የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ከፋሲል ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከወትሮው ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ተመልካች በታደመመበት እና በርካታ የፋሲል ደጋፊዎች በተገኙበት የዛሬው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ በወንድማማችነት መንፈስ በሁለቱ ክለብ በደጋፊዎች መካከል የክልላቸውን ባህል የሚያንፀባርቅ አልባሳት በለበሱ እንስት ደጋፊዎች አማካኝነት የስጦታ ልውውጥ አድርገዋል።
ፌ/ዳኛ ቢንያም ወርቅአገኘው ጨዋታውን በመቆጣጠር ፣ ውሳኔዎችን በተገቢው ጊዜ በመስጠት በጥሩ ብቃት በዳኘበት ጨዋታ በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ጎል አይቆጠር እንጂ የጨዋታው የኳስ ፍሰትም ሆነ አጠቃላይ እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ነበር።
ዳዊት እስጢፋኖስ በዘንድሮ የፋሲል ቆይታው ለመጀመርያ ጊዜ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ሲጫወት የአዳማው አምበል ሱሌማን መሀመድ ከሚታወቅበት የግራ መስመር ተከላከይነት ሚናው በተለየ መንገድ በሁሉም የሜዳ ክፍል በነፃነት የተጫወተ ሲሆን ባለሜዳዎቹ አዳማዎችም ሆኑ አፄዎች በ4-2-3-1 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል። የጨዋታው የመጀመርያ 20 ደቂቃ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጎል ሙከራ ያልተደረገበት እና የጥንቃቄ አጨዋወት የነበረበት እንዲሁም ኳሱ በተወሰነ የሜዳ ክፍል በተለይ በመሀል ሜዳ ላይ ብቻ ተገድቦ ቡድኖቹ የመስመር የማጥቃት ዞንን ሳይጠቀሙበት በመቅረታቸው የጎል ሙከራ እንዳንመለከት አድርጎናል። 27ኛው ደቂቃ ላይ ሲሳይ ቶሊ ከ16.50 መስመሩ ላይ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ቅጣት ምት ተከትሎ ደጋፊው ዳዊት እስጢፋኖስ ይጠቀምበታል በማለት ተስፋ ቢያደርግም ኳሱ በአዳማ ተከላካዮች ተደርቦ ሊወጣ ችሏል ።
አጼዎቹ በተወሰነ መልኩ በመሀል ሜዳው እንቅስቃሴ ብልጫ ወስደው ቢጫወቱም በሚገባ ኳስ ለአጥቂዎች ማድረስ እየተሳናቸው በአዳማ ተከላካዮች ሲጨናገፍባቸው ተስተውሏል። በ43ኛው ደቂቃ ላይ ኤርሚያስ ሀይሉ ከቀኝ መስመር በጥሩ መንገድ ተከላካዮችን አልፎ ያሻገረውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ፊሊፕ ዳውዝ ኳስን ከመሬት ጋር አንጥሮ ቢሞክርም ለጥቂት የወጣበት አጋጣሚ በመጀመርያው አጋማሽ የተመለከትነው ብቸኛው የጎል ሙከራ ነበር። ምን አልባት በመጀመርያው አጋማሽ ሙከራዎችም ሆነ ጎል እንዳይቆጠሩ የተከላካዮቹ ሚና ጠንካራ ቢሆንም በሁለቱም በኩል በአጥቂዎችና በአማካዮች መካከል በነበረው ሰፊ ክፍተት ምክንያት አጥቂዎቹ በብዛት ተነጥለው ይታዩ ነበር።
ከእረፍት መልስ ሁለቱ ቡድኖች በተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ጨዋታውን ቢቀጥሉም በአንፃራዊነት የተሻሉ የጎል ሙከራዎችን መመልከት ችለናል። 56ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሱሌማን መሀመድ ተከላካዮችን አሸማቆ በግራ እግሩ የመታውን ጠንካራ ኳስ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት እና በ66ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ከነአን ማርክነህ ከእጅ ውርወራ የተቀበለውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት በተከላካዮች እግር ሰር መሬት ለመሬት መቶ ግብ ጠባቂው ሳማኬ በድጋሚ ተወርውሮ ያዳነው በሁለተኛው አጋማሽ የተመለከትናቸው የጎል ሙከራዎች ነበሩ።
ኳሱ መሀል ሜዳ ላይ ብቻ ተገድቦ ፣ የተጨዋች ቅያሪ የበዛበት ሆኖ ፣ ተጨዋቾቹ በተለይ ከ75ኛው ደቂቃ በኋላ ተዳክመው ፣ የሁለቱም ቡድን ግብ ጠባቂዎች ስራ ፈትተው ፣ ጨዋታው ያለ ምንም ጎል ተጠናቋል።
ከጨዋታው በላይ የዳኛው ጨዋታን የመምራት ብቃት ጎልቶ በታየበት እና ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ስፖርታዊ ጨዋነት በሰፈነበት መልኩ ደጋፊዎች ቡድኖቻቸውን በአንድ ድምፅ ሲደግፉ መመልከት ከጨዋታው በላይ የተመለከትነው በጎ ተግባር ነው።
የአሰልጣኞች አስተየያየት
ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ
” ጨዋታው ጥሩ ነው። ወደ ሜዳ የገባነው ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ነበር። ለዚህም የሚረዳንን አጨዋወት ይዘን ቀርበናል። የተጨዋች ለውጥም አድረገን ነበር። የኳስ ነገር ሆኖ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ
” ከእኛ አዳማዎች የተሻሉ ነበሩ። ጨዋታው ያለ ጎል ቢጠናቀቅም ለተመልካች አዝናኝ ሆኖ አልፏል። አሁንም ጎል የማስቆጠር ችግራችን አልተቀረፈም። በቀጣይ እየሰራን ችግራችንን ለማስተካከል እንሞክራለን። “