አፍሪካ ውስጥ ስራቸውን የጀመሩት በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ ነው፡፡ በራዮን ስፖርት የአንድ አመት ቆይታ አድርገው ወደ ካሜሩን በማቅናት ከኮተን ስፖርት ጋር በሀገር ውስጥ እና በቻምፒየንስ ሊጉ መልካም ጉዞ አድርገዋል፡፡ ወደ አልጄርያ በመጓዝም ሲኤስ ኮንስታንቲን እና ስኪክዳን አሰልጥነው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለኢትዮጵያ ቡና የ2 አመታት ኮንትራት ፈርመዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ የ48 አመቱ ፈረንሳያዊ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስን በክለቡ የልምምድ ሜዳ ተገኝታ አናግራቸዋለች፡፡
በመጀመርያ ስለ ስራ ህይወትዎ በተለይም ስለ አፍሪካ ልምድዎ ያጫውቱን
አፍሪካ ውስጥ ስራ የጀመርኩት በሩዋንዳ ነው፡፡ ራዮን ስፖርት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በብዙ መንገድ ይመሳሰላል፡፡ በመንገድ ላይ እና በስታድየም ውስጥ በብዛታቸው እና በዝማሬያቸው የሚታወቁ ደጋፊዎች ያሉት ክለብ ነው፡፡ ቡድኑን ስረከብ በደረጃ ሰንጠረዡ ከመጨረሻው አንድ ደረጃ ብቻ ነበር ከፍ ብሎ የተቀመጠው፡፡ ዋንጫ ካነሳም 8 አመታት ተቆጥረው ነበር፡፡ ከዚህ ክለብ ጋር በሳምንት 12 የልምምድ ፕሮግራሞች ነበሩን፡፡ ከ6 ጨዋታዎች በኋላ ደረጃን መሻሻል ጀመረ፡ ጠንክረን በመስራት በዛው አመት ቻምፒዮን በመሆንም ደጋፊውን አስፈንድቀናል፡፡ በቀጣዩ አመት ባችፒየንስ ሊጉ ተሳታፊ የነበርን ቢሆንም ክለቡ የገንዘብ አቅሙ ደካማ በመሆኑ ደሞዜን በአግባቡ መክፈል ባለመቻላቸው ክለቡን ለቀቁሁ፡፡
በመቀጠል ያመራሁት ወደ ካሜሩኑ ኮተን ስፖርት ነበር፡፡ በወቅቱ ከአፍሪካ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ታላቅ ክለብ ነበር፡፡ በሁለት ተከታታይ አመታት ቻምፒዮን መሆን ስንችል የጥሎ ማለፉን ዋንጫ አንስተናል፡፡ በቻምፒዮንስ ሊጉም ግማሽ ፍፃሜ መግባት ችለናል፡፡ ኮተን በግሌ ብዙ የተማርኩበት ክለብ ነው፡፡ ምክንያቱም ከአሰልጣኝነት ባሻገር የክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ የክለብ ማኔጅመንት እና አሰልጣኝነት ላይ ያካበትኩት ልምድም ወደ አልጄርያ እንዳመራ ረድቶኛል፡፡
ወደ አልጄርያ የሄድኩት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ አልጄርያ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ሃገራት የተሸለ የስፖርት መሰረተ ልማት ካለባቸው መካከል ነች፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ከአልጄርያ የአንድ ሰአት በረራ ብቻ ርቀት ባላት ማርሴይ ከተማ የምትኖረው ልጄን በቅርበት የማግኘት እድል ስለሚኖረኝ ነው፡፡ ነገር ግን በአልጄርያ ስራው ቀላል አልነበረም፡፡ በሲኤስ ኮንስተንቲን የመጀመርያ የውድድር ዘመኔ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ቡድን