በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ወልዲያን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት በመለያየት ድል አልባ የውድድር ዘመኑን ገፍቶበታል።
እምብዛም ማራኪ እንቅስቃሴ እና ፉክክር ባልታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የተሻለ የእንቅስቃሴ የበላይነት የነበራቸው ወልድያዎች በጎል ሙከራ ረገድም የተሻሉ ነበሩ። 10ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ገብረመድህን የሰጠውና ፍፁም ገ/ማርያም ሳይጠቀምበት የቀረበት ፣ 26ኛው ደቂቃ ላይ ኤደም ኮድዞ ከፍፁም የተሻገረለትን ኳስ በቀጥታ መትቶ ፍቅሩ ወዴሳ እንደምንም ተወርውሮ ያወጣበት እንዲሁም ሰለሞን ገ/መድህን ተጫዋቾችን አታሎ ወደ ግብ የሞከራትና የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት ሙከራዎች ወልዲያን ቀዳሚ ሊያደርጉ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።
በሲዳማ በኩል 20ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ አይናለም በረጅም ያሻገረውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ በግል ጥረቱ አልፎ ወደ ሳጥን በመግባት የመታት ኳስ ኢላማውን ሳጠብቅ ወደ ውጭ የወጣችበት እና 43ኛው ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ መሀመድ በረጅሙ ከግራ መስመር ያሻገራትን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ሞክሮ ቢሌንጌ ሲመልስበት ሀብታሙ ገዛኸኝ አግኝቷት ወደ ላይ የሰደዳት ሙከራ የሚጠቀሱ ነበሩ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት አብዱለጢፍ መሀመድ በረጅሙ ያሻማትን ኳስ ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ሚካኤል አናን በግንባሩ ገጭቶ ሲዳማ ቡናን መሪ በማድረግ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ተሽለው ቢቀርቡም በቀጣዩቹ 20 ደቂቃዎች አድራሻ ከሌላቸው ተሻጋሪ ኳሶች ውጪ የጠራ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም። ይልቁንም በ63ኛው ደቂቃ ላይ ፍፀም ገ/ማርያም ወደ ግብ ሲመታት ዮናታን ፍሰሀ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ኤደም ኮድዞ በአግባቡ በመጠቀም ወልዲያን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከአቻነት ጎሉ በኋላ ሲዳማዎች በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም በድጋሚ መሪ የሚያደርጋቸውን ጎል ማግኘት አልቻሉም። 80ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች ባዬ ገዛኸኝ የእለቱ ዳኛ ዳዊት አሳምነው የሰጡትን ውሳኔ በመቃወም ባሳየው ያልተገባ ባህሪ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጫወት ቢገደዱም አሸንፈው ለመውጣት ጫና መፍጠር ችለዋል። በተለይ በ85ኛ ደቂቃ አምሀ በለጠ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ወንድሜነህ አይናለም ሞክሮ ኤሚክሪል ቢሌንጌ በአስደናቂ ሁኔታ ያወጣበት ኳስ ባለሜዳዎቹን የማታ ማታ ሶስት ነጥቦች ልታስገኝ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።
ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በውድድር አመቱ እስካሁን ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ያልቻለው ሲዳማ ቡና በ5 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወልዲያ በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና
“በዛሬው ጨዋታ ጥሩ አልነበርንም። በቅጣት እና በጉዳት። እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ወሳኝ ተጫዋቾቻችንን አጥተናል። በመጀመሪያ አጋማሽ በተጫዋቾቼ ድክመት ተበልጠናል። ይህም የሆነበት ተጫዋቾች በቦታቸው አልነበረም አብዛኛዎቹ የተጫወቱት። በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ላይ ግን የታክቲክ ለውጥ አድርገን ተጭነን ተጫውተናል። በሁለተኛው አጋማሽ የተሻልን ነበርን የባዬ መውጣት ግን የነበረንን ነገር አሳጥቶናል። ያገቡብንም በራሳችን ስህተት እንጂ እነሱ በፈጠሩት አልነበረም። እስከ አሁን አለማሸነፋችን ግን ተፅኖ አይፈጥርብንም። ቡድኔ ሲሟላ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን”
ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ወልዲያ
“በቅድሚያ ሜዳ ላይ ውጤት ያማረ ባይሆንም ደጋፊዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ ማድነቅ እፈልጋለሁ። ለኔ ከጨዋታው ይልቅ ከፍ ብሎ የታየኝ የደጋፊዎች ድጋፍ ነበር። ጨዋታውን ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ጨርሰን መውጣት ነበረብን።
” ወደዚህ ስንመጣ ባለፉት ሲዳማ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ተጋጣሚያዎቹን ባለማሸነፉ ጫና ውስጥ እንዳለ ስለምናቅ በጥንቃቄ መጫወትን መርጠናል። ብዙ እድህ ፈጥረናል ፤ አሸንፈን መውጣትም እንችል ነበር። ያን ባለማድረጋችን ከእረፍት በፊት ግብ አስተናገድን ሌላ ስራ ፈጥሮብን ለማስገባት ጥረት አድርገን አስቆጥረናል። ቢሆንም ለኔ ጨዋታው አስከፊ አልነበረም። ብዙ ወሳኝ ተጫዋቾቻችንንን እኛም እነሱም አተናል። በቀጣይ ጨዋታወች ግን ትክክለኛውን ወልዲያን ጠብቁ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች ነበሩ። እነሱ በቅርቡ ስለተፈቱ በቀጣይ በሙሉ ጥንካሬ እንቀርባለን፡፡”