ጌታነህ ከበደ ለዩንቨርሲቲ ኦፍ ፒሪቶሪያ ፈረመ

ከቤድቬስት ዊትስ ጋር በስምምነት ከተለያየ በኃላ ያለክለብ ረጅም ሳምንታትን ያስቆጠረው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል አጥቂ ጌታነህ ከበደ በስተመጨረሻም ለደቡብ አፍሪካው ክለብ ለዩንቨርሲቲ ኦፍ ፒሪቶሪያ ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል፡፡ አማተክስ በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው ክለቡ ጌታነህን በነፃ ዝውውር የግሉ አድርጓል፡፡

በቤድቬስት ዊትስ ሳይፈለግ የተለቀቀው ጌታነህ ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲያያዝ ነበር፡፡ ብሎምፎንቶን ሴልቲክ እና ማፑማላንጋ ብላክ አስ ከጌታነህ ፈላጊ ክለቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከማፑማላንጋ ብላክ አስ ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየው ጌታነህ ክለቡ በሱ ላይ ዕምነት በማጣቱ ሳያስፈርመው ቀርቷል፡፡

ዩንቨርሲቲ ኦፍ ፒሪቶሪያ ጌታነህን ለማስፈረም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደነበረ ያገኘናቸው መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ክለቡ በ2014/15 የውድድር ዘመን በአብሳ ፒሪሚየርሺፕ 13ኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን በሰሜን አየርላንዳዊው ሳሚ ትሮተን ይሰለጥናል፡፡ በ2003 ፒሪቶሪያ ኤፍሲ የተባለው ክለብ በመግዛት የተመሰረተው ዩንቨርሲቲ ኦፍ ፒሪቶሪያ የሚተዳደረው በዩኒቨርሲቲው ስር ነው፡፡ ጌታነህ ቀደም ሲል ሲጫወትበት የነበረው ቤድቬስት ዊትስም በዊትስ ዩኒቨርሲቲ ስር ያለ ክለብ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ፈፈፈ

አማተክስ የጌታነህን መፈረም በማስመልከት በክለቡ የትዊተር ገፅ ላይ በአማርኛ ‘እንኳን ደህና መጣ ጌታነህ ከበደ’ በሚል መልካም ምኞታቸውን አስፍረዋል፡፡ ጌታነህ በ2014/15 የውድድር ዘመን 2 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ በአማተክስም የተሻለ የመሰለፍ ዕድል እንደሚያገኝ ይታመናል፡፡ ጌታነህ ለአማተክስ የፈረመ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ነው፡፡ ከጌታነህ በፊት ፍቅሩ ተፈራ በአማተክስ መጫወቱ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል ለድረገፃችን ቅርብ የሆነ የደቡብ አፍሪካ ጋዜጠኛ ባደረሰን መረጃ ጌታነህ ለክለቡ የፈረመው በውሰት ውል ሲሆን ከቢድቬትስ ዊትስ እንዳልተሰናበተና የደሞዙን ግማሽ እንደሚከፍል ተነግሯል፡፡

ያጋሩ