ጅማ አባቡና 2-0 ሀላባ ከተማ
(በቴዎድሮስ ታደሰ)
በመጀመርያው ደቂቃ ሱራፌል አወል ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ካመከነው እድል ውጭ እስከ 35ኛው ደቂቃ ድረስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል እቅስቃሴም ሆነ የጎል ሙከራ ያልነበረ ሲሆን ከ35 ደቂቃ በኃላ ጥሩ መቀስቀስ የቻሉት አባቡናዎች በጥሩ ቅብብል በ40ኛው ደቂቃ ቴዎድሮስ ታደሰ ባስቆጠረው ግብ መሪነት ጨብጠው ሊወጡ ችለዋል።
ከእረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የጨዋታ እቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ሀላባዎች አጥቅተው በመጫወት ጫና መፍጠር ቢችሉም ያገኟቸውን የግብ አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻሉም። በባለሜዳዎቹ በኩል በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከተገኙት አጋጣሚዎች ውስጥ በ90ኛ ደቂቃ ከብዙአየሁ እንዳሻው የተሻገረለት ኳስ ሀይደር ሸረፍ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ጅማ አባቡናም በአመቱ የመጀመሪያውን ድል ያስመዘገበበትን ውጤት አግኝቷል።
በሌሎች ጨዋታዎች ዱራሜ ላይ ሀምበሪቾ ሀድያ ሆሳዕናን በ13ኛው ደቂቃ ፀጋአብ ድማሙ እና በ80ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ደስይበለው ባስቆጠረሸቸው ጎሎች 2-0 ሲያሸንፍ ወደ መቂ የተጓዘው ሻሸመኔ በመቂ 3-0 ሽንፈት ቀምሷል። ለመቂ ከተማ 45ኛው በላይ ያደሳ ፣ 75ኛው ተስፋዬ ሰለሞን እንዲሁም 85ኛው ደቂቃ አቢዩ እስማኤል ግብ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቢ ከ ድሬዳዋ ፖሊስ ያገናኘው ጨዋታ በመደበኛው ክፍለ ጊዜ 1-1 ዘልቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ በተቆጠረች ግብ ስልጤ ወራቤ 2-1 ሲረታ ወደ ቦንጋ የተጓዘው ወልቂጤ ከተማ ካፋ ቡናን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ነገሌ ቦረና ከ ቤንች ማጂ ቡና ደግሞ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በዕለተ ቅዳሜ በተደረጉት ጨዋታዎች ዲላ ከተማ በኩሴ ሙታራ ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በድንቅ አጀማመሩ ሲቀጥል ደቡብ ፖሊስ ናሽናል ሴሜንትን 6-0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ረቷል። ለደቡብ ፖሊስ በ14ኛው እና 70ኛው ደቂቃ ብሩክ ኤልያስ ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር በ44ኛው ደቂቃ ኤሪክ ሙራንዳ (ፍ.ቅ.ም) ፣ በ72ኛው ደቂቃ አበባየሁ ዮሀንስ ፣ በ82ኛው ደቂቃ አብደላ እንዲሁም በ88ኛው ደቂቃ በኃይሉ ዋኜ ሌሎቹን ጎሎች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
የደረጃ ሰንጠረዡን ሊንኩን በመጫን ይመልከቱ | LINK