ብሄራዊ ሊግ 2ኛ ቀን ፡ ዛሬ 5 ጨዋታዎች ተደርገዋል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ትላንት በይፋ ተጀምሯል፡፡ ትላንት በተደረገው ብቸኛ ጨዋታም የአስተናጋጇ ከተማ ክለብ የሆነው ድሬዳዋ ከነማ አርሲ ነገሌን 2-0 በማሸነፍ ውድድሩን በድል ከፍቷል፡፡ ከ2001 እስከ 2004 በፕረሚር ሊጉ ለተሳተፈው ድሬዳዋ ከነማ ክብሮም ሃጎስ እና ከድር ናስር የድል ግቦቹን ከመረብ አሳርፈዋል፡፡
በዚሁ ምድብ የሚገኙት ክለቦች ዛሬ ጨዋታቸውን አድርገዋል፡፡ በ8፡00 ወልዋሎን የገጠመው ፋሲል ከነማ 2-0 በማሸነፍ ከድሬዳዋ ከነማ እኩል የምድቡን አናት ተቆናጧል፡፡ የአፄዎቹን ሁለቱንም የድል ግብ የቀድሞው የዳሽን ቢራ የመስመር አማካይ ጅላሎ ሻፊ ከመረብ አሳርፏል፡፡ የወልዋሎው አምበል ተጫዋችን በግንባሩ በመግጨት በእለቱ አርቢቴር በቀይ ካርድ የተወገደ ሲሆን በዳኛው ውሳኔ ምክንያት መጠነኛ አለመግባባት ተፈጥሮ ጨዋታው ለጥቂት ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር፡፡ 10፡00 ላይ የተደረገው የቡራዩ ከነማ እና ፌዴራል ፖሊስ (ኦሜድላ) ጨዋታ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ይህንን ምድብ ድሬዳዋ ከነማ እና ፋሲል ከነማ በእኩል 3 ነጠብ እና የግብ ልዩነት ምድቡን መምራት ጀምረዋል፡፡
በምድብ 3 የሚገኙ ክለቦች በሙሉ ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ ጨዋታቸውን አድርገዋል፡፡ በ4፡00 በተደረገው ጨዋታ መቐለ ከነማ ከ ሼር ኢትዮጵያ ያደረጉት ጨዋታ ካለግብ ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው በግብ ባይታጀብም በሜዳው የተገኘውን ተመልካች ያስደሰተ ፍልሚያ አድርገዋል፡፡
በ8፡00 ሃላባ ከነማ ሰበታ ከነማን 1-0 በማሸነፍ የምድብ ጨዋታውን በድል ከፍቷል፡፡ የሃላባን የድል ግብ ተመስገን ይልማ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ይህንን ጨዋታ ተከትሎ በተጀመረው ጨዋታ በብሄራዊ ሊጉ ከፍተኛው የግብ መጠን ተመዝግቧል፡፡ ጅማ ከነማ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲን 3-2 ባሸነፈበት ጨዋታ የቀድሞው የዳሽን ቢራ ፣ አዳማ ከነማ እና ሐረር ቢራ አጥቂ አሸናፊ ይታየው 2 ግቦችን ለጅማ ከነማ አስቆጥሯል፡፡ የጅማን ቀሪ ግብ ታሪኩ ታምራት ሲያስቆጥር የደብረማርቆስን ግቦች ፍቃዱ አለሙ እና አቤል ግርማ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡
ይህንን ምድብ ሃላባ ከነማ እና ጅማ ከነማ 3 ነጥብ አንድ የግብ ልዩነት ይዘው ምድቡን መምራት ጀምረዋል፡፡
ውድድሩ ነገ የሚቀጥል ሲሆን የምድብ 2 እና 4 ክለቦች ከጥዋት 3፡00 ጀምሮ 6 ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡
ዳንኤል መስፍን (ድሬዳዋ)

ያጋሩ