ታህሳስ 16 በአፋር ሰመራ እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት እየተጠበቀ የሚገኘው የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚዎች ምርጫን በሚያስፈፅመው አስመራጭ ኮሚቴ አባላት መካከል ያሉ ልዩነቶች እየሰፉ መጥተዋል፡፡
በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው የተሰየመው የአስመራጭ ኮሚቴ አመራረጥ ከጅምሩ በጥርጣሬ ሲታይ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ አሁን የኮሚቴው አባላትን ጎራ የለዩ ልዩነቶች እየሰፉ የመጡ ሲሆን በአስመራጭ ኮሚቴው ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አባላት ምርጫው ተአማኒ በሆነ መንገድ እየሄደ አይደለም በሚል በቀጥታ ለፊፋ ደብዳቤ ለመላክ መዘጋጀታቸው ታውቋል። እንደ ምክንያት የሚያቀርቡትም በኮሚቴው ውስጥ የተካተቱት አቶ መኮንን ደስታ ከዛሬ አራት አመት በፊት አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩ ሆነው ሳለ አሁን በድጋሚ መመረጣቸው የፊፋን ህግ ይጣረሳል የሚል ነው፡፡
የሀገሪቱ የማህበራት ማደራጃ ደንብን በጣሰ መልኩ አንድ በሌላ የስፖርት ማህበር አመራር ውስጥ ላይ ያሉ ሰው ለፕሬዝዳንት እጩ ሆነው መቅረባቸውን ተገቢ አይደለም በሚልም የኦሮሚያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ለፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩ ከሆነ በምርጫው ላይ እንደማይሳተፍ አቋም መያዙ የተነገረ ሲሆን ሌሎች ክልሎችም ሀሳቡን እንዲጋሩ የፊርማ ማሰባሰብ መጀመሩ ተሰምቷል።
ከላይ የቀረቡት ቅሬታዎች ዛሬ ምሽት የአስመራጭ ኮሚቴው ቅረታ ሰሚ በሚያካሂደው ስብሰባ እንደሚታዩ ሲጠበቅ በስብሰባው ላይ ቅሬታውን ተቀብሎ ትክክለኛ ውሳኔ የማይሰጥ እንደሆነ ጥርጣሬ ውስጥ የገቡት አንድ የኮሚቴው አባል ወደ ፊፋ ሊያመረ እንደተዘጋጁ ሰምተናል።
ድራማዊ ክስተት እያስተናገደ የሚገኘው የምርጫው ሂደት እንዲህ ያሉ አወዛጋቢ ጉዳዮች እየታዩበት የሚሄዱ ከሆነ የፊፋ ጣልቃ ገብነት በድጋሚ የሚከሰትበት መሆኑ የማይቀር ከመሆኑ በተጨማሪ ምርጫው በታሰበለት ጊዜ የመካሄድን ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