ትላንት የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዛሬ ከፍተኛ ግምት የተሰጠውን የደደቢት እና የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ያስተናግዳል። ሶከር ኢትዮጵያም ጨዋታውን በሰፊው የዳሰሰችበትን ፅሁፍ ያዛላችሁ ቀርባለች።
ቦታ– አዲስ አበባ ስታድየም
ቀን– እሁድ ታህሳስ 22 2010
ሰዐት– 10፡00
ዳኞች – ዋና ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘ (ፌደራል)
ረዳት ዳኞች- አበራ አብርደው (ፌደራል) እና ፋንታሁን መለሰ (ፌደራል)
የእርስ በእርስ ግንኙነት
ተጫወቱ – 16
ደደቢት አሸነፈ – 9 አስቆጠረ – 29
ኢትዮጵያ ቡና አሸነፈ – 6 አስቆጠረ – 23
አቻ – 1
የቅርብ ጊዜ ውጤቶች
ደደቢት | አሸ-አሸ-አሸ-አቻ-አቻ
ኢትዮጵያ ቡና | ተሸ-አሸ-ተሸ-አቻ-ተሸ
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ የሚገናኙባቸው ጨዋታዎች በሜዳ ላይ ከሚያሳዩት ፉክክር ከመድመቃቸው ባለፈ በርካታ ግቦች የሚቆጠሩባቸው እና በመሸናነፍ የሚጠናቀቁ ናቸው። በ2009 የውድድር አመት ሁለተኛ ዙር ላይ እስኪገናኙ ድረስም ያልተሸናነፉበት እና ግብ ሳያስቆጥሩ ከሜዳ የወጡበት አጋጣሚ አልነበረም። ሆኖም በአምናው የመጀመሪያ ዙር በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ በተገናኙበት ወቅት ደደቢት 3-0 ሲያሸንፍ ሀሪሰን ሔሱ ከግብ ክልል ውጪ ኳስ በእጁ በመንካት በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣበት እና ጌታነህ ከበደ ሀትሪክ የሰራበት ሆኖ ነበር ያለፈው። እስካሁን በአማካይ 3.25 ጎሎችን እያስመለከተን እዚህ የደረሰው የደደቢት እና የኢትዮጵያ ቡና የሊግ ፉክክር ዘንድሮም በሁለቱ ቡድኖች የሜዳ ላይ እና የሜዳ ውጪ ጉዳዮች ምክንያት ተጠባቂነቱ ከፍ ብሏል።
ሊጉን በ16 ነጥቦች በመምራት ላይ የሚገኘው ደደቢት ሰሞንኛ አቋሙ አስገራሚ ሆኗል። ቡድኑ ያለፉትን ሶስት ጨዋታዎቹን በድል ሲያጠናቅቅ አስር ጎሎችንም ከመረብ በማሳረፍ ነበር። ይህ ቁጥር ከመጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ላይ ግብ ማስቆጠር ሳይችል ለቀረ ቡድን ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በአጥቂነት ሚና ከሚታወቁት ጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለውን በተጨማሪ ተከላካዩ ደስታ ደሙ እና አማካዮቹ ኤፍሬም አሻሞ እንዲሁም አለምአንተ ካሳ አስሩን ግቦች የማስቆጠር ድርሻ እንደነበራቸው ስናስብ ደግሞ የቡድኑ የግብ አስቆጣሪዎች ስብጥርም ሌላው የወቅቱ የሊጉ መሪዎች ጥንካሬ ሆኖ እናገኘዋለን።
ከቅድመ ውድድር ጊዜ አንስቶ አንድ የሀገር ውስጥ እና ሶስት የውጪ ተጨዋቾች የተፈራረቁበት ኢትዮጵያ ቡና ከዚህ ጨዋታ በፊት ያሳለፋቸው ሳምንታት ጥሩ ትዝታ ጥለው ያለፉ አልነበሩም። ቡድኑ በሳምንቱ አጋማሽ በቀሪ ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከደረሰበት ሽንፈት ባሻገር ጅማ ላይ በጅማ አባጅፋር የተረታበት ጨዋታም ካለፈ ገና ሁለት ሳምንታት ናቸው የተቆጠሩት። ቡድኑ በመሀል ወልድያን በኤልያስ ማሞ ሁለት ግቦች ማሸነፍ ችሎ የነበረ ቢሆንም የደጋፊዎቹን ጥያቄ ለመመለስ ግን ያ ድል በቂ አልነበረም። ደጋፊዎች በዋናነት በክለቡ አመራሮች ላይ እና በሜዳ ላይ በሚታየው ቡድናቸው ላይ የሚይልሰሙት ተቃውሞም እየጨመረ መጥቷል።
