አማካይነት ወደ ጎልነት ተቀይሯል። ፕሪንስ እንየው ካሳሁን በመስመር ይዞ ገብቶ ያሳለፈለትን እና በኤሌክትሪክ ተከላካይ የተጨረፈውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ መሬት ለመሬት በመምታት ነበር ያስቆጠረው።
​
የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ 27ኛው ደቂቃ ላይም በተመሳሳይ መልኩ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ እንዲሁ የተጨዋቹ ሌላኛው ጠንካራ ሙከራ ሆኖ ታይቷል። ከዚህ ውጪ ወልዋሎዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ለጎል የቀረቡበት አጋጣሚ 41ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር የተሰጠውን ቅጣት ምት ሙሉአለም ጥላሁን በቀጥታ መቶ የግቡ ቋሚ ሲመልስበት የታየ ነበር። ቢጫ ለባሾቹ ከሜዳቸው ውጪ ይጫወቱ እንጂ በሊጉ ባልተለመደ ሁኔታ ግቦችን ለማስቆጠር እና በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል ላይ በርካታ ደቂቃዎችን ለማሳለፍ የነበራቸው ድፍረት የሚበረታታ ነበር። ሆኖም የቡድኑ የማጥቃት ሀላፊነት ያላቸው አማካዮች የሜዳ ላይ የተጠጋጋ የቦታ አጠቃቀም ከተጋጣሚያቸው ድክመት አንፃር እንጂ በደካማ ጎንነት የሚነሳ ነበር።
በአንድ ጎል ልዩነት እየተመሩ ወደመልበሻ ክፍል ያመሩት ኤሌክትሪኮች በጨዋታው ባልተጠበቀ ሁኔታ ወርደው ታይተዋል። በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሃያ አምስት ደቂቃዎች የነበረው የቡድኑ ቅርፅ ግራ የሚያጋባ አይነት ነበር። በተከላካይ አማካዩ አዲስ ነጋሽ እና በፊት አጥቂው
ዲዲየ ለብሪ መሀል ባለው የሜዳው ክፍል ላይ የነበሩት ኃይሌ እሸቱ ፣ አልሀሰን ካሉሻ ፣ በሀይሉ ተሻገር እና ጥላሁን ወልዴ በቡድኑ መዋቅር ውስጥ የነበራቸው ሚና የተዘበራረቀ እና ያልተናበበ ነበር። በሂደት በተለይም አሰልጣኙ ተጨዋቾቹን ጠርተው ካናገሯቸው በኃላ ኃይሌ እና ካሉሻ ከዲዲዬ ለብሪ ጋር ከፊት መታየት ሲጀምሩ በተወሰነ መልኩ የቡድኑ መልክ እየለየ ለመምጣት ችሏል። የባለሜዳዎቹ ቁልፍ ተጨዋች አልሀሰን ካሉሻ በ12ተኛው ደቂቃ የወልዋሎው ግብ ጠባቂ በረከት አማረን ስህተት ተከትሎ ግብ የማስቆጠር ዕድልን ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ካሉሻ 15ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ ሞክሮት ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረው እና ኃይሌ እና ጥላሁን ከርቀት አርገዋቸው የነበሩት ሌሎች ሙከራዎች በኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጠቃሽ ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች የተሻለ ተነቃቅተው ጨዋታውን ጀምረዋል። ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ወደ ጎል ለመድረስ በመሞከር የአቻነቷን ግብ ፍለጋ ላይ የነበሩት ኤሌክትሪኮች 51ኛው ደቂቃ ላይ ምንያህል ይመርን በጥላውን ወልዴ ቀይረው በማስገባት ይበልጥ ጫና የመፍጠር ሀሳብ እንዳላቸው ቢያመላክቱም ከሦስት ደቂቃዎች በኃላ ግን ነገሮች ተቃያይረዋል። በዚህም 54ተኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ነጋሽ ቡድኑን ለረጅም ጊዜ በአምበልነት ሲመራ ከቆየ ተጨዋች በማይጠበቅ መልኩ ከድር ሳሊህን ከኳስ ውጪ በቡጢ በመማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል።
በዚህ ምክንያት በተፈጠረው ግርግር መሀል የወልዋሎው የቀኝ መስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን ግርማ በቀለ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት የፈፀመ ቢሆንም ከአልቢትሮቹ ዕይታ ውጪ በመሆኑ ተጨዋቹ የቀይ ካርድ ሰለባ ከመሆን ተርፏል። ከአራት ደቂቃዎች በኃላም የመሀል ተከላካዩ በረከት ተሰማ ሮቤል ግርማ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ቅጣት ምት በግንባሩ በመግጨት የወልዋሎን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። የቀድሞው የኤሌክትሪክ ሁለተኛ አምበል ግቡን በቀድሞው ክለቡ ላይ ካስቆጠረ በኃላ ደስታውን ከመግለፅ ሲቆጠብም ተስተውሏል። ከበረከት ጎል እምብዛም የማገገም ዕድል ያላገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የመሀል አማካዩ አፍወርቅ ሃይሉ 60ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ባስቆጠራት ድንቅ ግብ በሶስት ጎል ልዩነት ለመመራት ተገደዋል።
