​ሪፖርት | አዳማ ላይ የተደረገው የጅማ አባ ጅፋር እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ቅዳሜ ጅማ ላይ ሊደረግ የታሰበው የጅማ አባ ጅፋር እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ አባ ጅፋር ላይ በተላለፈው ቅጣት ምክንያት ዛሬ አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ ተካሂዶ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በጅማ አባ ጅፋር በኩል በሴካፋ ብሔራዊ ቡድን የተካተተው ኄኖክ አዱኛን በመተካት ቢንያም ሲራጅ በመጀመርያ አሰላለፍ ሲካተት በአጥቂ መስመር ላይ ፍራኦል መንግስቱ እና ተመስገን ገብረኪዳንም በሳምሶን እና እንዳለ ምትክ የመጀመርያ ተሰላፊ ሆነው ገብተዋል። በሲዳማ በኩል ደግሞ ሐብታሙ ገዛኸኝ እና ወንድሜነህ አይናለም ወደ ሴካፋ ያመራው አዲስ ግደይ እና አማካዩ አምሀ በለጠን ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

የጅማ አባጅፋሮች የተሻለ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ ጅማዎች በኳስ ቁጥጥር የበላይ በመሆን ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ ሲዳማዎች ለወትሮ ከሜዳ ውጪ በሚከተሉት አቀራረብ በራሳቸው የሜዳ ክፍል በመገደብና በመልሶ ማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል። ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ በሚደረጉ ሙከራዎች በታጀበው የመጀመርያ አጋማሽ በ19ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ሐብታሙ ገዛኸኝ ከግራ መስመር አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ያደነበት ሙከራ የመጀመርያው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

በጅማ አባጅፋር በኩል 23ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ ከርቀት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርግ በ32ኛው ደቂቃ ይሁን እንደሻው ከዩናስ ገረመው ጋር አንድ ሁለት በመቀባበል ወደ ግብ የመታት ኳስ በግብ ጠባቂው መሣይ ድኖበታል። በ39ኛው ደቂቃ ላይ አሚን ነስሩ በግሩም ሁኔታ ሁለት ተጫዋቹችን አልፎ ለኦኪኪ አፎላቢ የሰጠውን ኳስ ኦኪኪ በግቡ በስቀኝ በኩል ሲሰደው በ43 ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው ከርቀት የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። በ45ኛው ደቂቃ ኦኪኪ አፎላቢ የመሣይን መውጣት ተመልክቶ የመታው ኳስ የግቡን አናት ጨርፋ የወጣችበት ሙከራም ጎል ሊሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር።
እምብዛም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ያልቻሉት ሲዳማዎች ከርቀት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በ25ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ወደ ግብ አክርሮ ሲመታ ኤልያስ አታሮ ተደርቦ ያወጣበት ፣ በ30ኛው ደቂቃ አብዱልለጢፍ መሀመድ ከርቀት የመታውና በግቡ አናት የወጣችበት ሙከራ በሲዳማ በኩል ተጠቃሽ የመጀመሪያ አጋማሽ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡና ረጅም ደቂቃዎችን በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደደበት ክፍለ ጊዜ ነበር። በ53ኛው ደቂቃ ላይ ጅማ አባ ጅፋሮች ያገኙት የማዕዘን ምት ሲሻማ በነበረ ፍትጊያ የወደቀው አዳማ ሲሶኮን የሲዳማው ግብ ጠባቂ አዳማ ሲሶኮ በወደቀበት ተጠግቶ በቡጢ በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

የቀይ ካርዱን የሰጣቸው የቁጥር ብልጫን ተከትሎ ጅማዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆን በተለይ ኦኪኪ በ74ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ወደ ሊመታው ሲል ፍፁም ተፋሪ ደርሶ ያዳነበት ፣ በ76ኛው ደቂቃ ተመስገን ገ/ኪዳን ከኦኪኪ የታሻገረለትን ኳስ ሞክሮ የግቡን አግዳሚ መትቶ የወጣበት እንዲሁም በ86ኛው ደቂቃ ላይ ከማሀል ሜዳ በረጅሙ የተላከውን ኳስ ሳምሶን ቆልቻ በግንባሩ ገጭቶ ፍቅሩ ወዴሣ ያደነበት ሙከራ ጅማን ሶስት ነጥብ ለማስገኘት የተቃረቡ የጎል ሙከራዎች ነበሩ።

ከቀይ ካርዱ በኋላ መከላከል ይበልጥ በማዘንበል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሲዳማዎች አልፎ አልፎ ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። ባዬ ገዛኸኝ በ67ኛው ደቂቃ እንዲሁም በ78ኛው እና 80ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ ባልቻ ከርቀት አክርረው የመቷቸው ኳሶች በግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ተመልሶባቸዋል።

ጨዋታው ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎ ሀለቱም ቡድኖች በ4 ነጥቦች 13 እና 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

አስተያየቶች 

አለማየሁ አባይነህ – የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ

” በመጀመሪያው አጋማሽ ሶስት ጥሩ ሙከራዎች ብንሞክርም የዕለቱ ግብ ጠባቂ አድኖብናል። ከዕረፍት መልስ ለማጥቃት አስበን የገባን ቢሆንም የግብ ጠባቂያችን ስህተት ያሰብነውን ሳንተገብር እንድንወጣ አስግድዶናል። ነገር ግን ቶሎ ቶሎ ኳስ ወደ ፊት በመጣል ለማጥቃት ሞክረናል፡፡

” በኔ ቡድን ውስጥ እንደዚህ ኣይነት ባህሪ አጋጥሙኝ አያውቅም። ግብ ጠባቂው ቅጣት ይጠብቀዋል።  ስሜታዊ መሆን የለበትም። የተማፀመታ ተጫዋች መማታት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ”

ገ/መድህን ኃይሌ – የጅማ አባ ጅፋር አሰልጣኝ

” ጨዋታውን ተቆጣጥረነን መጫወት ብንችልም ከኃላ የመጣ ጫና አለ። የዛሬ ጨዋታ ላይ እሱ ነው የተንፀባረቀው፡፡ የተገኘውን አጋጣሚ መጠቀም አልቻሉም። በቀጣይ ውጤቱን ለመለወጥ እንጥራለን። አንድ ነጥብ በራሱ ጥሩ  ነው፡፡

” ተመስገንን ያስገባነው የጎል ዕድል መፍጠር የተሻለ ስለነበር ነገር። ግን ኦኪኪ አፎላቢ ከጨዋታ ጨዋታ ያገኘውን ኳስ አለመጠቀም ተይቶበታል። በቀጣይ ይህን ለመቅረፍ የምንሰራበት ነው የሚሆነው፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *