በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ቅዳሜ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 1-0 ሲረታ በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጅማሮ ያቡን ዊሊያምን ተክቶ የገባው ሙሉአለም ረጋሳ የማሸነፍያዋን ጎል ለማስቆጠር በሜዳ ላይ መቆየት ያስፈለገው 2 ደቂቃ ነበር፡፡ ያለፉት ሁለት አስርት አመታትን በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሰበታ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ መድን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ብቃቱን ያሳየው አማካይ በክለቡ ማልያ የመጀመርያ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል፡፡ ሙሉአለም ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ጎል በማስቆጠሩ የለተየ ስሜት እንደማይሰማው ገልቷል፡፡ “እኔ ማሸነፋችን እንጂ ግብ ማስቆጠሬን እንደተለየ ነገር አላየሁም፡፡ ጎል ከማስቆጠር ይልቅ ደስተኛ የሚያደርገኝ ኳስን ለጎል አመቻችቼ ማቀበል ነው፡፡››
ኢትዮጵያ መድን በ2006 ከፕሪምየር ሊጉ ከወረደ በኋላ ሙሉአለም ከሊጉ ርቆ የቆየ ሲሆን ከ3 የውድድር ዘመናት በኋላ ወደ ሊጉ ተመሶ እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ሆኖም ከሊጉ መራቁ በአቋሙ ላይ የፈጠረበት ተጽእኖ እንደሌለ ይናገራል፡፡ “ከእንቅስቃሴ አልራኩም፡፡ ምናልባት አዲሱ ፎርማት (ከፍተኛ ሊግ) ያለው ረጅም ጉዞ ብዙም ስላልተመቸኝ እዛ ውስጥ መግባት አልፈለኩም፡፡ ሆኖም ከእንቅስቃሴ ብዙም ስላልራቅሁ ብዙም ችግር አልፈጠረብኝም፡፡” ብሏል፡፡ ሙሉአለም አክሎም በወርቃማ ዘመኑ የነበረው እና አሁን ያለውን የሊጉ ደረጃ በዚህ መልኩ ገልፆታል፡፡
“ያኔ የነበረው የቡድናችን (ቅዱስ ጊዮርጊስ) አቋም ጥሩ ስለነበር ብዙ ቡድኖች እያፈገፈጉ ስለሚጫወቱ ትንሽ ሊጉን ለማወቅ ትቸገራለህ፡፡ ጊዮርጊስን ብዙዎቹ ፈርተው ስለሚመጡ ያኔ ከሌሎች ክለቦች ጋር የነበረን ልዩነት በጣም ሰፊ ነበር፡፡ ወደ ሌሎች ክለቦች ሄደህ ስትጫወት ግን ልዩነቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳይሀል፡፡ ቡድኖች ብዙ ጊዜ ተመልካችን ለማስደሰት አይደለም የሚጫወቱት፡፡ ቡድኖቹ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ከመፎካከር ይልቅ ሳይሸነፉ ለመውጣት መከላከል ላይ ስለሚያዘነብሉ የሚስብ ነገርን አታይም፡፡ ወደ ኋላ እያፈገፈግክ በሄድክ ቁጥር ከእንቅስቃሴ እና ከውጤት እየራቅክ ነው የምትመጣው”፡፡
የቅዳሜዋን የማሸነፍያ ጎል ከጎኑ ለነበሩት እና ሲያበረታቱት ለቆዩት የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች መታሰብያ ያደረገው ሙሉአለም በቀጣይ ቡድኑ የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ እንደተዘጋጀ ገልጻል፡፡ “ቡድኑ የሚፈልግብኝን ነገር ሁሉ ለማድረግ ሁሌም እዘጋጃለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን በየጨዋታው ላይ በመሰለፍ እና ባለመሰለፍ ላይ የሚወሰን ነገር አይደለም፡፡ ራሴን የማሻሽልበትን መንገድ ብቻ ነው የማሳየው፡፡ በተረፈ አሰልጣኛችን የሚወስነው ነገር ስለሆነ አስርም ሆነ ዘጠና ደቂቃ በተሰጠኝ እድል ራሴን ማሳየት እና ቡድኑ የሚፈልግብኝን ለማበርከት ነው የተዘጋጀሁት፡፡”