በ5ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሊጉ አናት ላይ የገኙ የነበሩ ክለቦችን ያገናኘው ጨዋታ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ2ኛው አጋማሽ ሙሉአለም ጥላሁን ባስቆጠረው ጎል በሜዳው የመጀመርያው 3 ነጥብ ማግኝት ችሏል፡፡
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ሁለቱ ክለቦች ስጦታ የተለዋወጡ ሲሆን ወልዋሎዎች በአዲግራት ተወዳጅ የሆነውን ጥህሎ መመገቢያ መሶብ ቅርፅ ፣ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ የሁለቱ ቡድኖች ፎቶ ያለበት ፎቶግራፍ ተለዋውጠዋል፡፡
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት በረከት አማረን በዘውዱ መስፍን ተክቶ ከመግባቱ ውጪ ባለፈው ሳምንት ኤሌክትሪክን ከሜዳው ውጪ ካሸነፈው ስብስብ ለውጥ ሳይደረግበት ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ ካለ ዋና አሰልጣኙ ኮስታዲን ፓፒች ወደ አዲግራት የተጓዘው ኢትዮጵያ ቡናም በተሳሳይ አርባምንጭን ካሸነፈበት ስብስብ መካከል ወደ ሴካፋ ባመራው ሳምሶን ጥላሁን ምትክ እያሱ ታምሩን በመተካት ነበር ወደ ጨዋታው የገባው፡፡
ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ወልዋሎዎች በሁለቱም የመስመር አጥቂዎች በተለይ ደግሞ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ በመጠቀም የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመርን መፈተን ችለዋል፡፡ በ 12ኛው ደቂቃ ሙሉኣለም ከግራ መስመር በኩል የሰጠውን ኳስ ፕሪንስ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ የመታው እና ሃሪሰን ወደ ውጪ ያወጣበት ኳስም የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር፡፡ በ20 ደቂቃ ደግሞ ከመሃል ሜዳ አጋማሽ ሙሉአለም ጥላሁን ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ከድር ሳልህ ያሻገረለትን ኳስ ከድር ሀሪሰንን በማለፍ ወደ ግብ ቢመታውም አስራት ቱንጆ በማይታመን መልኩ በግንባሩ የመለሰው ኳስ ለወልዋሎዎች ሌላ የሚያስቆጭ ኣጋጣሚ ነበር፡፡
ደቂቃዎች እየገፉ በሄደ ቁጥር የጨዋታው እንቅስቃሴ ላይ መቀዛቀዝ ቢታይም የወልዋሎው አጥቂ ሙሉአለም መስፍን በግሉ በሚያረገው እንቅስቃሴ የቡናን የተከላካይ መስመር መረበሽ ችሏል:: በአንፃሩ በመጀመርያ አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ 35 ደቂቃዎች ጠብቀዋል፡፡ ሳሙኤል ሳኑሚ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ ውጭ አክርሮ ሞክሮ ወደ ላይ ከወጣበት ሙከራ ውጪም ሌላ የሚጠቀስ የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሴኮንዶች ሲቀሩ ወልዋሎዎች በመሪነት ወደ እረፍት የሚያመሩበትን እድል ቢያገኙም ፕሪንስ ከሃሪሰን 1 ለ 1 ተገናኝቶ በግብ ጠባቂው ልዩ ብቃት መክናለች፡፡
ከመጀመርያው አጋማሽ ያነሰ የጎል ሙከራ ባስተናገደው በዚህ የቸዋታ ክፍለ ጊዜ ቡናዎች ከመጀመርያው በተሻለ መልኩ ጠንክረው የቀረቡ ሲሆን በወልዋሎ ሁለቱም መስመሮች በኩል ይመጡ የነበሩትን እንቅስቃሴዎች በመግታት ወደ ጨዋታው መመለስ ችለዋል፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ አክሊሉ በግንባሩ ገጭቶ ዘውዱ መስፍን በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ሙከራ እንግዶቹን መሪ ልታደርግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች፡፡
ጨዋታው በሁለቱም በኩል በሚሰነዘር ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ከድር ሳላህ በግራ መስመር በኩል ይዞ በመግባት ያሻገረውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ሙሉአለም መስፍን ጨርፎ በቀድሞ ክለቡ መረብ ላይ በማሳረፍ ወልዋሎን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡
ከጎሉ መቆጠር በኋላ የቀሩትን 15 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡና ጫና ፈጥሮ ቢጫወትም ቢጫ ለባሾቹ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ሰአት በማባከን እና የተከላካይ ቁጥር ጨምረው በማፈግፈግ ውጤታቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው መጨረሻ የተጨመረው 4 ደቂቃ ከባከነው አንፃር ጥቂት ነበር በሚል ቅሬታቸውን በእለቱ ዳኛ ላይ አሰምተዋል፡፡
ጨዋታው በወልዋሎ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎም አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ከ5 ጨዋታዎች 9 ነጥቦችን በመሰብሰብ የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሲቀመጥ በሜዳው የመጀመርያ 3 ነጥቡንም አሳክቷል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በአመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በክልል ሜዳ ባደረገው ጨዋታ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡
ብርሀኔ ገብረግዚአብሔር – የወልዋሎ አሰልጣኝ
” ጨዋታው ጥሩ ነበር። ጨዋታውን ተቆጣጥረነው ነበር። በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ ብዙ የጎል አጋጣሚዎች መፍጠር ችለን መጠቀም አልቻልንም። ውጤቱ ይገባናል። በዚህ ከቀጠልን ቻምፒየንነት የማንጫወትበት ምክንያት የለም። ”
ሐብተወልድ ደስታ – የቡና ም/አሰልጣኝ
” ጨዋታው ጥሩ ነበር። እኛ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በተቻለ መጠን ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረን ነበር። እነሱ ግን በአንፃሩ ጨዋታውን ለመጫወት የነበራቸው ፍላጎት አነስተኛ ነበር:: በዚ ጨዋታ የነበሩንን ክፍተቶች አርመን ለቀጣይ ጨዋታ እንቀርባለን። ”