ድሬዳዋ በእንግዶቿ ደምቃለች

የዘንድሮው የብሄራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር የሚካሄድባት ድሬዳዋ በእንግዶቿ ደምቃለች፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ በከተማው ተዘዋውራ እንደታዘበችው በከተማዋ በከተሙት 24 ክለቦች እና አጠቃላይ እንግዶች ደመቅመቅ ብላለች፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ያነጋገረቻቸው አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ቅዳሜ ለሚጀመረው ውድድር ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ የተናገሩ ሲሆን የውድድሩ አዘጋጅ አካል በዳኛ አመዳደብ ላይ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

የውድድሩ የምድብ ድልድል ዛሬ እንደሚወጣ ቢጠበቅም ወደ ነገ ተዘዋውሯል፡፡ የመክፈቻው ቀንም ከአርብ ወደ ቅዳሜ ተሸጋግሯል፡፡

የኢትዮጵያ እገርኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው ድልድሉ በ4 ምድብ (በአንድ ምድብ 6 ቡድኖች) የሚከፈል ሲሆን በጥሎ ማለፍ ውድድሮች በመደበኛ የጨዋታ ክፍለጊዜ አቻ የሚወጡ ቡድኖች በቀጥታ ወደ መለያ ምት ያመራሉ፡፡

ውድድሩ በድሬዳዋ ስታድየም እና ሳቢያን ሜዳ እንደሚደረግም ታውቋል፡፡ ከድሬዳዋ ስታድየም በመቀጠል 2ኛው ስታድየም የትኛው ይሁን የሚለው ሲያከራክር የቆየ ሲሆን ትላንት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሙ አባላት እና ዳኞች ሜዳዎችን ተዟዙረው በመገምገም ሳቢያን ሜዳን 2ኛ ምርጫ አድርገዋል፡፡

ዳንኤል መስፍን ከ ድሬዳዋ

ያጋሩ