በሊጉ 3ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ረድቸዋለሁ፡፡ ክለቡን ቻምፒዮን ማድረግ ባልችልም በማራኪ እንቅስቃሴው የሚታወቅ ቡድን መገንባት ችለን ነበር፡፡ ከዛም ወደ ምስራቅ አፍሪካ ተመልሼ ለመስራት አስብኩ፡፡ በኬንያ ፣ ታንዛንያ እና ሩዋንዳ እንዲሁም በዛው በአልጄርያ የሚገኙ ክለቦች ጥያቄ ቢደርሰኝም ከድሮ ጀምሮም በታሪክ ወደማውቃት ኢትዮጵያ መጥቻለሁ፡፡ ሩዋንዳ የአፍሪካ ስራዬን የጀመርኩበት በመሆኑ ጥሩ ስሜት ቢኖረኝም ኢትዮጵያን መርጬ ነው የመጣሁት፡፡ በፊትም ቢሆን በፈረንሳይ እያለሁ ለቤተሰቦቼ አንድ ቀን ኢትዮጵያ መጥቼ እንደማሰለጥን እነግራቸው ነበር፡፡ በእርግጥ አሁን ከቤተሰቦቼ ርቄ ነው የምኖረው፡፡ ቡና ብዙ ደጋፊ ያለው ትልቅ ክለብ ነው፡፡ እኔም ይህን ክለብ ለማሰልጠን በመታደሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ቡናን መርጬ በመምጣቴ እንደ አሰልጣኝም እንደ ግለሰብም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
በፈረንሳይ ካንን አሰልጥነዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የተሸለ የእግርኳስ ደረጃ ባላቸው ካሜሩን እና አልጄርያም አሰልጥነዋል፡፡ አሁንም ሌላ የአሰልጥንልን ጥያቄዎች ቢመጣልዎትም ኢትዮጵያ ቡናን መምረጥዎን ገልፀዋል፡፡ ታድያ ወደ ኢትዮጵያ ቡና መምጣትን ለምን መረጡ? ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ ያለዎት መረጃስ ምን ያህል ነው?
ስለ ኢትዮጵያ አግርኳስ አውቅ ነበር፡፡ ከኮተን ስፖርት ጋር በቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ወደ ሌሎች ሀገሮች ስንጓዝም ቢሆን ሁለት ሶስት ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ትራንዚት አድርገናል፡፡ አሸናፊ ግርማ የነበረበት ብሔራዊ ቡድንን በቴሌቪዥን የመመልከት እድል ባገኘሁባቸው ጨዋታዎች በሚገባ እከታተል ነበር፡፡ አሸናፊ ግርማ አስገራሚ አማካይ ነበር፡፡ ያን ጊዜ የነበረው ብሔራዊ ቡድንም ደረጃው ከፍ ያለው ነበር፡፡ በኃይማኖት ፣ ፖለቲካ እና የሰው ልጆት ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ ትልቅ ስፍራ ያላት ሀገር መሆኗን ስለማውቅ ለዛ ነው በኢትዮጵያ መስራትን የመረጥኩት፡፡ ዳሎል እና የዓባይን መነሻ ለማየት ጓጉቻለሁ፡፡ የሰሜን ተራሮችን ፈረንሳይ እያለው በምስል ተመልክቻለሁ፡፡ እዛም መሄድ እፈልጋለሁ፡፡ የሚደነቅ እና የትም የሌለ ቡና አላችሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከማውቃትም በላይ ድንቅ ውበት እና ትልቅ ሀገር ናት፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ አንድ ሳምንት ሊሆንዎት ነው፡፡ ፊርማዎን ያስቀመጡት ዛሬ (አርብ) ቢሆንም ጥቂት ቀናትን አሰልጥነዋል፡፡ በጅማ ተገኝተውም ጨዋታውን ተመልክተዋል፡፡ ቡናን እንዴት አገኙት?
