አንዳንድ ነጥቦች በብሄራዊ ሊጉ ላይ…

_______________________

አስተያየት – ሚካኤል ለገሰ

_______________________

ከሐምሌ 24 እስከ ነሀሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በ24 ክለቦች መካከል የሚደረገው የኢትዮጲያ ብሄራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር በድሬዳዋ ይካሄዳል፡፡ ለ2008 ዓ.ም. በኢትዮጲያ ፕሪምየርሊግ ለመሳተፍም ክለቦች ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በውድድሩ ባህርይ ምክንያት ለሚድያ ፣ ተመልካች እና አወዳዳሪው አካል አመቺ ያልሆነው ውድድር ከሙሉ የውድድር ዘመኑ ይልቅ ከየዞናቸው አሸንፈው የመጡት ቡድኖች የሚያደርጉት የማጠቃለያ ውድድር የተሻለ ትኩረት ይስባል፡፡ በአንድ ከተማ ተቀምጠው በሚያደርጉት ውድድርም ያልታሰቡ ቡድኖች ሊያልፉ የሚችሉበት እድል ከመፈጠሩም በላይ የክለቦቹን ፉክክር ተመጣጣኝ ያደርገዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

በተቀራረበ የፉክክር ባህርዩ በብዙዎች ከፕሪሚር ሊጉ የተሻለ እንደሆነ የሚታሰበው ብሄራዊ ሊግ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በ32 ክለቦች መካከል ወደሚደረግ የሊግ ውድድር እንደሚቀየር ፌዴሬሽኑ ማስታወቁን ተከትሎ የ84 ክለቦች ውድድር እንደሚቀር ይጠበቃል፡፡

ፌዴሬሽኑ አምናም በተመሳሳይ ወቅት በ18 ክለቦች መካከል የከፍተኛ ብሄራዊ ሊግ በሚል ስያሜ እንደሚካሄድ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም በክለቦች ቅሬታ ምክንያት ቀርቶ ነበር፡፡ አሁን እንደገና ውድድር ለማድረግ ማሰቡ እሰየው የሚያስብል ቢሆንም የውድድሩ አካሄድ ምን መሆን እንዳለበት ከወዲሁ በጥልቀት ሊያስብበት ይገባል፡፡ ክለቦች የፋይናንስ አቅማቸውን ያማከለ ውድድር እንዴት ማዘጋጀት እንዳለበት ፣ ለፌዴሬሽኑ እና ለሚድያ እንዴት አመቺ መሆን እንዳለበት ፣ በጊዜ ውድድሩ የሚናቀቅበት እንዲሁም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያልፉት ክለቦች በምን አኳሃን እንደሚሆን ከወዲሁ ሊያስብበት ይገባል፡፡

 

የብሄራዊ ሊግ ተሳታፊዎች ቁጥር ማነስ ጥቅሙ ብዙ ነው

በብሄራዊ ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች መብዛት ውድድሩን በዞን ለማድረግ አመቺ ቢሆንም በአወዳዳሪው አካል እና በሚድያ ትኩረት ሲነፈገው አስተውለናል፡፡ ይህም በ8 ዞኖች የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ምን አይነት እንቅስቃሴ እንደታየ ፣ የዳኝነት ውሳኔዎች ምን እንደሚመስሉ ለመከታተል አስቸጋሪ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ያሰበው የ32 ክለቦች ሊግ ምናልባትም እነዚህን ችግሮች ሊቀርፍ ይችላል፡፡

አዲሱ ፎርማት አዲስ የሊግ እርከን የሚፈጥር በመሆኑ የክለቦችን ደረጃ እንድንለይ ሊረዳን ይችላል፡፡ ክለቦች ደረጃቸው የቱ ጋር እንደሆነም ያውቁበታል፡፡ ከክልል ቻምፒዮና አልፈው የሚመጡ ቡድኖች ከተቋቋሙ አጭር እድሜ ብቻ ያስቆጠሩ በመሆናቸው ወደ ብሄራዊ ሊግ ባደጉበት አመት ብሄራዊ ሊጉን በብቃት ተወጥተው ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚገቡ ከሆነ በፈተናዎች ያለፉ ባለመሆናቸው በሊጉ የፋይናንስ ፣ የተጫዋች ጥራት እና ጫና የመቋቋም አቅም አይኖራቸውም፡፡ ከክልል ቻምፒዮና ወደ ብሄራዊ ሊግ 2 – ወደ ብሄራዊ ሊግ – ፕሪሚየር ሊግ የሚያደርጉት ሽግግር ግን በየአመቱ እና በየውድድሩ ባህርይ ደረጃቸውን ሊያሻሽል የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡

በቀጣዩ የውድድር ዘመን ፌዴሬሽኑ ሊያስብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች

 

ውድድሩን በቶሎ ማጠናቀቅ

የብሄራዊ ሊግ ውድድር በብዙ ምክንያቶች ከፕሪሚየር ሊጉ ቀድሞ ሊጠናቀቅ ይገባል፡፡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያልፉት ክለቦች ቀደም ብለው በአእምሮ ፣ በፋይናንስ ፣ በስብስብ እና በመሳሰሉት ተዘጋጅተው ለመምጣት ብሄራዊ ሊጉ በቶሎ ሊጠናቀቅ ይገባል፡፡

