የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 4ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀምር ጌዲኦ ዲላ የአመቱን የመጀመርያ ድል አስመዝግቧል።
መከላከያ 2-3 ጌዲኦ ዲላ
08:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ከሊጉ ጠንካራ ክለቦች አንዱ የሆነው መከላከያ ጌዲኦ ዲላን አስተናግዶ 3-2 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
ጌዲኦ ዲላዎች በ11ኛው ደቂቃ ገነሜ ወርቁ ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ በመሆን የመጀመርያው አጋማሽን ማጠናቀቅ ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ግብ በመቅረብ የተሻለ ቢንቀሳቀሱም በ53ኛው ደቂቃ ሳራ ነብሶ ያስቆጠረችው ጎል ይበልጥ ጨዋታውን አክብዶባቸዋል።
በ56ኛው ደቂቃ እመቤት አዲሱ እንዲሁም በ69ኛው ደቂቃ ሔለን እሸቱ አከታትለው ያስቆጠሯቸው ጎሎች መከላከያን አቻ በማድረግ ወደ ጨዋታው መልሰውታል። ከጎሉ በኋላ መከላከያዎች ጫናቸውን አጠናክረው በመቀጠል የጎብ እድሎች መፍጠር ቢችሉም በረጅሙ ከሚላኩ ኳሶች በግል ጥረቷ አደጋ ስትፈጥር የነበረችው ሳራ ነብሶ በ86ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ አስቆጥራ እንግዳው ጌዲኦ ዲላን ለድል አብቅታለች።
ውጤቱ ለጌዲኦ ዲላ የመጀመርያ ድል ሆኖ ሲመዘገብ ለመከላከያም የመጀመርያ ሽንፈት ሆኗል። ወረጤቱን ተከትሎም መከላከያ በ ነጥቦች ባለበት 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቆይ ጌዲኦ ዲላ በ5 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ሀዋሳ ከተማ 1-1 አዳማ ከተማ
ሀዋሳ ላይ የተካሄደው ይህ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀዋሳዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩ ሲሆን በ12ኛው ደቂቃ ምርቃት ፈለቀ በቀኝ መስመር ወደ ግብ የላከችው ኳስ የአዳማዋ ግብ ጠባቂ እምወድሽ በመዘናጋቷ ከመረብ አርፎ ሀዋሳወች መሪ መሆን ሲችለ በ25ኛው ደቂቃ አስካለ ገብረፃድቅ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን በመግባት ባስቀሰጠረችው ጎል አዳማዎች አቻ መሆን ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማወች በርካታ አጋጣሚን በመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በአንፃሩ አዳማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አደጋ መፍጠር ችለዋል። 56ኛው ደቂቃ ላይ በመስመር በኩል ጥሩ አጋጣሚ ስትፈጥር የነበረችው አስካለ ገ/ፃዲቅ ያቀበለቻትን ኳስ ሰርካዲስ ጉታ በቀጥታ መታ የግቡ ቋሚ ሲመልስባት 60ኛ ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች በመሳይ አማካኝነት ያገኙትን የግብ አጋጣሚ ግብ ጠባቂዋ እምወድሽ መልሳባታለች፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ምርቃት ፈለቀ ከመስመር በግሩም ሁኔታ ያቀበለቻትን ኳስ ተቀይራ የገባችሁ ነፃነት መና ከግቡ ጋር ብቻዋን ተገናኝታ ወደ ውጭ የሰደደችው ኳስ ሀዋሳን አሸናፊ ልታደርግ የምትችል ነበረች።
ውጤቱን ተከትሎ አዳማ በ5 ነጥብ 3ኛ ላይ ሲቀመጥ ሀዋሳ በ4 ነጥብ 7ኛ ላይ ተቀምጠዋል።
የሊጉ 4ኛ ሳምንት ቀጣይ ጨዋታዎች ነገ ሲደረጉ አአ ስታድየም ላይ በ08:00 ኤሌክትሪክ ከ ንግድ ባንክ ፣ ይርጋለም ላይ በ09:00 ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ድሬዳዋ ላይ በ09:30 ድሬዳዋ ከተማ ከደደቢት ይጫወታሉ።
ሊጉን ደደቢት በ9 ነጥቦች ሲመራ መከላከያ በ7 ይከተላል። ሰርካዲስ ጉታ፣ መዲና አወል፣ ሔለን እሸቱ እና ምርቃት ፈለቀ በ3 ጎሎች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱ ይመራሉ።