ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀደመ ዝናው በተቃራኒ መንገድ የቁልቁለት ጉዞ መጓዙን ባለፉት ተከታታይ አመታት ቀጥሎበታል። የ3 ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ ኤሌክትሪክ በዘንድሮ አመት የውድድር ዘመን ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች አንዱን አሸንፎ 2 ጨዋታ አቻ በመውጣት ከኢትዮጵያ ቡና እና ወልዲያ ጋር ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ራሱን ባለፉት አመታት ላይ እንደነበረው ሁሉ በሰንጠረዡ የመጨረሻ ሶስት ደረጃዎች ላይ አግኝቶታል።
ክለቡ በክረምቱ የተሻለ የዝውውር እንቅስቃሴ በማድረግ ጥሩ አጀማመር ቢያሳይም በተከታታይ በወልዋሎ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከጅማ ጋር ያለ ጎል አቻ መለያየቱን ተከትሎ በአሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ ቀጣይነት ዙርያ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛሉ።
ከ2007 ጀምሮ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እየመሩ የሚገኙት አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ ከኃላፊነታቸው ሊነሱ እንደተቃረቡ ከክለቡ አካባቢ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን በክለበለ ዙርያ ያሉ ሰዎችመ የተለያዩ አስተያየቶች እየሰጡ ይገኛሉ። አሰልጣኙ ባለፉት የውድድር ዘመናት ቡድኑ ከስብስብ ጥራቱ በተቃራኒው ላለመውረድ እንዲጫወት ያደረጉ በመሆናቸው ክለቡ ከሚገባው በላይ ታግሰሸቸዋል የሚሉ እንዳሉ ሆነው ከሌሎች ክለቦች አሰልጣኞች በንፅፅር አነስተኛ የሆነ ወርኃዊ ደሞዝ እየተከፈላቸው በስራቸው እንደመቀጠላቸው እንዲሁም እስካሁን እያስመዘገቡት ያለው ውጤት ከአሰልጣኝነት እስከመነሳት የሚያደርስ ባለመሆኑ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል የሚሉ ወገኖችም አሉ። ሆኖም የክለቡ አመራሮች በአሰልጣኙ ላይ እምነት እንዳጡ በተለያዩ መንገዶች ከማሳየታቸው በተጨማሪ ለተጫዋቾቹ የአሰልጣኝ ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል እንደተነገራቸው ተሰምቷል።
ኤሌክትሪክ ባሳለፍነው እሁድ ሦስት አሰልጣኞችን (አሸናፊ በቀለ ፣ ጥላሁን መንገሻ እና ወንድማገኝ ከበደ) በክለቡ ቢሮ በመጥራት ኢንተሪቪው እንዳደረገ ተገልጿል። ዛሬ ረፋድ ላይ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው አሰልጣኝ መካከል አሸናፊ በቀለ እንዳሸነፉ የተነገረ ሲሆን በቅርቡ ክለቡ ይፋ እንደሚያደርገውም ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ምንጮቿ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ብርሃኑ ቡድኑን ለደደቢት ጨዋታ እያዘጋጁ እንደሆነ ገልፀው የሚባለውን ነገር ከመስማት ውጭ ምንም ነገር እንደማያውቁ ገልፀዋል። የሚሆነውን ነገር በትግስት በመጠበቅ ወደፊት የሚሆነውን አይተው ሰፊ ማብራሪያ እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
የክለቡን አሰልጣኝነት ለመረከብ በዝግጅት ላይ እንዳሉ የተነገረላቸው አሰልጣኝ አሸናፊን በቀለን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን ከፌዴሬሽኑ አካባቢ ባገኘነው መረጃ የሴካፋ የብሔራዊ ቡድኑን ቀይታ አስመልክቶ አሰልጣኙ ሪፖርት እንዲያቀርቡ እየተጠበቀ ነው። ከሌላ ወገን ጋር ድርድር ለማድረግ ምንም ቅድመ ሁኔታዎች ባልተፈፀሙበት ሁኔታ ከኤሌክትሪክ ጋር ከስምምነት ላይ ስለመደረሳቸው ጉዳዩን በመከታተል ተከታትሎ አስፈላጊውን ምላሽ እንደሚሰጥም ለማወቅ ችለናል።
ከዋልያዎቹ ጋር በቅርብ አመታት ያልታየ ዝቅተኛውን ውጤት እያስመዘገቡ የሚገኙት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከኤሌክትሪክ በተጨማሪ ከቀድሞ ክለባቸው ሲዳማ ቡና ጋርም ስማቸው ተያይዞ እየተነሳ ይገኛል።