በጅማ ከተማ ተገኝቼ ጨዋታውን ተመልክቻለሁ፡፡ የራሴን ምልከታ እና ማስታወሻም ይዣለሁ፡፡ በእርግጥ በቡድኑ ውስጥ ከበጎው ይልቅ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ደካማ ጎኖች ይበዛሉ፡፡ በተለይ ታክቲክን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ብዙ ይቀረናል፡፡ ነገር ግን በርካታ በግላቸው ጥሩ የቴክኒክ ችሎታን የያዙ ተጫዋቾች አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ በታክቲኩ ረገድ ብዙ ልንሰራ ይገባል፡፡ እኔም ያለኝን ለመስጠት እና የምችለውን ለማድረግ ነው እዚህ የተገኘሁት፡፡ ደጋፊው ብዙ ነገር ይጠብቅብናል፡፡ ስለዚህ ቀን ከሌሊት መስራት አለብን፡፡ ለተጫዋቾቼ የነገርኳቸውም ይህንን ነበር፡፡
አሁን የመጡበት ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና በጥሩ ሁኔታ ላይ በማይገኝበት ወቅት ነው፡፡ ደጋፊውም በቡድኑ ያዘነበት ሰአት ላይ ነው የተገኙት፡፡ ስለዚህ ወቅታዊ እና የወደፊት እቅድዎ ምንድን ነው በኮንትራታችሁ ላይስ የተነጋገራችሁት ቅድመ ሁኔታ ምንድነው?
አሁን መረጋጋት እፈልጋለሁ፡፡ ጊዜ እንፈልጋለን፡፡ ክለቡ እየታየ ሊታደስ የሚችል የሁለት አመት ኮንትራት ነው የሰጠኝ፡፡ አላማችን ዋንጫ ማንሳት ነው፡፡ በቡና ከዋንጫ ውጪ ምንም ሊታሰብ አይችልም፡፡ ይህን ሁላችሁም እንደምታውቁት ግዴታ ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ብዙ ነጥቦች ጥለናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ነጥብ መጣል አይፈቀድልንም፡፡ ብዙ ነጥብ መሰብሰብ ይኖርብናል፡፡ ቀላል ባይሆንም ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ አለብን፡፡
ኮተን ስፖርት እያለሁ ተጫዋቾችን ለአውሮፓ ክለቦች የሚሸጡ የታዳጊ ማዕከላት ነበሩን፡፡ ብዙ ወጣቶችንም ወደ ዋናው ቡድን ማሳደግ ችለናል፡፡ እዚህም የቡና ከ17 እና ከ20 አመት በታች ቡድኖችን መከታተል እፈልጋለሁ፡፡ ያሰብኩት ነገር ሁሉ እንዳቀድኩት ከሄደ ከታዳጊ እና ወጣ ቡድኑ ጋር በጋራ መስራት እፈልጋለሁ፡፡ የክለቡ እቅዶች ላይ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ደጋፊው እምነቱን ካሳደረብን እና እጅ ለእጅ ከሰራን ብዙ ነገር ማድረግ እንችላለን፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ከውጤት ባሻገር ቀድሞ ይታወቅበት የነበረው እንቅስቃሴ እንዲመለስ ይፈልጋል፡፡ እርስዎስ ምን አይነት ዘይቤ ነው ይዘው የመጡት?
እኔም እንደቡና ደጋፊዎች በአስቀያሚ እንቅስቃሴ ከማሸነፍ በምርጥ ጨዋታ መሸነፍን እመርጣለሁ፡፡ በሩዋንዳ እያለው ራዮን ስፖርት ‹‹የሩዋንዳው ባርሴሎና›› እስከባል ደርሶ ነበር፡፡ በካሜሩንም ይህን ለማድረግ ከባድ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የነበርኩበት ክለብ ፍላጎታቸው ይህ ነበር፡፡ በእርግጥ ሜዳው እዚህ ካለውም የባሰ አስቸጋሪ ቢሆንም ለውብ ጨዋታ የሚያመቹ ተጫዋቾችን በመያዛችን መልካም እግርኳስን እንጫወት ነበር፡፡ ግብ ከማስቆጠራችን በፊት በብዙ ቅብብሎች ነበር ወደ ግብ የምንደርሰው፡፡ በኳስ ቁጥጥር እና ውብ እንቅስቃሴ አምናለሁ፡፡ ለተጫዋቾቼም የነገርኳቸው ይህንኑ ነው፡፡ ብዙ የኳስ ቅብብሎችን በማድረግ የተቃራኒ የግብ ክልል ላይ ጫና በማሳደር አምናለሁ፡፡
እርስዎ ለሚፈልጉት አቀራረብ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ቡድኔ ይዟል ብለው ያምናሉ?
