ጋብሬል አህመድ ለንግድ ባንክ ፈረመ

 

በዝውውር መስኮቱ መሪ ተዋናይ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋብሬል ‹‹ሻይቡ››አህመድን የግሉ አድርጓል፡፡ ተጫዋቹ ከደደቢት ጋር ያለው ውል ሰኔ 30 መጠናቀቁን ተከትሎ ከባንክ ጋር ለ2 አመት ለመጫወት የተስማማ ሲሆን ምን ያህል እንደሚከፈለው ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡

ከዝውውሩ በኋላ ተጫዋቹ ለባንክ በመፈረሙ ደስተኛ መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ገልጧል፡፡ ‹‹ በደደቢት ባሳለፍኳቸው 4 አመታት ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ምንም ችግርም አላጋጠመኝም፡፡ አሁን በአዲስ ክለብ አዲስ ፈተናን መጋፈጥ እፈልጋለሁ፡፡ በሰማያዊዎቹ ቤት ለነበሩኝ ጣፋጭ አመታት ደጋፊውን ፣ የክለቡን አመራሮች ፣ አሰልጣኞችን እና የቡድን ጓደኞቼን አመሰግናለሁ፡፡ ወደ ባንክ እንድመጣ በማሳመን ትልቁን ሚና የተጫወቱት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ናቸው፡፡ ›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

2

ከ4 አመታት በፊት በቱርካዊው አሰልጣኝ ሜህሜት ቱርክሜን አማኝነት ደደቢትን የተቀላቀለው ጋብሬል ባለፉት የውድድር አመታት ሳየው ድንቅ አቋም በሊጉ ከሚገኙ ምርጥ አማካዮች አንዱ አድርጎታል፡፡

ጋብሬል በአዲሱ ክለቡ ከቀድሞው የቡድ አጋሩ ፊሊፕ ዳውዚ ጋር ይገናኛል፡፡ ሁለቱ ተጫዋቾች በጋና 2ኛ ዲቪዥን ክለብ ውስጥ አብረው የተጫወቱ ሲሆን በደደቢት ለ6 ወራት አብረው ተጫውተዋል፡፡

 

ያጋሩ