በኬንያ አስተናጋጅነት በሶስት ከተሞች ለሁለት ሳምንታት የሚካሄደው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ዛሬ በካካሜጋ አስተናጋጇ ኬንያ እና ሩዋንዳ በሚካሄዱት ጨዋታ ይጀምራል፡፡ ኬንያ በአዲስ አሰልጣኝ ፖል ፑት እየተመራች ለሴካፋው የምትቀርብ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በካካሜጋ ሐሙስ ጠዋት ያመራ ሲሆን ማክሰኞ ከደቡብ ሱዳን ጋር ጨዋታው በማድረግ ይጀምራል፡፡
ዛሬ በካካሜጋ እና ማቻኮስ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሴካፋው ሲጀምር በምድብ አንድ 8፡00 ሰዓት ላይ ኬንያ ከሩዋንዳ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ ማቻኮስ ላይ ተጋባዧ ሊቢያ ከታንዛኒያ ይፋለማሉ፡፡ ሩዋንዳ ውድድሩን ለአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና መዘጋጃ እንደምትጠቀምበት ሲታወቅ በምድቡ ጠንካራ ቡድኖች መኖራቸው ደግሞ ለአሰልጣኝ አንቶይን ሄይ ይበልጥ ቡድናቸውን እንዲፈትሹ ያስችላቸዋል፡፡ ቤልጄሚያዊው ፑት የሃራምቤ ከዋክብቶቹ አሰልጣኝ ከሆኑ በኃላ ቡድናቸውን የሚመሩበት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ይሆናል፡፡ ከዚህ ምድብ ዛንዚባር የመጀመሪያው ጨዋታ አራፊ ትሆናለች፡፡
የውድድሩ አዘጋጆች የዚምባቡዌ ከውድድሩ መሰናበት ተከትሎ የፕሮግራም ለውጥ አድርገዋል፡፡ ይህንን ተክተሎም ሰኞ 8፡00 ላይ ኢትዮጵያ ከቡሩንዲ የሚያደርጉት ጨዋታ ቀርቶ ቡሩንዲ ዩጋንዳን ትገጥማለች፡፡ ዋሊያዎቹ ደቡብ ሱዳንን በምግጠም የሴካፋ ውድድራቸውን ይጀምራሉ፡፡ ጨዋታው በካካሜዳ በሚገኘው ቡኩንጉ ስታዲየም ይደረጋል፡፡
በተያያዘ ሴካፋ ቅዳሜ እለት በናይሮቢ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ሱዳናዊው የምክር ቤቱ ፕሬዝደንት ሙታሲም ጋፋር በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ አምስት አባላትንም ወደ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አካቷል፡፡
የዛሬ ጨዋታዎች
ኬንያ ከ ሩዋንዳ (8፡00)
ሊቢያ ከ ታንዛኒያ (10፡00)
ሰኞ
ዩጋንዳ ከ ቡሩንዲ (9፡00)
ማክሰኞ
ዛንዚባር ከ ሩዋንዳ (8፡00)
ኬንያ ከ ሊቢያ (10፡00)
ኢትዮጵያ ከ ደቡብ ሱዳን (9፡00)
የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ በሶከር ኢትዮጵያ እንዲቀርብ ያስቻለው ጎ ቴዲ ስፖርት ነው፡፡ ጎ ቴዲ ስፖርት በኢትዮጵያ የማራቶን ትጥቆች ወኪል አከፋፋይ!!