አዎን ይመስለኛል፡፡ በዕርግጥ ዋናው ነገር ተጫዋቾቹ ብቻ ሳይሆኑ ፍልስፍናው ነው፡፡ በተጫዋቾ አዕምሮ ውስጥ የምታስቀምጠው አስተሳሰብ ነው፡፡ ኤልያስ ለምሳሌ ለዚህ አጨዋወት የተፈጠረ ተጫዋች ነው፡፡ ሆኖም ኳስን እግሩ ስር ብዙ ይዞ ይቆያል፡፡ ይህንን እንዲያስተካክል ነግሬዋለሁ፡፡ እሱ ብዙ ነገር ይረዳናል፡፡ እንደ ቡድን ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ብዙ የግል ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ቡድን ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ እውነት ለመናገር ተጫዋቾቹ ያላቸው አሁን ያላቸው ተነሳሽነት ጨምሯል፡፡
የመጡት በአዲስ አመት ዋዜማ ነው፡፡ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም አቅደዋል?
አዎን፡፡ ነገር ግን ትንሽ ክለቡን ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ያለውን ክፍተት በሚገባ ማጥናት እፈልጋለሁ፡፡ ላሉት ተጫዋቾች ዕድሉን መስጠት አለብኝ፡፡ በክለቡ ያለውን አቅምም በሚገባ መገምገም ይጠበቅብኛል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ተጫዋቾች በአሰልጣኝ መቀያየር ምክንያት ተዳክመው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ዕድሉን ሰጥተን እናያለን፡፡ የክለቡ ፕሬዝዳንትም ለዚህ ፍቃዳቸውን ሰጥተውኛል፡፡ ሁኔታዎችን በደንብ ካጠናን በኋላ በዕውነትም ክለቡን የሚያጠናክሩ ተጫዋቾችን ክፍተት ባሉብን ቦታዎች ላይ ብቻ እናስፈርማለን፡፡
የቋንቋ ችግር በክለቡ አልገጠመዋትም?
እስካሁን አላጋጠመኝም፡፡ ምክንያቱም አምበሉ (መስዑድ) በጣም ጥሩ እንግሊዝና ይናገራል፡፡ እኔም ሩዋንዳ ስለሰራሁ እንግሊዝኛን ተምሬያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ እዚህ ለስራ የሚጠቅመኝን ያህል አማርኛ ለመማር አስቤያለሁ፡፡ እስካሁን ያለው ነገር ጥሩ ነው፡፡ ምንም ችግር የለም፡፡
ከእርስዎ በፊት የነበሩት አሰልጣኝ ክለቡን በፈቃዳቸው ነው ጥለው የሔዱት፡፡ ደጋፊዎችም አሁን አርስዎ ስለመቆየትዎ ጥርጣሬ እንደገባቸው ይታያል፡፡ ስለ እርስዎ ምን ማረጋገጫ መስጠት ይቻላል?
ትላንት ማታ ለምሳሌ በስልክ የአሰልጥንልን ጥያቄ ነበረኝ፡፡ ለቡና የፈረምኩት ዛሬ (አርብ) ነው፡፡ ለቡና አልፈረምኩም ፣ ቆይ ላጢነው ማለት እችል ነበር፡፡ ነገር ግን ለማውራት እንኳ ፈቃደኛ ሳልሆን ነው ስልኩን የዘጋሁት፡፡ በቡና ራሴን መፈተን እፈልጋለሁ፡፡ መረጋጋት እፈልጋለሁ፡፡ ቡና የፈረምኩት ከመሰረቱ እንዳዲስ ክለቡን ለማዋቀር ስለምፈልግ ነው፡፡ በቡና ማሳካት የምፈልገው ብዙ ነገር አለ፡፡
ከቡና ቤተሰብ ጋር ዋንጫ ማግኘት እና ደስተኛ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ከቡና ጋር መነጋገር የጀመርነው አሁን አይደለም ፣ ለወራት አስቤበት ተዘጋጅቼ ነው የመጣሁት፡፡ ቡና የፈለገኝ አሁን አይደለም፡፡ ለወራት አስቤበት ተዘጋጅቼ ነው የመጣሁት፡፡ ኮንትራቴን ማክበር እፈልጋለሁ፡፡ እስከ ውሌ መጨረሻ እቆያለሁ፡፡