ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

ነገ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ከሚስተናገዱ ጨዋታዎች መሀከል አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ሀዋሳ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ከፍ ያለ ግምት አግኝቷል። ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት የሚጠበቀውን ይህን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።


ቦታ | አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም

ቀን | እሁድ ህዳር 24 2010

ሰዐት | 09፡00

ዳኞች | ዋና ዳኛ– ቴዎድሮስ ምትኩ (ፌዴራል ዳኛ)

ረዳት ዳኞች፡ ፍቅረዝጊ ተስፋዬ (ፌዴራል ዳኛ) እና  ሻረው ጌታቸው (ፌዴራል ዳኛ)


የቅርብ ጊዜ ውጤቶች (ከቅርብ ወደ ሩቅ)

አዳማ ከተማ | አቻአሸአቻተሸ

ሀዋሳ ከተማ |   አሸተሸአሸተሸ


ሁለቱ ክለቦች በተገናኙባቸው የቅርብ ጊዜያት ጨዋታዎች በውዝግቦች የተሞሉ እና በርካታ ካርዶች የሚመዘዙባቸው ጨዋታዎች መስተናገዳቸው ፉክክራቸው የደርቢ አይነት ስሜት የሚነበብበት እንዲሆን አድርጎታል። አምና በተመሳሳይ መርሀ ግብር አዳማ ላይ ተገናኝተው 2-2 በሆነ ውጤት መለያየታቸውም የነገው ጨዋታ ምናልባት በሊጉ የሚታዩትን ጎል አልባ ዘጠና ደቂቃዎች ላያሳየን እንደሚችል የሚጠቁም ነው። ከሜዳው ውጪ አንድም ነጥብ ማሳካት ያልቻለው ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን በማሳካቱ ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል። አዳማ ከተማ በበኩሉ በሊጉ መጀመሪያ በወልድያ ከደረሰበበት ሽንፈት በኃላ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻን መርታቱ እና ሁለት አቻ ውጤቶችን ማስመዝገቡ 9ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጥቶታል። በመሆኑም የነገው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ከሜዳው ውጪ አዳማ ከተማ ደግሞ በሜዳው የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ይሆናል።


በጨዋታው ምን ይጠበቃል ?

ሁለቱ ቡድኖች ጥሩ የሚባል የአማካይ ክፍል ስብስብ አላቸው። ሆኖም አጠቃቀማቸው ለየቅል ነው። አዳማ ከተማ በአንፃራዊነት ከአምናው በተሻለ ኳስ ለመመስረት የሚችል የአማካይ ክፍል ቢኖረውም በየጨዋታው በሚኖሩ ለውጦች እና ሽግሽጎች ቡድኑ ከስብስቡ ማግኘት የሚገባውን ያህል ጥቅም እንዳያገኝ አርጎታል። በተለይ ቡድኑ በአንድ አጥቂ በሚጫወትበት ወቅት የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹ በጨዋታው የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ የበላይ ለመሆን ባይቸገሩም ከፊት አጥቂው ጋር ያላቸው ግንኙነት ውጤታማ አይደለም። በብቸኛ አጥቂነት ተስለፍው የታዩት እንደነ ሙጂብ ቃሲም እና ሚካኤል ጆርጅም ያሉ ተጨዋቾች የሚያደርጉት እንቅስቃሴም ከበስተኃላቸው ለሚሰለፉ ፈጣሪ አማካዮች ክፍተት የሚፈጥር አልነበረም። ይህም በመሆኑ የመሀል ክፍላቸው እጅግ ከተዳከሙት ከእንደነ መከላከያ አይነት ቡድኖች ጋር እንኳን ተጫውቶ በርካታ የግብ ዕድል ሲፈጥር አይታይም። ቡድኑ አጥቂዎቹ በሙሉ ጤንነት ላይ ሲሆኑ እና ሶስት አጥቂዎችን ሲጠቀም ደግሞ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹ በቁጥር ሲያንሱ የቀደመውን የመሀል ሜዳ የበላይነት ለማግኘት ይቸገራል። ነገር ግን የቡድኑ አጥቂዎች ለጨዋታ ብቁ ከሆኑ አዳማ በሶስት አጥቂዎች የመጫወቱ ነገር እርግጥ ይመስላል።

