በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ደደቢት እና ፋሲል ከተማ በአዲስ አበባ ስታድየም ተገናኝተው ያለግብ ጨዋታቸውን ጨርሰዋል።
ከሳምንቱ የአማራ ደርቢ ቋሚ ተሳላፊዎቻቸው ውስጥ ራምኬል ሎክ እና ፍፁም ከበደን ለቤሔራዊ ቡድን ባስመረጧቸው አብዱርሀማን ሙባረክ እና አምሳሉ ጥላሁን ተክተው ወደሜዳ የገቡት ፋሲሎች ለ4-2-1-3 የቀረበ አሰላለፍ ተጠቅመዋል። ደደቢቶችም በ4-4-2 ቅርፅ ወደ ሴካፋ ባቀናው አቤል ያለው ፋንታ አኩዌር ቻሞን ፊት ላይ ከጌታነህ ጋር አጣምረዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የግብ ዕድሎች በብዛት ሲፈጠሩ አልታዩም። የተሻለ ተንቀሳቅሰው የነበሩት ፋሲሎች በቀኝ መስመራቸው በኩል ከፈጠሩት ጫና ያገኙትን የቅጣት ምት 36ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ሎክ አሻምቶ ይስሀቅ መኩሪያ በግንባሩ ሲሞክር በቀኙ ቋሚ በኩል የወጣው ኳስ የሚጠቀስ ቢሆንም ሌላ ጥርት ያለ የግብ ዕድል ግን መታየት አልቻለም። በሰዒድ ሁሴን እና ራምኬል ሎክ ቅንጅት የቀኝ መስመራቸውን እንደዋነኛ የጥቃት አማራጭ ሲጠቀሙ የነበሩት ፋሲሎች ወደ ተጋጣሚያቸው ሜዳ ይዘዋቸው የሚገቡት ኳሶች ከሌሎች የማጥቃት ባህሪ ካላቸው ተጨዋቾች ጋር ሲደርሱ ባልተሳኩ ቅብብሎች ምክንያት እንደታሰበው አደጋን መፍጠር ሲያቅታቸው ታይቷል። በተመሳሳይ እንደተለመደው ደካማ የማጥቃት ተሳትፎ በነበራቸው የደደቢት የመስመር ተከላካዮች እንቅስቃሴ ምክንያት የደደቢት ዋነኛ የማጥቃት አማራጮች የሆኑት ሽመክት እና ኤፍሬም ወደኋላ መሳብ የፊት አጥቂዎቹ ጌታነህን እና አኩዌርን ከቡድኑ ነጥሏቸው ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪም የአስራት መገርሳ ለተከላካዮች ቀርቦ መጫወት ደደቢት የመሀል ሜዳ የበላይነት እንዲወሰድበት ምክንያት ሆኗል።
ሁለተኛው አጋማሽ በሙከራ ረገድ የተሻለ ነበር። በመጀመሪያዎቹ የሁለተኛ አጋማሽ ደቂቃዎች ኤፍሬም አለሙ እና ሰይድ ሁሴን በፋሲል ከተማ በኩል ከረጅም ርቀት ያረጓቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። 51ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ ሰለሞን ሀብቴም በተመሳሳይ ከርቀት አክርሮ ሲመታ ሚኬሌ ሳማኬ ተፎቶ በድጋሜ ያዳነበት አጋጣሚም በደደቢት በኩል ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር። ደደቢቶች ያብስራ ተስፋዬን እና አቤል እንዳለን ቀይረው ባስገቡባቸው የመጨረሻዎቹ 25 ደቂቃዎች የአማካይ ክፍል ቁጥራቸውን በማበራከት የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን ለማግኘት ጥረዋል። 64ተኛው ደቂቃ ላይ ከያብስራ በተነሳ ኳስ በቁጥር በርክተው የፋሲል ሳጥን ውስጥ የገቡት የደደቢት ተጨዋቾች የተሻለ ዕድል ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ቡድኑ ከጌታነህ ከበደ የ82ኛ እና 89ኛ ደቂቃ ሙከራዎች በተጨማሪም በሽመክት አማካይነት 70ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ዕድል ቢፈጥርም ግብ ማስቆጠር ግን አልተቻለውም።
ፋሲል ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ሲያገኙ ተስተውለዋል። ደደቢት ራሱን ወደ መከላከል ቅርፅ ከመቀየሩ በፊት በተደጋጋሚ እስከ ሳጥኑ ድረስ ይደርሱ የነበሩት አፄዎቹ ያገኟቸውን ክፍተቶች በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም። 61ኛው ደቂቃ ላይ ኤርሚያስ በቀኝ መስመር ሰብሮ ገብቶ ሲሞክር በክሌመንት የተመለሰበት እና ወደ ላይ የተነሳችው የራምኬል 88ኛ ደቂቃ የርቀት ቅጣት ምት ቡድኑን ከሜዳ ውጪ ሶስት ነጥብ ለማስገኘት የተቃረቡ ነበሩ። ነገር ግን ወደ መጨረሻ ሙከራነት አይቀየሩ እንጂ ፋሲሎች ወደ ማጥቃት ያደርጉ የነበረው ፈጣን ሽግግር ይበልጥ አስፈሪ አድርጓቸው አምሽቷል። በዚህ መልኩ ሁለተኛውም አጋማሽ በፉክክር ረገድ ከመጀመሪያው የተሻለ ሆኖ ጎል ግን ሳያስተናግድ ጨዋታው ተጠናቋል።