ዛሬ በተደረገው የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) ፍፃሜ ደደቢት ቅዱስ ጊዮርጊስን 2-1 አሸንፎ የ2006 አም. የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ከጨዋታው ቀደም ብሎ ደደቢት የአፍሪካ ተሳትፎውን በማረጋገጡ እንዲሁም የፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቻምፒዮንስ ሊጉ እነደሚሳተፍ በማረጋገጡ ጨዋታው ያን ያህል ትኩረት አልሳበም፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስላል የስታድየሙ ግማሽ ክፍል ባዶ ሆኖ ታይቷል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንያህል ተሾመ ፣ ሮበርት ኦዶንግካራ ፣ አዳነ ግርማ ፣ ሳላዲን በርጊቾ ፣ ኡመድ ኡኩሪን እና ፍፁም ገብረማርያምን ጨምሮ ዋና አሰልጣኙን ሳይዝ ደደቢትን የገጠመ ሲሆን ሰማያዊ ጦረኞችም ሻይቡ ጋብሬል ፣ ስዩም ተስፋዬ ፣ አክሊሉ አየነው እና ሲሳይ ባንጫን ሳይዙ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በጨዋታው ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሲሆኑ የደደቢት ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ናይጄርያዊው ሳመሙኤል ሳኑሚ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ ጨዋታው እምብዛም ሳቢ ያልነበረ ቢሆንም የደደቢት አጥቂዎች በመልሶ ማጥቃት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ሲቀሩትም የመስመር አጥቂው ሽመክት ጉግሳ ደደቢትን አቻ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደፊት ተጠግቶ ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርግ ደደቢቶች በበኩላቸው በፈጣን የመልሰ ማጥቃት የፈረሰኞቹን ተከላካዮች ሲያስቸግሩ አምሽተዋል፡፡ በ72 ኛው ደቂቃ ዳዊት ፍቃዱ በመልሶ ማጥቃት ያስቆጠራት ግብም ደደቢትን ወደ መሪነት አምጥቷቸዋል፡፡ ዳዊት ግቧን ካስቆጠረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ተመሳሳይ አጋጣሚ ቢያገኝም አምክኗል፡፡

ጨዋታው ከግብ ሙከራዎች ይልቅ በሽኩቻዎች እና በአደገኛ ጥፋቶች የታጀበ ሲሆን እንደ ጨዋታው ዳኛ ትእግስት ባይሆን ነጆሮ በርካታ ካርዶች ይመዘዙ ነበር፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የደደቢት ተጫዋቾቸእ በኢትዮጵያ እግርኳስ ባልተለመደ መልኩ ማልያቸውን ለደጋፊ በመወርወር ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

ደደቢት ከዚህ ቀደም በ2002 በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ ባለድል የሆነ ሲሆን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዋንጫን ሲያነሳም ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡

ያጋሩ