ብፅአት ፋሲል ትባላለች። እግርኳስ ተጨዋች ነች። በሴቶች እግርኳስ ያለፉትን 15 አመታት ካየናቸው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል አንዷ ናት። ይህችን እንስት ከሌሎች ተጫዋቾች ሁሉ ለየት የሚያደርጋት ነገር አለ። እሱም መስማት የተሳናት መሆኗ ሳይገድባት ስትጫወት መቆየቷ ነው።
የእግርኳስ ህይወቷን የጀመረችው በትውልድ ከተማዋ አዳማ ከወንዶች ጋር በሰፈር ውስጥ በመጫወት ነበር። በክለብ ደረጃ መጫወት የጀመረችው ከ1997 በአለቤ ሾው የሴቶች ቡድን ሲሆን በመቀጠል ለወንጂ ፣ ለድሬዳዋ ከተማ በመጨረሻም አምና ለአዳማ ከተማ ተጫውታለች። ብፅአት በእግርኳስ ለረጅም ጊዜ በፅናት ስለመቆየቷ እና ቀጣይ እቅዷ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ያደረገችውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።
መስማት የተሳነሽ በምን ምክንያት ነው ?
በተፈጥሮ ነው መስማት የተሳነኝ። ያም ቢሆን በውስጤ በነበረው መንፈሰ ጠንካራነት ከባዱን ነገር ታግዬ ይኸው እዚህ ደርሻለው። ለዚህም ፈጣሪዬን አመሰግናለው።
የእግርኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት እንዴት አደረብሽ?
ብዙ ጊዜ ሰፈር ውስጥ ከወንዶች ጋር ኳስ መጫወት እወድ ነበር። ይህ መነሻ ሆኖኝ የጀመርኩት እግርኳስ በኋላ በሰዎች ድጋፍና እገዛ በክለብ እንድጫወት ነግረውኝ በአለቤ ሾው ጀምሬ ይኸው እዚህ ደርሻለው።
እግርኳስን ያለ መግባቢያ ቋንቋ መጫወት ከባድ አይሆንም?
ከባድ ነው። ሆኖም የመጫወት ፍላጎቱ ካለህ እና ሁሌም እግርኳስ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ለሟሟላት ከሰራህ ከባድ አይደለም። የእግርኳስ ጨዋታ ራሱ ቋንቋ ነው። ትግባባለህ። መስማት ቢሳንህም በእይታ ብቻ ሁሉን ነገር ማድረግ ትችላለህ።
መስማት የተሳነሽ በመሆንሽ ያጋጠመሽ ችግር አለ ?
በእርግጥ ከተፈጥሮ ጋር መታገል አይቻልም። የሚያጋጥሙ ችግር አለ። አንድ ጊዜ ያጋጠመኝን ልንገርህ ለአዳማ ምርጥ ተመርጬ ስጫወት እኔ ባስቆጠርኩት ጎል የዋንጫ አሸናፊ ብንሆንም ተጋጣሚያችን ቡድን ክስ ከሶ መስማት የተሳናነሽ ነሽ ተብዬ ዋንጫ የተከለከልንበት ጊዜ አረሳውም። በሌላ አጋጣሚ እንዲሁ መስማት የተሳነሽ ተብዬ ለመጫወት ወደ ውጭ ከመሄድ የቀረሁበት ጊዜ ነበር። ያው ይህ ሁሉ አልፏል ፈጣሪ ይመስገን።
በሜዳ ላይ ሆነ ከሜዳ ውጭ ከተጨዋቾች ጋር ያለሽ መግባባት ምን ያህል ነው? ምን ያህልስ ያግዙሻል?
በጣም ጥሩ በሆነ ነገር ሁሉ ያግዙኛል። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሆኖም ግን እኔ የማግዛቸው ይበልጣል። እግርኳስ በራሱ ቋንቋ በመሆኑ።
የሴቶች እግርኳስ አሁን ያለበትን ደረጃ እንዴት ትገለጭዋለሽ ?
ጥሩ ለውጥ እና እድገት አለ። ግን አንድ ነገር መዋሸት የሌለብኝ ነገር አለ። ደሞዙ ለወንዶቹም ለሴቶቹም አድጓል ጥሩ ነው። ግን ኳሱ ላይ በሀገር ውስጥም ሆነ በኢንተርናሸናል ደረጃ እጅግ በጣም የወረደ ነው። ለወደፊቱ የተሻለ ለውጥ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለው።
ከተጫዋቾች ማንን ታደንቂያለሽ?
ሎዛ አበራን አደንቃታለው። ድፍረቷ ፣ ድሪብሏ እና ጎል በምታስቆጥርበት መንገድ ጠንካራ ሴት በመሆኗ አደንቃታለው። ግን እኔ እበልጣታለው። (ፈገግታ)
አሁን የት ክለብ እየተጫወትሽ ነው ?
ከብዙ ክለቦች እንድጫወትላቸው ጥያቄ አቅርቦልኝ ነበር። ሆኖም ፌዴሬሽኑ እንዳልጫወት በመከልከሉ ምክንያት መጫወት አቁሜ ይህን አመት ቁጭ ብያለው። ኳስ እንዳልጫወት በመወሰኑ ምክንያት ከምቀመጥ ብዬ አዳማ ላይ የሚገኙ መስማት የተሳናቸውን እያሰለጠንኩ እገኛለሁ።