ሀዋሳ ከተማም በተመሳሳይ በውድድር አመቱ ሦስት እንዲሁም አምስት የአማካይ መስመር ተሰላፊዎችን ሲጠቀም ተስተውሏል።  ቡድኑ በሊጉ ካሉ ቡድኖች የተሻለ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አቅም ያለው እና እንደ ታፈሰ ሰለሞን አይነት የመጨረሻ ኳሶችን የማቅረብ አቅም ያላቸው ተጨዋቾችን የያዘ ነው። ይህም በመሆኑ ከፊት ሦስት አጥቂዎችንም ሲጠቀም መስመር ላይ የሚኖሩት አጥቂዎቹን የአማካይ ክፍል ተሳትፎ ከፍ በማድረግ በተጋጣሚ ላይ የበላይነት ለመውሰድ ይሞክራል። ሆኖም የዳዊት ፍቃዱ የአጥቂ በሀሪ መላበስ ቡድኑ በግራው የአማካይ ክፍሉ ላይ ፍሬው ሰለሞን እንደሚሰለፍበት የቀኝ ክፍል በቂ እገዛ አያገኝም። የፍሬው ሰለሞን በአዳማው ጨዋታ አለመኖር የሀዋሳን የቀኝ መስመር ማጥቃትም የሚያሳሳው ቢሆንም አዳማ ከተማም ከንአን ማርክነህን የማያሳልፍ መሆኑ በሱራፌል ዳኛቸው ብቃት ላይ የተመሰረተ የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲኖረው ያደርጋል።

በጨዋታው ወሳኝ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ የሜዳ ክፍሎች መሀልም የአዳማው የተከላካይ አማካይ ኢስማኤል ሳንጋሪ ከታፈሰ ሰለሞን ጋር እንዲሁም በተቃራኒው ጂብሪል አህመድ ከሱራፌል ዳኛቸው ጋር የሚገናኙበት ቦታዎ ተጠቃሽ ናቸው። የዳዊት ፍቃዱ ከግራ መስመር የሚነሳ ማጥቃትም የአዳማን የቀኝ መስመር የመከላከል ክፍል እንደሚፈትን ይጠበቃል። በሀዋሳ በኩል በፊት አጥቂነት የሚሰለፈው ያቡን ዊልያም ከሙጂብ ቃሲም እና ተስፋዬ በቀለ ጥምረት ጋር የሚፋለምበትም እንቅስቃሴ ተጠባቂ ይሆናል።


የቡድን ዜናዎች

ወሳኙን አማካይ ከንአን ማርክነህን እና ዳዋ ሁቴሳን ለቤሔራዊ ቡድን ያስመረጠው አዳማ ከተማ ደሳለኝ ደባሽን ፣ በልቻ ሹራን እና ታፈሰ ተስፋዬን በጉዳት ምክንያት የማይጠቀም ይሆናል። ሀዋሳ ከተማም ፍሬው ሰለሞንን እና ግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆን በቤሔራዊ ቡድን ምርጫ እንዲሁም ዳንኤል ደርቤ በጉዳት ምክንያት በቡድን ስብስብ ውስጥ አያካትትም።


ምን ተባለ ?

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ- ሀዋሳ ከተማ

” አርብ ዕለት ነበር ወደ አዳማ የመጣነው። ግጅታችንን አጠናቀን የጨዋታውን መጀመር እየጠበቅን እንገኛለን። በቂ ዝግጅትም አድርገናል።  ከሜዳችን ውጪ ያለን ሪከርድ ጥሩ ባይሆንም ከጨዋታው ሙሉ ነጥብ ለማገኘት አስበናል። ጅማ ላይ በጭማሪ ደቂቃ ነበር ጎል ያስተናገድነው። የደደቢቱ ጨዋታ ላይም በተከላካይ ክፍላችን ላይ ክፍተት ነበረብን ። ያንን ማስተካከል ያለብን የመስለኛል። በጠቃላይ አጥቅተን በመጫወታችን ከኃላ ሚፈጠሩ ክፍተቶች ሲኖሩ በተለይ ከሜዳ ውጪ ተጋጣሚ ከተጠቀመባቸው መልሶ ለማገገም ይከብዳል።  ስለዚህ ከኃላ ያለብን ክፍተት ላይ ማስተካከያ አድርገን በጥንቃቄ እንጫወታለን። ፍሬው ጥሩ ተጨዋች በመሆኑ የሱ አለመኖር ሌላ ራስ ምታት ነው። ሆኖም ባሉን ልጆች ክፈተቱን ሸፍነን የተሻለ ለመጫወት እንሞክራለን ። ”

አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ- አዳማ ከተማ

“ማንኛውም ክለብ እንደሚዘጋጀው ተዘጋጅተናል። አንድ ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን እንደሚዘጋጀው ተዘጋጅተናል። ወደፊት ግብ የሚያስቆጥሩ ተጨዋቾችን እንፈጥራለን”


ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጃኮ ፔንዜ

ምኞት ደበበ –  ተስፋዬ በቀለ –  ሙጂብ ቃሲም – ሱሌይማን መሐመድ

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ – ሱራፌል ዳኛቸው

በረከት ደስታ – አላዛር ፋሲካ – ሚካኤል ጆርጅ


ሀዋሳ ከተማ  (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

አዲስአለም ተስፋዬ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሀንስ

ሙሉአለም ረጋሳ – ጂብሪል አህመድ – ታፈሰ ተስፋዬ

ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን – ያቡን ዊልያም– ዳዊት ፍቃዱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *