በሁለተኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ላይ መደረግ ሲኖርበት በይለፍ ተይዞ የቆየው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ዛሬ 11፡30 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ተደርጎ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-1 አሸናፊነት ተደምድሟል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ወልድያን 2-0 መርታት የቻለው ኢትዮጵያ ቡና በዛሬው ጨዋታ በረከት ይስሀቅን በእያሱ ታምሩ በመተካት ብቻ የቅርፅ ለውጥ ሳያደርግ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ በመጀመሪያው ጨዋታቸው በተጠቀሙበት የ4-3-3 አሰላለፍ ቀርቧል። በዚህ ረገድ ተለይቶ የታየው የአስቻለው ግርማ በፊት አጥቂነት መሰለፍ ሲሆን በመጨረሻ አጥቂነታቸው የሚታወቁት ማናዬ ፋንቱ እና አቡበከር ነስሩ በተጠባባቂነት መያዛቸው ለውጡ ከአማራጭ እጦት የመጣ እንዳልሆነ አመላክቷል። በ7ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር በደደቢት የ3 -1 ሽንፈት የገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተጨዋች ምርጫው ላይም ሆነ ቡድኑ በተጠቀመበት የ 4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፍ ላይ ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ገብቷል። አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩን በሳምንቱ መጀመሪያ ያሰናበታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሙሉ ጨዋታውን በግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ቅጣው ሙሉ አማካይነት ነበር የተመራው።
በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ የተፋዘዘ እንቅስቃሴ የተስተናገደበት ነበር። ቡድኖቹ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመግባት የቻሉ ቢሆንም ያየናቸው የግብ ሙከራዎች ከሦስት መብለጥ አልቻሉም። ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኃላ ወደዚህ ጨዋታ የመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ምንም እንኳን በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም የተጋጣሚያቸው አጨዋወት ፍሪያማ እንዳይሆን በማድረግ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ግብ ማስቆጠር አልተሳናቸውም። በቻሉት አጋጣሚ የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሀል ሜዳው አስጠግተው የተጫወቱት ኤሌክትሪኮች የኳስ ቁጥጥር ቢወሰድባቸውም ተጋጣሚያቸውን በራሱ ሜዳ ላይ በማስጨነቅ እና ኳሶችን በማበላሸት ረገድም ሆነ ኳስ በግብ ክልላቸው ስትገኝ ክፍተትን ባለመስጠቱ በኩል ተሳክቶላቸዋል። አብዛኛው የማጥቃት መስመራቸው ዲዲዬ ለብሪ አመዝኖ ወደሚጫወትበት የግራ መስመር አመዝኖ በቆየባቸው ደቂቃዎች ኤሌክትሪኮች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የነበራቸው አስፈሪነት እምብዛም ነበር። በዚህም 15ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም አሰፋ ከሔኖክ ካሳሁን ከተቀበላትን ኳስ የሞከረው ቀላል ሙከራ ሌላ ዕድል አልፈጠሩም። ሆኖም 35ኛው ደቂቃ በኃላ ዲዲዬ ለብሪ የማጥቃት አቅጣጫ ወደ ቀን ከዞረ በኃላ ክፍተት ሲታይበት የነበረውን የኢትዮጵያ ቡና የግራ የተከላካይ ክፍል ለመጠቀም ሁለት ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈለጉት። በዚህም 37ኛው ደቂቃ ላይ ክልሉሻ አልሀሰን ከጥላሁን ወልዴ በግሩም ሁኔታ ያለፈለትን ኩስ በመጠቀም በኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች መሀል በማለፍ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። ይህች የ ካሉሻ ጎል ኢትዮ ኤሌክትሪኮችን በጣሙን ያነቃቃች ስትሆን ከወልድያው ጨዋታ በተለየ በድናቸውን በድምቀት ሲያበረታቱ የነበሩትን የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን ወደተቃውሞ የመራች ነበረች። ከዚህ ደቂቃ ጀምሮ በእረፍት እና በሁለተኛው አጋማሽ ጭምር የቀጠለው የደጋፊዎቹ ተቃዎሞ ሙሉ ለሙሉ በክለቡ አመራሮች ላይ ያነጣጠረ ነበር። 