ትላንት በተካሄዱ ሁለት የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ለፍፃሜ አልፈዋል፡፡ ሰማያዊው ጦርም ለ2015 የአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ማለፉን ከወዲሁ አረጋግጧል፡፡
9፡00 ላይ ደደቢት ከ መከላከያ ያደረጉትን ፍልሚያ ደደቢት 2-0 አሸንፎ ወደ ፍጻሜው ተሸጋግሯል፡፡ ጨዋታው ኃይል የተቀላቀለበት እና በውዝግቦች የታጀበ ሲሆን የመጀመርያዋ ግብ የተቆጠረችው በ37ኛው ደቂቃ በታደለ መንገሻ አማካኝነት ነው፡፡
ከግቧ መቆጠር በኋላ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱ ቡድኖች ከፍፁም ቅጣት ምት እና ካርዶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ውዝግቦች ውስጥ የገቡ ሲሆን ግብ ጠባቂው ሲሳይ ባንጫ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል፡፡ በተመሳሳይ አማካዩ ሻይቡ ጂብሪልም ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የደደቢቱ ተከላካይ አክሊሉ አየነው በሁለት ቢጫ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን አብዛኛውን 2ኛ አጋማሽ በጎዶሎ ልጅ ለመጫወት ተገደዋል፡፡
የመጨረሻዎቹን 30 ደቂቃዎች በጥልቀት አፈግፍገው ሲከላከሉ የነበሩት ደደቢቶች በመልሶ ማጥቃት በዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን በ2-0 አሸናፊነት አጠናቀዋል፡፡ በዚህም ቅዳሜ ሰኔ 28 ለሚካሄደው የፍፃሜ ፍልሚያ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን የፍፃሜ ተፋላሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን በማረጋገጡ ደደቢት የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳትፎን አረጋግጧል፡፡
11፡30 በተደረገው የሙገር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍልሚያ የፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮኖቹ በፍፁም ቅጣት ምት አሸንፈው ወደ ፍፃሜው ተሸጋግረዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፊል ቋሚ ተሰላፊዎቹን ሳያሰልፍ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን አሉላ ግርማ በአማካይ ስፍራ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ጨዋታው እምብዛም ትኩረት ሳቢ ያልነበረ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በኡመድ ኡኩሪ በጠንካራ ምቶች ተደጋጋሚ ሙከራዎች ከማድረጉ ውጪ በሙከራዎች ሳይታጀብ ጨዋታው 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
አሸናፊዎቹን ለመለየት ከ30 ደቂቃ ጭማሪ ይልቅ በቀጥታ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት የተሸጋገሩ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-3 አሸንፎ ወደ ፍፃሜው ማለፉን አረጋግጧል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አበባው ቡታቆ ከሙገር በኩል ደግሞ አዲሱ አላሮ እና ጌድዮን አካፖ ፍፁም ቅጣምቶችን ያመከኑ ሲሆን በሃይሉ አሰፋ የመጨረሻዋን ፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ፍፃሜ መርቷል፡፡
የኢትዮጰያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2006 አም. በአዲስ አበባ ስታድየም በደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ይካሄዳል፡፡