የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ዛሬም በ3 ጨዋታዎች ቀጥለው ሲካሄዱ አዲግራት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያደረጉት ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ባለሜዳው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ7ኛው ሳምንት በመከላከያ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ውስጥ በዘውዱ መስፍን ፣ ተስፋዬ ዲባባ እና እንየው ካሳሁን ምትክ በረከት አማረ ፣ ኤፍሬም ጌታቸው እና ብርሃኑ አሻሞን ወደ መጀመርያ አሰላለፉ በማካተት በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገባ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንጻሩ አርባምንጭ ከተማን 3-0 ከረታው ስብስብ ምንተስኖት አዳነን በአዳነ ግርማ ተክቶ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በማካተት በተመሳሳይ 4-3-3 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምሯል፡፡
ፈጠን ባለ የጨዋታ እንቅስቃሴ በተጀመረው ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በማጥቃት እንቅስቃሴ እና የግብ አድሎች በመፍጠር በእንግዶቹ ላይ የበላይ መሆን ችለው ነበር፡፡ በ13ኛው ደቂቃ ፕሪንስ በግምት ከ18 ሜትር ወደ ግብ የመታውና ሮበርት በቀላሉ በተቆጣጠረው ሙከራ የመጀመርያ የጎል እድል የፈጠሩት ወልዋሎዎች በመስመር አጥቂዎቻቸው በተለይ በፕሪንስ ሰቨሪንሆ በኩል በተደጋጋሚ ወደ ማጥቃት ወረዳው መድረስ የቻሉ ሲሆን በ27ኛው ደቂቃ በድጋሚ ፕሪንስ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ መትቶ ሮበርት ያመከናት እንዲሁም በ33ኛው ደቂቃ ከቀኝ ማዕዘን ምት ለኤፍሬም አቀብሎት ተከላከዩ ኤፍሬም አክርሮ መትቶ በግቡ ቋሚ የወጣበት ኳስ ወልዋሎ በቀኝ መስመር ያጋደለ የማጥቃት ጫና ማሳያዎች ነበሩ፡፡
ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮች በረጅሙ በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች የወልዋሎን የተከላካይ መስመር ለመስበር የሞከሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንጻሩ ለግብ የቀረበ ሙከራ በመጀመርያው አጋማሽ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በ14ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ከመስመር ወደ ግማሽ ጨረቃው ያጠፈውን ኳስ ሙሉአለም ሞክሮ በረከት የያዘበት ሙከራም ብቸኛው የሚጠቀስ ሙከራ ነበር፡፡
የመጀመርያ አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ወልዋሎዎች ጨዋታውን አሸንፈው ሊወጡባቸው የሚችሏቸው ሁለት መልካም አጋጣሚዎች ማግኘት ችለው ነበር፡፡ በ41ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው አፈወርቅ ኃይሉ በግምት ከ25 ሜትር የቀኙ የሜዳ ክፍል በግራ እግሩ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን የላይኛው ቋሚ ለትሞ ሲመለስ ከድር ሳሊህ ግብ ሊያስቆጥርበት የሚችልበት ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረ ቢሆንም ወደ አናት የሰደዳት እንዲሁም በ45ኛው ደቂቃ ሙሉአለም በቀኝ መስመር ተከላካዮችን አምልጦ በመውጣት ለከድር ያሻገረውን ኳስ የመስመር አጥቂው ሳጠቀምበት ቀርቷል፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አዳነ ግርማ በጋዲሳ መብራቴ በተደረገ ቅያሪ የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመርያው አንጻር የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት እና ሁለቱም ቡድኖች ለማጥቃት ረጃጅም ኳሶችን የመረጡበት ነበር፡፡ በመጀመርያው ደቂቃ በወልዋሎ የግብ ክልል በአልሳሪ እና ግብ ጠባቂው በረከት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ፣ ከሮቤል በ3 አጋጣሚዎች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል የተላኩ እና ወደ አስደንጋጭ የግብ ሙከራነት ያልተለወጡ ኳሶች እንዲሁም ከአበባው ቡታቆ የተሸማውና በበረከት የተያዘው ቅጣት ምት በሙሉ መነሻቸው ከረጅም ርቅት በሚሻገሩ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ፡፡
ወልዋሎ በዚህኛው የጨዋታ አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ከተጋጣሚው መውሰድ ቢችልም የጠራ የግብ እድል መፍጠር የቻለው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡ በ61ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ተከላካዩ አሳሪ አልመሀዲ በጥሩ የፊት ለፊት ሩጫ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ተጠግቶ ለሙሉአለም ያሻገረለትን ኳስ አጥቂውን ግብ የማስቆጠር ወርቃማ አጋጣሚ ቢፈጥርለትም ኳሷን ሙሉ ለሙሉ ሳያገኛት በሚያስቆጭ መልኩ አምክኗታል፡፡
ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ12 ነጥቦች በነበረበት 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቆይ ወልዋሎ በ11 ነጥቦች ሁለት ደረጃዎችን በማሻሻል 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