25ኛው ደቂቃ ላይ አስናቀ ሞገስ ከግራ መስመር ያሳለፈው እና አስቻለው ሳይደርስበት የቀረው ኳስ ኢትዮጵያ ቡናዎች ለግብ የቀረቡበት ብቸኛ አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል። በግራ መስመር አጥቂነት የሚታወቀው አስቻለው ግርማ ከትሰለፈበት የፊት አጥቂነት ሚና እያሱ ታምሩ ወደተሰለፈበት የግራው የቡና የማጥቃት መስመር አድልቶ እና ኤልያስ ማሞም ተጨምሮበት አብዛኛው የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ በሶስቱ ተጨዋቾች መሪነት የሚካሄድ ነበር። ሆኖም በዚህ መንገድ በቂ የመቀባበያ ክፍተትን መፍጠር ባለመቻሉ እና ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በሜዳው ስፋት እስከ ቀኝ መስመር አጥቂው አስራት ቱንጆ ድረስ የኤሌክትሪክን ተከላካይ መስመር መለጠጥ ባለመቻሉ ቡድኑ የሚያጠቃበት መንገድ ለአዋቾቹ የግራ መስመር የተጠጋጋ ማጥቃት ሲቋረጥ በቶሎ ኃላቸውን መሸፈን ሳይችሉ የቡናን የግራ መስመር መከላከል ክፍተት እንዲኖርበት መንስኤ ሆኗል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር በኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኩል የጎላ ለውጥ ባይታይም አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ አስቻለው ግርማን በአቡበከር ነስሩ የቀየሩ ሲሆን መስዑድ መሀመድን ከነበረበት የተከላካይ አማካይነት ሚና በመቀየር ከኤልያስ ጋር የማጥቃት ሂደቱ ላይ እንዲሳተፍ በማድረግ አክሊሉ ዋለልኝን ወደኃላ የመለሱበት አኳኃን በቡናማዎቹ በኩል ተጠቃሽ ነበር። በእንቅስቃሴም ህምነ በሙከራ ረገድም ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ሆኗል። አሁንም ኳስ መስርቶ በመግባት ክፍተቶችን ለማግኘት ሲሞክር በነበረው ኢትዮጵያ ቡና በኩል ኤልያስ ማሞ በኤሌክትሪክ የግራ መስመር የመከላከል ክፍል በተስፋዬ እና ዘካሪያስ መሀል እየገባ ተከላካይ መስመሩን ወደመሀል እንዲሰበስበብ የሚያደርግበት እንቅስቃሴ ተደጋግሞ ይታይ ነበር። ከዚህ እንቅስቃሴ መነሻነትም የቀኝ መስመር አጥቂው አስራት ቱንጆ ነፃ ሆኖ ይታይ የነበረ ሲሆን 54ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ አኳኃን ከሳጥን ውስጥ ግልፅ የሚባል ዕድል አግኝቶ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። ውጤት የማስጠበቅ ሀሳብ ያልታየባቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከቀደመው በበለጠ የተከላካይ መስመራቸውን እስከ መሀል ሜዳ አስጠግተው በተለይ ከኢትዮጵያ ቡና አማካዮች የቅብብል ስህተቶች መነሻነት የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ጥቃት በመቀየር ሙከራዎችን የሚያደርጉበት መንገድ ቀጥሎ ታይቷል። 52ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ተሻገር ከርቀት ሞክሮ ወደውጩ የወጣበት እንዲሁም 58ኛው ደቂቃ ላይ ካሉሻ አልሀሰን መሀል ለመሀል ኳስ ይዞ በመግባት እና የቡናን ተከላካዮች ወደራሱ ስቦ በግራው የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ይገኝ ለነበረው ጥላሁን ያሳለፈለትን ጥላሁን ሞክሮ የሳተበት አጋጣሚዎች ቡድኑ ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ላይ እንደነበር ምስክሮች ነበሩ። ከዚህ እንቅስቃሴ የማዕዘን ምት ያገኙት ኤሌክትሪኮች በፈጠሩት ጫናም 59ኛው ደቂቃ ላይ አወት ገ/ሚካኤል ያሻማውን ኳስ በመጠቀም መሀል ተከላካዩ ግርማ በቀለ ባስቆጠረው ኳስ መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሻግረዋል። ከደቂቃዎች በኃላም ዲዲዬ ለብሪ ጥላሁን ወደ መሀል ተጠግቶ በነበረው የቡና የተከላካይ ክፍል መሀል የላከለትን ኳስ በተሳሳተ የመጀመራ ንክኪው ምክንያት መጠቀም ሳይችል ቀረ እንጂ የቡድኑ መሪነት ወደ ሶስትም ከፍ ሊል ተቃርቦ ነበር። ከወትሮው በተለየ አቋሙ ጥሩ ያልነበረው ዲዲዬ ለብሪ 87ኛው ደቂቃ ላይም ከአስናቀ ሞገስ የተሳሳታ ቅብብል ከሀሪሰን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል። ከዚህ በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በተመሳሳይ አኳኃን ለማጥቃት ቢጥሩም 70ኛው ደቂቃ ላይ ትዕግስቱ አበራ እንዲሁም 71ኛው ደቂቃ ላይ አስናቀ ሞገስ አሻምተዋቸው ሱሊማና አቡ ከያዛቸው ኳሶች ውጪ ዕድሎችን አልፈጠሩም። ሆኖም የ73ኛው ደቂቃ የሚኪያስ መኮንን በመሀል ተከላካዩ ኤፍሬም ወንደሰን መቀየር ተከትሎ ቅርፃቸውን ወደ 3-4-3 የቀየሩት ቡናዎች በዚሁ ደቂቃ በእያሱ ታምሩ አማክልይነት ጎል ማግኘት ቻሉ። እያሱ በረጅም ወደ ኤሌክትሪኮች የግብ ክልል የተጣለውን ኳስ ተከላካዮች በሚገባ ሳያርቁት ሲቀሩ አግኝቶ በቀጥታ በመታት ነበር ያስቆጠረው። ከግቧ በኃላ በነበሩት 15 ደቂቃዎች የቡንምዎች ጫና እጅግ የበረታ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ያላፈገፈጉት ኤሌክትሪኮችም በዲዲዬ ለብሪ እና ካሉሻ አልሀሰን አማካይነት ሙከራዎችን ማድረጋቸው አልቀረም። በተቃራኒው 80ኛው ደቂቃ ላይ በአቡ የተመለሰችን የኤልያስ ማሞ የቅጣት ምት ከግቡ አፋፍ ላይ የነበሩ ሶስት ተጨዋቼች ሳይጠቀሙበት የቀሩት ፣ 82ኛው ደቂቃ ላይ ከመስዑድ የማዕዘን ምት ትዕግስቱ በግንባሩ ሞክሮ አቡ በቅልጥፍና ያዳነበት እና 90ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ከአበበከር ተቀብሎ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ የሳተበት ሶስት አጋጣሚዎች ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊፈፀም የቀረበባቸው የኢትዮጵያ ቡና ከባድ ሙከራዎች ነበሩ። ሆኖም በጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት በተጨዋቼች የግል ብቃት እና እንደ ቡድንም የነበራቸው ተነሳሽነት እጅግ ከፍ ብሎ የታዩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በደጋፊ ተቃውሞ በታጀቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ላይ የ2-1 ድል በማስመዝገብ ጨታውዋ ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
” ለረጅም ጊዜ በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ቆይቻለው። ዛሬ ደግሞ ይሄንን ቡድን ራሴ መርቼ በማሸነፌ ከልብ ተደስቻለው። ብልጫ ወስዶ የተጫወተ ቡድን ያሸንፋል። ዘጠና ደቂቃ በትኩረት ተጫውተን ካገኘናቸው እድሎች ግቦች አስቆጥረን ማሸነፍ ችለናል። ተጨዋቾቹም ካጋጠማቸው የሶስት ጊዜ ሽንፈት በኃላ በእልህ ተጫውተው ውጤት ይዘው ወተዋል። በቀጣይ ያሉንን ልጆች በዐዕምሮው ረገድ አዘጋጅተን በሌሎች ጨዋታዎችም እንዲሁ በሞራል ተነሳስተው ወደ ውጤት ይመጣሉ ብዬ አስባለው። የመውረድ ስጋት የለብንም”
አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና
” እጅግ በጣም አዝኛለው። ምክንያቱም የመጀመሪያው አጋማሽ በሚገባ ሳንፋለም አልፎናል። ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የነበረ ቢሆንም በመጀመሪያው አጋማሽ መጥፎ ነበርን። የመጣውት ባሳለፍነው ሳምንት ነው። ብዙ መስራት እና ብዙ ነገሮችን ማሻሻል ይጠበቅብናል። ፍልስፍናዬን ለማስረፅም ጊዜ ያስፈልገኛል። ቢሆንም የዛሬውን ጨዋታ ወደ ሁለተኛነት ከፍ ለማለት ማሸነፍ እጅግ ወሳኝ ነበር። እረፍት በጣም ተናድጄ ነበር በመልበሻ ክፍልም ተጨዋቾቼ ለደጋፊው ሲሉ እንዲፋለሙ ነግሪያቸው ነበር። በርግጥም አድረገውታል ግን በቂ አልነበረም። ለደጋፊዎቻችንም ይቅርታ መጠየቅ ፈልጋለው። “