​ሪፖርት | ደደቢት ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሀከል ትግራይ ስታድየም ላይ የተደረገው የመቐለ ከተማ እና የደደቢት ጨዋታ ሰማያዊ ለባሾቹ በጌታነህ ከበደ እና አለምአንተ ካሳ ጎሎች አማካይነት ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ ባለፈው ሳምንት ከጨዋታ በፊት በወልድያ እና በመቐለ ከተማ ደጋፊዎች መሀከል በተነሳው ግጭት ህይወቱን ላጣው የመቐለ ከተማው ደጋፊ ሰለሞን ከበደ የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን ከዚህ በፊት በስቴድየም ዙርያ የሚታየውን ረዣዥም ሰልፍ ለማስቀረት ተጨማሪ የመግቢያ በሮች ተከፍለው ተመልካቹ በቀላሉ ወደ ሜዳ መግባት ችሏል።

የተቀዛቀዘ እና በመሀለኛው ሜዳ ክፍል በሚደረጉ ተደጋጋሚ ያልተሳኩ አጫጭር ቅብብሎች በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የታየው በ5ኛው ደቂቃ መድሃኔ ታደሰ ከፍፁም ቅጣት ምት ጠርዝ ላይ ያገኘውን ኳስ ሞክሮ ክሌመንት በቀላሉ ሲያድንበት ነበር። በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ መቐለ ከተማዎች ከደደቢት በተሻለ አጥቅተው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችንም ፈጥረው ሲያመክኑ ታይተዋል።  በተለይም በ13 ደቂቃ ላይ መድሃኔ ታደሰ ከሚካኤል ደስታ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ የመታው እና ደስታ ደሙ ተደርቦ ያወጣበት ኳስ ቀይ እና ነጭ ለባሾቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበ ነበር። በዚሁ የተቀዛቀዘ እና የግብ ሙከራዎች እምብዛም ባልታየበት የመጀመርያው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት ደደቢቶች የመጀመርያ ሙከራ ለማድረግ 20 ደቂቃዎች ፈጅቶባቸዋል። በዚህም ጌታነህ ከበደ በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ለሰለሞን ሀብቴ አቀብሎት ሰለሞን ቢሞክርም ኳሷ በግቡ ቋሚ ለጥቂት ወጥታበታለች። ከዚች ሙከራ በተጨማሪ በ 24ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰለሞን ሐብቴ በረጅሙ ለጌታነህ ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ ሞክሮ ወደላይ ተነስቶበታል። ደደቢቶች 31ኛው ደቂቃ ላይ በብዙ የኳስ ንክኪ እና በጥሩ ፍሰት በቁጥር ተበራክተው ወደ መቐለዎች የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ከገቡ በኃላ የፈጠሩትን ዕድል ወደ ሙከራነት ሳይቀይሩ የቀሩበት አጋጣሚም ተጠቃሽ ነው።

በዚህ መልኩ ጫና ሲፈጥሩ የቆዩት ደደቢቶች ቡድኖቹ ለእረፍት ወደ መልበሻ ቤት ከማምራታቸው ሶስት ደቂቃዎች በፊት የመጀመሪያውን ጎል አግኝተዋል።  ግቧም ከደደቢቶች የአማካይ ክፍል ተነስቶ ከቀኝ መስመር በኤፍሬም አሻሞ አማካይነት ከተሻማ ኳስ የተገኘች ነበረች። ይህ ኳስ በግራ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ለነበረው ሰለሞን ደርሶባት ወደግብ የመታትን ኳስ ጌታነህ ከበደ አግኝቶ ወደ ግብነት ቀይሯታል።


ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር መቐለ ከተማዎች አለምነህ ግርማን በዱላ ሙላቱ በመተካት የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም ይበልጥ ወደ ጎን ተለጥጠው ለመጫወት ሞክረዋል። በዚህ ረገድ ተቀይሮ የገባው ዱላ ሙላቱ በቀኝ የቡድኑ የማጥቃት መስመር በኩል የተለየ ጫና ሲፈጥር ተስተውሏል። በደደቢቶች በኩል ደግሞ ኤፍሬም አሻሞ እና ሽመክት ጉግሳ ወደ መሃል እያጠበቡ በመግባት እንዲጫወቱ መደረጉ ቡድኑ በሜዳው ቁመት የመሀል መስመሩ የማጥቃት ሀይል እንዲጨምር ሆኗል። ከመጀመሪያው በተሻለ ጫን ብለው የተጫወቱት መቐለዎች ወደ ቀኝ መስመር ባደላ ፈጣን እንቅስቃሴ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። በዚህ መነሻነትም ዱላ ሙላቱ 65ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ለማግኘት ወደ ደደቢት ሳጥን ሲገባ በከድር ኩሊባሊ ጥፋት ስለተሰራበት ኢ/ዳኛ በላይ ታደሰ ለባለሜዳዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። ሆኖም ተጨዋቾቹን  እና ዳኛውን አካቶ ሶስት ደቂቃዎችን ከፈጀ ክርክር በኃላ የተመታው የመድሀኔ ታደሰ ፍፁም ቅጣት ምት በክሌመንት ቀኝ ቋሚ በኩል ወደ ውጪ ወጥቷል። መቐለዎችም አቻ የሚሆኑበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
ከዚህ በኃላ በነበረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች ቅያሪዎችን በማድረግ ጭምር ግቦችን ለማግኘት ባደረጉት ተመጣጣኝ ፉክክር መቐለዎች በያሬድ ከበደ እንዲሁም ደደቢቶች በሽመክት ጉግሳ አማካይነት የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ታይተዋል። ሆኖም በስተመጨረሻ ስኬታማ የነበሩት ደደቢቶች ነበሩ። 82ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር አጥቦ በመገባት ኤፍሬም አሻሞ አማካይነት ከሰነዘረው ጥቃት የመጣለትን ኳስ ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ በአራቱ መቐለ ከተማ ተከላካዮች መሀል አሾልኮ በአቤል እንዳለ  ተቀይሮ ለገባው አለምአንተ ካሳ አሳልፎለት አለምአንተ ቀለል ባለ አጨራረስ የደደቢትን መሪነት ማስፋት ችሏል። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳይታይበት ሲጠናቀቅ መቐለ ከተማ በሜዳው የመጀመሪያ ሽንፈት ደርሶበታል።

ዮሀንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ

” በጨዋታው መጀመርያ አጋማሽ ጥሩ አልተንቀሳቀስንም። እነሱ አንድ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው አገቡብን። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ያለቀላቸው የግብ እድሎችንም አምክነናል። ከዚ በተጨማሪም ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተን አልተጠቀምንበትም። በቀጣይ ጨዋታ ያሉብን ክፍተቶች አርመን እንቀርባለን። ”

ንጉሴ ደስታ – ደደቢት

” ሜዳው ለጨዋታ ምቹ ስለሆነ እና ተጫዋቾቼም ይዘነው የገባነውን ታክቲክ በሚገባ በመተግበራቸው አሸንፈን ወጥተናል። ተጋጣሚያችን ተከላክሎ ቢጫወትም ይህንን ሰብረን አሸንፈን በመውጣታችን ደስተኛ ነኝ። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *