በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ቅዳሜ እለት ሊደረጉ የነበሩት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።
መከላከያ 1-1 ሀዋሳ ከተማ
(በዳንኤል መስፍን)
09:00 ላይ የተደረገው ይህ ጨዋታ ጎል የተስተናገደበት ገና በመጀመርያው ደቂቃ ነበር። ካሜሩናዊው ያቡን ዊልያም የአወል አብደላን መዘናጋት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ በአቤል እግሮች መሀል አሾልኮ በማስቆጠር ሀዋሳ ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ሀዋሳዎች በማጥቃት እንቅስቃሴው ቀስ በቀስ መቀዛቀዝ ማሳየታቸው መከላከያን እንዲያገግም እድል ሰጥቶት ጫና መፍጠር ችሏል። በ19ኛው ደቂቃ ላይም መሳይ ጳውሎስ በሳሙኤል ሳሊሶ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወደ ጎል ቀይሮታል። ፍፁም ቅጣት ምቱ የተሰጠበት ሂደት ያላሳመናቸው የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች እና አባላት በመሀል ዳኛው ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ላይ ቅሬታ አሰምተዋል።
ከዚህ በኋላ ጨዋታው ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በሁለቱም በኩል የጎል ሙከራዎች ተስተናግደዋል። በ21ኛው ደቂቃ ታፈሰ ከግራ ያሻማውን ኳስ ዳዊት ሞክሮ ግብ ጠባቂው አቤል እንደምንም ያወጣበት እንዲሁም ታፈሰ ሰለሞን ከርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ ሞክሮ አቤል ያዳነው ኳስ ሀዋሳን ዳግም መሪ ሊያደርጉ የተቃረረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ። 29ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ኪዳኔ ከቀኝ መስመሮ ያሻገረውን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ቢያገኘውም አገባው ተብሎ ሲጠበቅ ሶሆሆ ሜንሳህ የመለሰበት እና የተመለሰውን ኳስ በተመሳመይ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ምንይሉ ሞክሮ ሶሆሆ ያዳነበት እንዲሁም 44ኛው ደቂቃ ሳሊሶ ከመስመር ሰብሮ በመግባት ያሻገረው እና ምንይሉ ያመከነው በመከላከያ በኩል የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች ተቀይሮ በገባው ፍርዳወቅ ሲሳይ አማካኝነት ከፈጠሩት የግብ እድል ውጪ አመዛኞቹን ደቂቃዎች ጥንቃቄ ላይ አመዝነው ተንቀሳቅሰዋል። በአንፃሩ መከላከያ ጫና ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ምንያምር ፀጋዬ – መከላከያ
” ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ኳስ የሚጫወቱ ቡድኖች በመሆናቸው ነፃ ጨዋታ ነበር። ጎሎች ተሞክረዋል እንቅስቃሴውም ጥሩ ነበር። ያው ለማሸነፍ ነበር የገባነው አልተሳካልንም”
ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ
” ጨዋታውን ባለመረጋጋት ውስጥ ሆነን ነው የተጫወትነው። ምክንያቱም አንደኛ ተከታታይ ሽንፈት ስለገጠመን ከሜዳ ውጪ የሚደረጉ ጨዋታዎች ፎቢያ ውስጣችን አለ። ሁለተኛ ደግሞ ጨዋታው መካሄድ ከነበረበት ቀን ተቀይሮ ነው የተጫወትነው። በዚህም ከልምምድ እና ካመጋገብ ጋር ተያይዞ መዘበራረቅ ተፈጥሯል። እናም ጨዋታው አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ገምተን ነበር። ከዚህ አንፃር ጨዋታው መጥፎ አልነበረም።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-0 ጅማ ጅፋር
(በሚልኪያስ አበራ)
በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሙከራዎች የታጀበ ነበር። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል 7ኛው ደቂቃ ላይ በብዙ ተጨዋቾች የኳስ ንክኪ ከተፈጠረ ዕድል ዲዲዬ ለብሪ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ የሚጠቀስ ሲሆን 19ኛው ደቂቃ ላይም ኃይሌ እሸቱ በተከላካዮች መሀል የሾለከለትን ኳስ ሞክሮ ሲመለስበት ዲዲዬ ለብሪ በድጋሜ አግኝቶ ቢሞክርም ዳዊት አሰፋ አድኖበታል። ጅማ አባጅፋሮችም በኩል በተመሳሳይ 38ኛው ደቂቃ ላይ የፊት አጥቂው ኦካኪ አፎላቢ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ በግቡ አግዳሚ ወደ ላይ ወጥቶበታል።
በሁለተኛው አጋማሽ ላይ የሀይል ሚዛኑ ወደ እንግዳዎቹ ያመዘነ ነበር። በዚህ አጋማሽ ተጠቃሽ የነበረው የኢትዮ ኤሌክትሪኮች 64ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ተሻግር ከሳጥን ውጪ የሞከረው እና በግቡ አናት ተነስቶ የወጣው ኳስ ነው። 61ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት የሞከረው እና በግቡ አናት የወጣባት ሲሆን የሄው ናይጄሪያዊ አጥቂ 84ኛው ደቂቃ ላይ ከኃላ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ቢሞክርም ሱሊማን አቡ ሊያድንበት ችሏል። ከዚህ ውጪ 76ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ሳምሶን ቆልቻ በግንባሩ ሞክሮ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል። ሆኖም ጨዋታው በሁለቱም በኩል ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል።
የኢትዮ ኤሌክትሪኩ የተከላካይ አማካይ ሔኖክ ካሳሁን አይኑ በኳስ ተመትቶ ለህክምና ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል ያመራ ቢሆንም ከአቅማችን በላይ ነው በማለታቸው በሪፈር ለተጨማሪ ህክምና ወደ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል አምርቷል። ሆኖም ቦሌ ወደሚገኝ ሌላ የዐይን ማዕከል አምርቶ ህክምናውን በአግባቡ ተከታትሎ ተመልሷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ብርሀኑ ባዩ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
” ሶስት ነጥብ ይዘን ለመውጣት ነበር ያሰብነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ ለጎል የቀረቡ ኳሶችን ስተናል። በሁለተኛው አጋማሽም እንዲሁ በተሻለ ተንቀሳቅሰናል። እነሱ ሲከላከሉ እኛ ግብ ለማግኘት እየሞከርን ነበር ሆኖም አልተሳካም። ኳስ እንዲህ በመሆኑ ነጥብ ተጋርተን ወጥተናል።”
ገብረመድህን ኃይሌ – መከላከያ
” ጨዋታው ጥሩ ነው። ሁለታችንም በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የምንገኝ ከመሆናችን አንፃር ፉክክሩ ቀላል አልነበረም። እኛ ለማሸነፍ ነበር የመጣነው። በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም የተሻለ ተንቀሳቅሰናል ብዬ ነው የማምነው። በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው ባይሆንም በተታክቲኩ ረገድ የተሻልን ነበርን”