ከዚህ በኃላ በነበረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኤሌክትሪኮች በዲዲዬ ለብሪ የግል ብቃት ላይ ተመስርተው ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል ለመግባት ቢሞክሩም ለመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ ሲጋለጡ ታይቷል። በተለይ በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በዋለው ፕሪንስ ሰቨሪኒሆ በኩል ወልዋሎዎች ሲፈጥሯቸው የነበሩ ዕድሎች ቡድኑ ከዚህም በላይ በጎል እንዲንበሸበሽ የሚያስችሉ ነበሩ። 69ኛው ደቂቃ ላይ በሰከንዶች ልዩነት እንየው ካሳሁን ሁለት ጊዜ የሞከራቸው እና አንዴ በዮሀንስ ጥረት ቀጥሎም ኢላማን ባለመጠበቅ የተሳቱት ኳሶች ለዚህ ማሳያ ነበሩ። እዮብ ወ/ማርያም ተቀይሮ ገብቶ ከኤሌክትሪክ ተከላካይ መስመር ጀርባ ካገኘው ንፁህ ዕድል የሞከረውን ኳስ አሁንም ዮሀንስ በድንቅ ብቃት አውጥቶበታል። ምንም እንኳን ሶስት ግቦችን ቢያስተናግዱም የኤሌክትሪክ ተጨዋቾች በግላቸው ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ እና የነበራቸው የጨዋታ ፍላጎት መልካም ነበር። ዲዲዬ ለብሪ ሰፊ የሜዳ ክልል በመሸፈን እና ከተከላካዮች ጋር በመታገል እንዲሁም አልሀሰን ካሉሻ ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ተጠቃሽ ነበሩ። 70ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ለብሪ በግንባሩ ካደረገው ጠንካራ ሙከራ በኃላ 87ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት በፍጥነት የጀመሩት ኤሌክትሪኮች ዐወት ገ/ሚካኤል በቀኝ መስመር ለካሉሻ ባሳለፈለት እና ካሉሻ በጥሩ አጨራረስ ባስቆጠረው ግብ በባዶ ከመሸነፍ ድነዋል። በጥቅሉ አዲስ አበባ ስታድየም ትላንት ካስተናገደው እጅግ አሰልቺ ጨዋታ በኃላ በመልካም የጨዋታ ፍሰት ሙከራዎች የታዩበት ፣ ግቦች በብዛት የተቆጠሩበት እና በደጋፊዎች ድባብ የደመቀበትን የጨዋታ ቀን አሳልፏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
” አንዳንድ ጊዜ ያልተጠበቀ ነገር ይከሰታል። ዛሬ የተለየ ነው የሆነብኝ ቡድኑ። በአጠቃላይ ለኔም ግልፅ አልነበረም። ልጆቻችን ዲሲፕሊንድ አልነበሩም። አምበላችንም ራሱን ሊቆጣጠር ይገባ ነበር። እሱ ከወጣ በኃላ ደግሞ ይበልጥ አለመረጋጋት ነበር። ዳኝነቱ ምንም ችግር አልነበረውም ጥሩ ነበር። የራሳችን ችግር ነው። ጥሩ አልነበርንም። የተሻለ ዲሲፕሊንድ የነበረ ቡድን አሸንፏል። ጨዋታውን ተቆጣጥረውት ነበር ማሸነፋቸውም ይገባቸዋል። ”
አሰልጣኝ ብርሀነ ገ/እግዚአብሄር
” ዝግጅታችንን በጊዜ ባለመጀመራችን እና ከሊጉ መጀመር በፊት ጨዋታዎችን ባለማድረጋችን የመጀመሪያዎቹን ጨዋታዎች እንደመዘጋጃ ነበር የወሰድናቸው። በዚህም ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻልን መጥተን ዛሬ ከሙሉ 90 ደቂቃ ብልጫ ጋር አሸንፈናል። ማሸነፋችን ቡድኑ ውስጥ የማሸነፍ ስሜትን ከመፍጠር አንፃር በጣም ጥሩ ነው። ”
” እኔ ድሮ የኤልፓ ደጋፊ ነበርኩ። ኤልፓ ኳስ በመጫወት እንጂ በቦክስ አይታወቅም። ይሄ ቡድኑን አይወክለውም። ዳኝነቱ ግን ቆንጆ ነበር። ”
” በመሀላችን ልዩነት ነበር። እነሱ በተክለሰውነት የገዘፉ ናቸው። በዚህ ላይ የተመሰረተ ቡድን ይዘው ነበር የቀረቡት። እኛ ደሞ ኳስ መስርተን በመጫወት ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረናል። ይሄ የኔ እምነት ነው ያሉትን ስህተቶች እያረምን እንሄዳለን እንጂ አጨዋወታችንን አንቀይርም። በቀጣዩ ጨዋታም ቡናን እናሸንፋለን”