ዛሬ አዲስ አበባ እና ጎንደር ላይ በሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች የሊጉ ስምንተኛ ሳምንት ይጀምራል። እንደተለመደውም እነዚህን ጨዋታዎች በተመለከተ የምናነሳቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልዲያ
በማኑሄ ወልደፃዲቅ መሪነት 9፡00 ላይ በሚጀምረው በዚህ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አሰልጣኝ እና በደጋፊዎች ተቃውሞ ታጅቦ ባለፉት ሳምንታት በሜዳው ሊያደርጋቸው የነበሩ ሁለት ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ የተላለፉበትን ወልዲያን ያስተናግዳል።
አመቱን በድል ጀምረው የነበሩት ወልድያዎች ከዚያ በመቀጠል ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ማሳካት የቻሉት ሶስት የአቻ ውጤት ነጥቦችን ብቻ ነው። አምና መልካ ቆሌ ላይ በተገናኙበት ወቅት ወልድያ በበድሩ ኑርሁሴን ብቸኛ ጎል ማሸነፉን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሴቪችን ማሰናበቱ ይታወሳል። ዘንድሮ ደግሞ በተመሳሳይ ወልድያን የሚያስተናግድበት ጨዋታ የአዲሱ ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ የመጀመሪያ ጨዋታ የመሆኑ አጋጣሚ ትኩረት ስቧል። ቡድኑ ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካቱን እና በሰባተኛው ሳምንት ጅማ ላይ ያሳየውን ደካማ አቋም ተከትሎ ሳምንቱን ሙሉ የክለቡ ደጋፊዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በክለቡ አመራሮች ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ሲያሰሙ ሰንብተዋል። ከውጤት መጥፋቱ በተጨማሪ የቡድኑ አጨዋወት እንደወትሮው አለመሆኑ ለደጋፊዎች ደስተኛ አለመሆን ተጨማሪ ምክንያት ሲሆን በዛሬው ጨዋታ ላይም ይህ ጉዳይ በሰፊው እንደሚንፀባረቅ የሚጠበቅ ነው።
በወልዲያ በኩል ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበረው አዳሙ መሐመድ ልምምድ ቢጀምርም ለዚህ ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ወደ ሴካፋ ከማቅናቱ በፊት ጀምሮ ጉዳት ላይ የነበረው ተስፋዬ አለባቸው እና የምግብ መመረዝ ህመም የገጠመው ብሩክ ቃልቦሬ ለጨዋታው የማይደርሱ ይሆናል። ክሪዚስቶም ንታንቢን ለሳምንታት በጉዳት ባጣው ኢትዮጵያ ቡና በኩል መስዑድን መሀመድ ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ ቢጠበቅም ጅማ ላይ ተጎድተው የወጡበትን የመሀል ተከላካዮቹን አክሊሉ አያናው እና ቶማስ ስምረቱን አገልግሎት የማያገኝ ሲሆን በአባጅፋሩ ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ሌላኛው ተጨዋች ሳሙኤል ሳኑሚም ለዛሬው ጨዋታ የመድረሱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል።
