የ4ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች አዲስ አበባ እና ክልል ስታዲየሞች ላይ ቀጥለው ሲደረጉ ጎንደር ላይ ፋሲል ከተማ ወልድያን አስተናግዶ ነጥብ ተጋርቷል።
ፋሲሎች በውድድር ዘመኑ ያደረጉት 3ኛ ጨዋታ ሲሆን በደጋፊያቸው እና ከአፍ እስከ ገደፉ በሞላው ሜዳቸው ፊት ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ከክለቡ ጋር ከተለያዩ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ሜዳ የተመለሱት አሰልጣኝ ዘማርያምን “እንኳን ዘወደ ቤትህ መጣህ” የሚል ባነር በመያዝ አቀባበል አድርገውለታል።
ሁለቱም ተጋጣሚዎች መቀመጫቸው አማራ ክልል እንደመሆኑ የአማራ ደርቢ የሚል ስያሜ በተሰጠው ጨዋታ ቡድኖቹ የተሻለ ፉክክር ማድረጋቸው የታየ ሲሆን ወደ ጎል በመድረስ ረገድ አፄዎቹ በንፅፅር የተሻሉ ነበሩ።
በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ሁለቱ ቡድኖች እምብዛም ወደ ጎል በመድረስ ረገድ ጥሩ ያልነበሩ ሲሆን ባለሜዳዎቹ ፋሲሎች በ16ኛው ደቂቃ በአብዱረህማን ሙባረክ አማካኝነት የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገው የጎሉን ቋሚ ገጭቶ ኳሷ ወደ ውጭ ወጥቷል። እንግዶቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በብርሃኔ አንለይ አማካኝነት የተሻለ የግብ ማግባት እድል ያገኙ ቢሆንም የፋሲል ግብ ጠባቂ ሳማኬ ሚኬልን የፈተነ አልነበበረም። በንፅፅር ፋሲሎች በመጀመሪያው አጋማሽ በፊሊፕ ዳውዚ እና በአብዱራህማን ሙባረክ አማካኝነት ተደጋጋሚ የግብ ማግባት እድሎችን ያገኙ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያዎች ተስፋዬ አለባቸውን በጉዳት ምክንያት ከቀየሩ በኃላ ሰለሞን ገ/መድንን በማስገባት ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ ለመመለስ ያደረጉት ጥረት እምብዛም ባይሳካላቸውም በ64ኛው ደቂቃ የአሰልጣኙን አስገዳጅ ቅያሪ ፍሬያማ የሚያደርግ የግብ እድል በሰለሞን ገ/መድን አማካኝነት አግኝተው ነበር። ሰለሞን ወደ ቀድሞ ክለቡ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ መልሶበታል።
ፋሲሎች ጎል ለማግኘት ከሁለቱም የመስመር አጥቂዎቻቸው ከፍተኛ ጥረቶችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በ87 ኛው ደቂቃ ከመስመር ያሻገሩት ኳስ ብሩክ ቃልቦሬ የፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በእጁ በመንካቱ የፍጹም ቅጣት ምት በማግኘት የማታ ማታ ድል ለመጨበጥ ተቃርበው ነበር። ሆኖም በጨዋታው ድንቅ የነበረው አብዱረህማን ሙባረክ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈጽሟል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ
“በጨዋታው እኛ ጥሩ ነበርን ፤ ብዙ የግብ እድሎችን ለመፍጠርም ችለን ነበር። ነገር ግን ሳይሳካልን ቀርቷል። ጨዋታውን እንደመቆጣጠራችን እኛ ማሸነፍ ይገባን ነበር።
“ቡድኔ ዛሬ ባሳየው እንቅድቃሴ ብዙም አልተከፋሁም። ጥሩ ነገር ለማሳየት ጥረናል። ነገር ግን አንዳንድ የቅንጅት ክፍተቶች እንዳሉ ታዝቤያለው። እነዚህን ለማስተካከል ስራዎችን እንሰራለን።”
ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ወልዲያ
“የቀድሞ ክለቤን ገጥሜ በአቻ ውጤት በማጠናቀቄ ደስተኛ ነኝ።
“በጨዋታው የነበሩብንን ክፍተቶች ለማስተካከል በቀጣይ እንጥራለን። “