በ4ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሜዳው ትግራይ ስታድየም ጅማ አባ ጅፋርን የገጠመው መቐለ ከተማ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ 3 ነጥብ ማሳካት ችሏል።
በ50 ሺ በሚገመት ተመልካችና በደማቅ ህብረ ዝማሬ ታጅቦ በተካሄደው ጨዋታ የግብ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የሆኑት እንግዶቹ ጅማዎች ሲሆኑ ዮናስ ገረምው ያሻገረውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ኦኪኪ ኣፎላቢ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረውን ኳስ ኢቮና አድኖበታል።
በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች መቐለ ከተማዎች በሁለቱም መስመሮች በኩል ለጥቂዎች በሚሻሙ ረጃጅም ኳሶች ተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዝሩ የታዩ ሲሆን የጨዋታው ብቸኛ ጎል መቆጠር የቻለውም በዚህ መንገድ ነበር። 11ኛው ደቂቃ የውድድር አመቱን የመጀመርያ ጨዋታ ያደረገው አለምነህ ግርማ ከቀኝ መስመር ያሻገራትን ኳስ ያሬድ ከበደ በግንባሩ ገጭቶ መቐለን ቀዳሚ አድርጓል።
ከጎሏ መቆጠር በኋላ ጅማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድ የአቻነት ጎል ለማግኘት ቢጥሩም የመቐለን የተከላካይ መስመር መስበር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአንፃሩ በመቐለዎች በኩል በ35ኛው ደቂቃ ሚካኤል ደስታ በ2 ተጫዋቾች መሃል አሾልኮ ለያሬድ ያቀበለውን ኳስ ዳዊት ኣሰፋ የግብ ክልሉን ለቆ በመውጣት ያመከነው ኳስ ተጨማሪ ግብ ሊሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር። በ40ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ሚካኤል ያሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ያሬድ ቢያገኝውም በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወጥቶበታል።
ሁለተኛው አጋማሽ በጅማ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲጀምር በተለይም በአማካይ ክፍል የተጣመሩት አሚን ነስሩ እና ይሁን እንደሻው ያደርጉ የነበረው እንቅስቃሴ ቡድኑ በመሀል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲኖረው አስችሎታል። ሆኖም የኳስ ቁጥጥር ብልጫቸውን ያህል የፈጠሩት የግብ እድል ጥቂት ነበር። በ 60ኛው ደቂቃ ላይ ይሁን እንደሻው ያሻማውን ቅጣት ምት እንዳለ ደባልቄ ሞክሮ ለጥቂት የወጣበት እንዲሁም በ65ኛው ደቂቃ ኦኪኪ አፎላቢ ከ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጭ አክርሮ የመታውና ፍሊፕ ኢቮኖ እንደምንም ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
በ2ኛው አጋማሽ በተለይም ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ በእጃቸው የገባው መሪነት ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ኃይሉ ገ/እየሱስን በመድሀኔ ታደሰ ቀይረው በማስገባት በጥልቀት አፈግፍገው በመከላከል የተጠመዱት መቐለዎች በ50 ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር ያሻገረውና ያሬድ ተንሸራቶ ሳይደርስባት ከደረሰችው አጋጣሚ በቀር አደጋ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም በመቐለ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱ ለመቐለ ከተማ በታሪኩ የመጀመርያውን የፕሪምየር ሊግ 3 ነጥብ ሲያስገኝ ጅማ አባ ጅፋር 3ኛ ተከታታይ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ገብረመድህን ኃይሌ – ጅማ አባ ጅፋር
” ውጤቱ ለእኛ ጥሩ አድደለም። በጨዋታው ጥሩ ነበርን ፤ ነገር ግን እድለኞች አልነበርንም። ጎሉ የተቆጠረብንም በተጫዋቾቼ የትኩረት ችግር ነው። በድሬዳዋ እንዲሁም በሜዳችን በፋሲል የተሸነፍንበት ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። በቀጣይ ይህንን ችግር ፈተን እንቀርባለን።”