ኢትዮጽያ ቡና በአዲስ አሰልጣኝ ስር ጨዋታውን እንደማድረጉ የሚኖረውን አቀራረብ ከወዲሁ ለመተንበይ አስቸጋሪ ያደርገዋል። እስካሁን በአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ስር የ4-4-2 ዳይመንድ እንዲሁም በአሰልጣኝ ሀብተወልድ ደስታ ስር በ 4-2-3-1 አሰላለፍ የተመለከትነው ቡና በአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ስር ደግሞ ሌላ አይነት አቀራረብ ሊኖረው ይችላል። ሆኖም አሰልጣኙ ስራቸውን በዚህ ሳምንት ከመጀመራቸው አንፃር በተጨዋቾች ምርጫ እና በኳስ ቁጥጥር ላይ ከተመሰረተው የቡድኑ አጨዋወት ላይ የጎላ ለውጥ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው ወልድያ የማጥቃት ስትራቴጂ አማራጮቹ ጥያቄ ውስጥ ገብተዋል። በክረምቱ ዝውውር ካገኛቸው የተጨዋቾች ስብስብ በመነሳት አምና ከወገብ በላይ የነበረው የቡድኑ ድክመት ዘንድሮ ሊቀረፍ እንደሚችል ቢጠበቅም እስካሁን የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልቻለም። በዛሬው ጨዋታ ኢትዮጽያ ቡና እስካሁን ከተጠቀመበት የመሀል ተከላካዮች ጥምረት በተለየ የአምናውን የወንድይፍራው ጌታሁን እና ኤፍሬም ወንደሰን ጥምረት መጠቀሙ ምናልባት ለወልዲያ የፊት መስመር አጥቂዎች የተሻለ ዕድልን የሚፈጥር ሊሆን ይችላል። እዚህ ቦታ ላይ ከሚጠበቀው ፍልሚያ በተጨማሪም ባለፉት ጨዋታዎች ተጋጣሚው ሳጥን ድረስ ዘልቆ የመግባት ችግር የታየበት የቡናማዎቹ የአማካይ መስመር ብሩክ ቃልቦሬን እና ተስፋዬ አልባቸለውን እንደማይጠቀም ከሚጠበቀው የወልድያ አማካይ ክፍል ጋር የሚያደርገው ፉክክር ጨዋታውን ለመወሰን የሚኖረው ድርሻ ከፍ ያለ ነው።
ፋሲል ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
እስካሁን ሽንፈት ካላስተናገዱ ጥቂት ክለቦች መሀከል አንዱ የሆነው ፋሲል ከተማ ዘንድሮ በሜዳው ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ማግኘት ችሏል። በመሆኑም የዛሬው ጨዋታ ላይ የሚያመዘግበው ውጤት ቡድኑ ከአምና ጀምሮ በሜዳው ላይ በሚያደርገው ጨዋታዎች ወቅት የሚታይበት አንፃራዊ ድክመት ዘንድሮም አብሮት መኖሩን እና አለመኖሩን የሚያመላክት ይሆናል። በተመሳሳይ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻን ማሳካት ለቻለው ሀዋሳ ከተማም የዚህ ጨዋታ ውጤት ከሜዳው ውጪ በሚያሳየው አቋም ጥያቄ ለሚነሳበት ክለብ ሌላ ዕድል የሚሰጥ ይሆናል። በዕኩል አስር ነጥቦች አራት እና አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ቡድኖች የሚያገናኘውን ይህ ጨዋታ በተፈሪ አለባቸው የመሀል ዳኝነት እንደሚደረግ የሚጠበቅ ሲሆን አምና ስድስተኛ ሳምንት ላይ ተገናኝተው 1-1 የተለያዩት ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ ጨዋታውን መልካም እንቅስቃሴ እና ብርቱ ፉክክር ሊታይባቸው ከሚችሉ የሳምንቱ ጨዋታዎች አንዱ የሚያደርገው ይሆናል።
ፋሲል ከተማ የይስሀቅ መኩሪያን አገልግሎት ከጉዳት መልስ የሚያገኝ ሲሆን ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው ያሬድ ባየህ ከጨዋታው ውጪ ከመሆኑ ባሻገር የመስመር አጥቂው አብዱርሀማን ሙባረክ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል። ዮናታን ገዙ ፣ እስራኤል እሸቱ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ ተክለማሪያም ሻንቆ ፣ ጋብሬል አህመድ እና ዮሀንስ ሴጌቦ ደግሞ በሀዋሳ ከተማ በኩል በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ ተጨዋቾች ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን የመጡበትን መንገድ ስንመለከት ጥንካሪያቸው እና ድክመታቸው የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን። ሀዋሳ ከተማ እስካሁን ስምንት ግቦችን ከመረብ በማገናኘት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በርካታ ግቦችን ከማስቆጠር አንፃር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአንፃሩ ፋሲሎች ማስቆጠር የቻሏቸው አራት ግቦች ከተጋጣሚያቸው በቁጥር በግማሽ ያነሱ ናቸው። በአንፃሩ ከመጀመሪያው ጨዋታ በኃላ ግብ ያላስተናገደው ፋሲል ከተማ ከቅዱስ ጊዮጊስ እና ድሬደዋ ከተማ ጋር በሊጉ ጥቂት ግብ ያስተናገደ ቡድን ሆኖ ለዚህ ጨዋታ ሲደርስ በተቃራኒው ሰባት ግቦች የተቆጠሩበት ሀዋሳ ከተማ በርካታ ግቦችን በማስተናገድ በሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዚህ መሰረትም በጨዋታው ጠንካራው የፋሲል ከተማ የተከላካይ መስመር በርካታ ዕድሎች ከሚፈጠርለት የሀዋሳ የፊት መስመር ጋር የሚገናኝ መሆኑ በቦታው የሚኖረውን ፉክክር እጅግ አጓጊ ያደርገዋል። በሌላኛው የሜዳ ክፍል ደግሞ ክፍተት የሚታይበት የሀዋሳ ከተማ የተከላካይ መስመር የሜዳውን ስፋት በአግባቡ ከሚጠቀመው የፋሲል ከተማ የአጥቂ መስመር የሚገጥመው ፈተናም ቀላል የሚባል አይሆንም። ከሁሉም በላይ ግን ጨዋታው በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ላይ የተመሰረተን ቡድን የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ማዕከል ከሚያደርግ ቡድን ጋር የሚያገናኝ መሆኑ ተጠባቂነቱን ከፍ ያደርገዋል። በመሆኑም የሀዋሳ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል ላይ ከሚኖራቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመነሳት እንዲሁም ፋሲሎች ይህን የሀዋሳን አጨዋወት ካቋረጡ በኃላ ወደ ሀዋሳዎች የግብ ክልል የሚደሩሱበትን ፍጥነት በመጠቀም የሚፈጥሯቸው የግብ ዕድሎች ከቡድኖቹ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች የጨዋታ ባህሪ አንፃር አሸናፊውን ቡድን ለመለየት ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ደደቢት
በደረጃ ሰንጠረዡ 14ኛ እና የ1ኛ ደረጃ ላይ መገኘታቸው በራሱ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ደደቢት ዛሬ በሣህሉ ይርጋ የመሀል ዳኝነት ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊት በሊጉ ጉዟቸው የሚገኙበትን የተለያየ ፅንፍ የሚያሳይ ነው። ከፋሲል ከተማ እና ድሬደዋ ከተማ ጋር ያለግብ ከተለያየ በኃላ መቐለ ከተማን እና ሲዳማ ቡናን በተከታታይ ማሸነፍ የቻለው ደደቢት በሁለቱ ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ግቦቹ የተቆጠሩት በአምስት የተለያዩ ተጨዋቾች አማካይነት መሆኑ ደግሞ የደደቢት የማጥቃት አማራጮች መበራከት እና ለአጠቃላይ ቡድኑ መሻሻል ማሳያ ነው። በአንፃሩ በሜዳው ከጅማ አባጅፋር ጋር ያለግብ ከመለያየቱ በፊት ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሳምንት ከወልድያ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ በመተላለፉ ራሱን ለማስተካከልም ሆነ ከጠንካራው ደደቢት ጋር ለመፋለም ሰፊ የዝግጅት ጊዜ እንደነበረው መናገር ይቻላል። ሆኖም የዛሬው የ 11፡30 ጨዋታ ለአሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ የመጨረሻ የቀዮቹ ቤት ጨዋታ መሆኑ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል። በቀጣይም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ብሔራዊ ቡድኑን ለመልቀቅ ለሁለተኛ ጊዜ መልቀቂያ ያስገቡትን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ እንደሚቀጥር እየተጠበቀ ይገኛል።