በውድድሩ ቶሎ መጠናቀቅ ክለቦቹ ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች እኩል የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጊዜ የሚኖራቸው ሲሆን ፌዴሬሽኑም ውድድሩን ለመገምገም ሰፊ ጊዜ ያገኛል፡፡

 

የዝውውር መስኮት ጉዳይ

ወደ ሊጉ የሚያልፉት ክለቦች ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ጋር እኩል የዝውውር ጊዜ ሊያገኙ ይገባል፡፡ የ2007 የኢትዮጵያ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ባለንበት ወር መጀመሪያ ላይ መከፈቱ ይታወሳል፡፡ የብሄራዊ ሊጉ ክለቦች ደግሞ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ይግቡ አይግቡ የሚያውቁት ከነሀሴ 17 በኃላ ነው፡፡ የብሄራዊ ሊጉ ክለቦች ከሰኔ 30 በፊት በፕሪምየር ሊጉ መሳተፍ እና አለመሳተፋቸውን ቢያውቁ ኖሮ በቀጣይ አመት ለፕሪምየር ሊጉ ጉዟቸው አልያም ለብሄራዊ ሊጉ የሚሆናቸውን ተጨዋች አስቀድመው ያስፈርሙ ነበር፡፡ ነገር ግን ነሀሴ 17 ቁርጣቸውን የሚያውቁት ክለቦች ለፕሪምየር ሊጉ የሚመጥኑ ተጫዋቾችን ከገብያው ሊያጡ ይችላሉ፡፡

ውድድሩ ቀድሞ የሚጠናቀቅ ቢሆን የብሄራዊ ሊጉ ውድድር ሳይጠናቀቅ ተጫዋቾቻቸውን በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከመነጠቅ ይድኑ ነበር፡፡ ዘንድሮ በደቡብ ፖሊስ መልካም አቋም ያሳየው ሚካኤል ለማ ለሲዳማ ቡና የፈረመው ብሄራዊ ሊጉ ሳይጠናቀቅ ነው፡፡

ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያልፉ ክለቦች የሚለዩበት መንገድ

ዘንድሮ ከ8 ዞኖች ከ1 እስከ 3 የወጡ ክለቦች ድሚ ውድድር አድርገው የፍፃሜ ተፋላሚዎቹ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያልፋሉ፡፡ ይህ አሰራር የውድድር ዘመኑን በሙሉ በጥሩ አቋም ያጠናቀቁ ክለቦች ይጎዳል በሚል ተቃውሞ ይቀርብለታል፡፡ ከዚህ ይልቅ ከየዞናቸው 1ኛ የወጡት ክለቦች በጥሎ ማለፍ መልክ ጨዋታ ቢያደርጉ ይመረጣል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ክለቦች የውድድር አመቱን በሙሉ የለፉበትን በአመቱ መጨረሻ እንዲያገኙ የሚያደርግ አሰራር በቀጣዩ አመት ከፌዴሬሽኑ ይጠበቃል፡፡

ጥሎ ማለፉን ታሳቢ ማድረግ

ላለፉት ጥቂት አመታት የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) በፕሪሚር ሊግ ክለቦች መካከል ብቻ የሚደረግ ውድድር ሆኗል፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን የብሄራዊ ሊግ ክለቦችም እንዲሳተፉ በማድረግ ለቀጣይ የውድድሩ ጥንካሬ መሰረት ሊጥል ይገባዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ይህን ውድድር በ2 የሊጉ እርከኖች ሞክሮ በቀጣይ አመታት ወደታችኛውም እርከኖች ቢያመራ ጥሩ ነው፡፡ የብሄራዊ ሊጉ ውድድር በዞን ተከፋፍሎ እንደሚደረግ የሚጠበቅ በመሆኑም የጥሎ ማለፍ ውድድሩ በክለቦቹ ላይ ጫና የመፍጠር እድሉ ዝቅተኛ ይሆናል፡፡

ለምሳሌ – በቅድሚያ በአንደኛው ዙር በብሄራዊ ሊጉ የ2007 የውድድር ዘመን ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው 4 ክለቦች እርስ በእርስ ተጫውተው የሚያልፉት 2 ክለቦች ከነሱ የተሻለ ደረጃ ካላቸው 18 ክለቦች ጋር ተቀላቅለው ይጫወታሉ፡፡ በ2ኛው ዙር የሚያልፉት 10 ክለቦች ደግሞ ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው የብሄራዊ ሊጉ ክለቦች ጋር በ3ኛው ዙር ተጫውተው 10 ቡድኖች ወደ 4ኛው ዙር ያልፋሉ፡፡ ከ4ኛው ዙር ጀምሮ የፕሪሚየር ሊን ክለቦች በማካተት ውድድሩን ማካሄድ የተሳታፊ ክለቦችን ከማብዛቱ በተጨማሪ የውድድሩን ትክክለኛ ጣእም እንድንረዳ ያደርገናል፡፡የጥሎ ማለፉ ለብሄራዊ ሊግ ክለቦች ብቸኛው የአፍሪካ ውድድር ተሳትፎ መንገድ በመሆኑም ጠንክረው እንዲቀርቡ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡

ያጋሩ