ደደቢት አሁንም የግራ መስመር ተከላካዩ ብርሀኑ ቦጋለን በጉዳት ሳቢያ የማያሰልፍ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዲስ ነጋሽን በቅጣት ካለመጠቀሙ ባሻገር ኄኖክ ካሳሁንን ከጉዳት መልስ እንዲሁም ግርማ በቀለን ከብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ በኃላ የሚያገኝ ይሆናል።
የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታው ደደቢት ካለው አነስተኛ የተጨዋቾች ስብስብ አንፃር ከውጤቱ ማማር ባለፈ በአቀራረብ ደረጃ እያሳየ ያለው ተለዋዋጭነት አስገራሚ ሆኗል። እስከ ስድስተኛው ሳምንት ድረስ በ 4-4-2 እና 4-2-3-1 አሰላለፎች ሲጠቀም የሰነበተው ደደቢት ሳምንት ከፊት ሶስት አጥቂዎችን በመጠቀም በ4-3-3 ቅርፅ ወደ ሜዳ ገብቶ ጨዋታውን በሰፊ ግብ ልዩነት ከማሸነፉም ባለፈ በእንቅስቃሴም ከሌላው ጊዜ ከፍ ባለ ደረጃ አስፈሪ ሆኖ ታይቷል። የጌታነህ ከበደ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ለቡድኑ የአማካይ ክፍል እየቀረበ መጫወት እና ግብ የሆኑ ኳሶችን እስከማቀበል መድረስ ከአቤል ያለው ፍጥነት ጋር ተዳምሮ ቡድኑ በተጋጣሚ ሳጥን ዙሪያ የሚፈጥረውን ጫና ሁለገብ አድርጎታል። ደደቢት በሲዳማው ጨዋታ ላይ በተጠቀመው አቀራረብም ከተከላካይ አማካዩ አስራት መገርሳ ፊት የተሰለፉት አቤል እንዳለ እና የአብስራ ተስፋዬ እንዲሁም ተቀይሮ የገባው አለምአንተ ካሳም ጭምር በማጥቃት ሽግግር ወቅት የነበራቸው የቦታ አያያዝ ቡድኑ በተጨዋቾች መሀከል የተመጠነ ርቀት እንዲኖረው እና በሁለቱ መስመሮችም ሆነ መሀል ለመሀል ጥቃትን ለመሰንዘር አማራጭ እንዲኖረው ያስቻለ ነበር። በዛሬውም ጨዋታ ይህ የሁለት አማካዮች ጥምረት ከኢትዮ ኤሌክትሪኩ የተከላካይ አማካይ ሔኖክ ካሳሁን ፊት የሚኖረው እንቅስቃሴ ለደደቢት እጅግ ወሳኝ ነው። በተቃራኒው በሲዳማ ጨዋታ ላይ ቡድኑ ወደ መከላከል በሚያደርገው ሽግግር ላይ የአማካይ ክፍሉ ደካማ እንቅስቃሴ ከረጅም ጊዜ በኃላ በሊጉ በአንድ ጨዋታ ሁለት ግቦችን እንዲያስተናግድ ምክንያት ሆኖታል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ይህን የተጋጣሚውን ክፍተት ለመጠቀም የሚያደርገው ጥረት ሌላው የጨዋታው ውሳኝ ኩነት እንደሚሆን ይጠበቃል። አልሀሳን ካሉሻ ፣ ዲዲዬ ለብሪ እና ኃይሌ እሸቱ ቡድናቸው ወደ ማጥቃት በሚሸጋገርበት ቅፅበት ከአማካይ ክፍላቸው የተመጠኑ ኳሶች ከደረሷቸው እንደ ሲዳማ ሁሉ የደደቢትን የተከላካይ መስመር አልፈው ግብ ለማስቆጠር የሚችሉባቸውን ዕድሎች ለማግኘት የሚያበቃ የግል ብቃት ያላቸው መሆኑ ለኢትዮ ኤላክትሪክ ተስፋ የሚሰጥ ይመስላል። ሆኖም ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዚህ ጨዋታ ላይ የተከላካይ መስመሩ ከስህተት የፀዳ እና በሁለቱ መስመሮችም ሆነ ከኄኖክ ጀርባ በሚኖረው ቦታ ላይ ለተጋጣሚው ክፍተት ላለመስጠት በእጅጉ መጠንቀቅ ይኖርበታል።