በዚህ መልኩ በተለያየ ፅንፍ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች በዛሬው ፍልሚያቸው ላይ ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ውጤት ይመዘገባል ወይንስ ጨዋታው ያልተጠበቁ ክስተቶችን እና ውጤትን ያስመለክተናል የሚለው ጉዳይ በእጅጉ ተጠባቂ ሆኗል።
የቡድኖቹ አጨዋወት ባለፉት ሳምንታት
አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በተጨዋች ስብስብ ረገድ ጥያቄ የሚነሳበትን ቡድናቸውን በተለያዩ ቅርፆች እየሞከሩ ቆይተው አሁን ወደ ትክክለኛው መንገድ የገቡ ይመስላል። ሶስቱን ጨዋታዎች ሲያሸንፉም ቡድኑ በአሰላለፍም ሆነ በተጨዋቾች ምርጫ ተመሳሳይ ሆኖ ከመቅረብም ባለፈ በእንቅስቃሴ ረገድም መሻሻሎሽን አሳይቷል። ደደቢት ወደ 4-3-3 አሰላለፍ ከመጣ በኃላ ቡድኑ ያገኛቸውን ጠንካራ ጎኖች ስንመለከት አቤል ያለውን በቅድሚያ ማንሳት ተገቢ ነው። በእነዚህ ወቅቶች የመስመር አጥቂነት ሚና የተሰጠው አቤል አራት ግቦችን ከማስቆጠሩም በላይ ፍጥነቱን በመጠቀም የቡድኑ ዋነኛ የጥቃት መሳሪያ ለመሆን በቅቷል። የመሀል አጥቂው ጌታነህ ከበደም ቀድሞ ከምናውቀው ግብ የማስቆጠር ሚናው በተጨማሪ በተወሰኑ ሜትሮች ወደ ኃላ በመሳብ እና በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ በመሳተፍ ግብ የሆኑ ኳሶችን እስከማስቆጠር ደርሷል። ከተከላካይ አማካዩ አስራት መገርሳ ፊት የሚሰለፉት ሁለቱ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮች የአብስራ ተስፋዬ እንዲሁም አቤል እንዳለ/አለምአንተ ካሳ በማጥቃት ሂደት ላይ በመሀላቸው የሚኖረውን ክፍተት የተመጠነ በማድረግ በርካታ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ከብርሀኑ ቦጋለ ጉዳት በኃላ በግራ መስመር ተከላካይነት ላይ እየተሰለፈ የሚገኘው ሰለሞን ሐብቴም የማጥቃት ተሳትፎው ለቡድኑ እጅግ ወሳኝ ሆኗል።
ወደ ኢትዮጽያ ቡና ስንመጣ እንደተጋጣሚው ሁሉ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ወደ 4-3-3 የተመለሰ ቡድን ሆኖ እናገኘዋለን። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑን የመሩት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ ሁለትኛ አጋማሽ ላይ 3-4-3ን ከመጠቀማቸው ውጪ ቡድኑ በዋነኝነት በፊት ይጠቀምበት ወደነበረው ቅርፅ እንደተመለሰ መናገር ይቻላል። በዚህ ውስጥም በተመሳሳይ የሜዳ ክፍል ላይ ችምችም የማለት ችግሩ በተወሰነ መልኩ የተቃለለ ቢሆንም የቡድኑ መዋቅር አሁንም ብዙ እንደሚቀረው መናገር ይቻላል። በኤሌክሪኩ ጨዋታ እያሱ ታምሩን እና አስናቀ ሞገስን በግራ በመስመር አጥቂነት እና ተከላካይነት እንዲሁም ኤልያስ ማሞን በግራ የአማካዩ ክፍል ይዞ የነበረው ቡድኑ የማጥቃት ሂደቱን ሙሉ ለሙሉ በዚሁ ግራ መስመር በማድረግ ተገማችነቱን ከፍ ማድረጉ እና ይህው የግራ ወገን ለጥቃት ተጋልጦ መታየቱ ለቡድኑ መዋቅር በበቂ ሁኔታ አለመደራጀት አንዱ ማስረጃ ነው። በጨዋታው የአስቻለው ግርማ በፊት አጥቂነት መሰለፍ እና ቀድሞ ይጫወትበት ወደነበረው የግራ መስመር አጥቂነት ሚና አመዝኖ መታየትም ለዚህ ክስተት ሌላኛው ምክንያት ነበር። መስዑድ መሀድ እና አክሊሉ ዋለልኝ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተጫወቱበት የሚገኘው የተከላካይ አማካይ ቦታም እንዲሁ ገና በስራ ሂደት ላይ ያለ የቡድኑ ክፍል ነው። ሆኖም አሰልጣኙ ስራውን ከተረከቡ ጥቂት ሳምንታት ማስቆጠራቸውን ላሰበ በቡድኑ ላይ የሚታዩ መሰል ክፍተቶችን በሂደት ሊያሻሽሉ እንደሚችሉ የሚገምተው ጉዳይ ነው። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን በዛሬው ጨዋታ ከማሸነፍ ግዴታ ጋር ቡድናቸውን እየመሩ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
በጨዋታው ምን ይጠበቃል ?
በተመሳሳይ ቅርፅ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ በሚጠበቁት ሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት የአማካይ መስመራቸው ፍልሚያ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በዚህ ረገድ በመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎ የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆን ሲጠበቅ ደደቢት ሽመክት ጉግሳ በመስመር አጥቂነት በሚሰለፍበት አቅጣጫ የተሻለ የመከላከል ሽፋንን እንደሚያገኝ መናገር ይቻላል። የጌታነህ ከበደ በኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ መስመር ፊት እና የተከላካይ አማካይ ጀርባ የሚኖረው ነፃነት እና የቡድኑ ሁለት የማጥቃት አማካዮች ከጌታነህም ሆነ ከመስመር አጥቂዎቻቸው ጋር የሚኖራቸው የኳስ ስርጭት ለቡድኑ የግብ ዕድል ለመፍጠር ዋነኛ መሳሪያዎች ናቸው። በአንፃሩ የኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት አማካዮች ከአስራት መገርሳ ግራ እና ቀኝ ወደ መስመር አጥቂዎቻቸው አቅጣጫ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከደደቢት ተመሳሳይ ቦታ ተሰላፊዎች ጋር የሚኖረውን ፉክክር ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ከነዚህ ነጥቦች አኳያም ጨዋታው ክፍተቶችን ለመፍጠር በመሞከር ከመሀለኛው የሜዳ ክፍል መነሻውቸን በሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተመስርቶ ከፍተኛ ፍልሚያ እንደሚያስተናግድ ሲጠበቅ በርከተ ያሉ የግብ ዕድሎች የሚታዩበት እንደሚሆንም ይገመታል።
የቡድን ዜናዎች
በደደቢት በኩል የግራ መስመር ተከላካዩ ብርሀኑ ቦጋለ ካጋጠመው ጉዳት ባለማገገሙ ምክንያት ይህ ጨዋታ የሚያልፈው ብቸኛው የቡድኑ ተጨዋች ይሆናል። ለረጅም ጊዜ ሜዳ ላይ ካልተመለከትነው ክሪዚስቶም ንታንቢ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ቡና አዲስ ፈራሚ የመሀል ተከላካዮቹን ቶማስ ስምረቱ እና አክሊሉ አያናው ጅማ ላይ ባስተናገዱት ጉዳት ምክንያት የማይጠቀምባቸው ሲሆን አለማየው ሙለታም በሳምንቱ አጋማሽ በተደረገው የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ ከገጠመው ጉዳት እንዳላገገመ ሰምተናል። ከዚህ ውጪ ሳሙኤል ሳኑሚ እና ሳምሶን ጥላሁን ወደ ቡድኑ ስብስብ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ደደቢት (4-3-3)
ክሌመንት አዞንቶ
ስዩም ተስፋዬ – ደስታ ደሙ – ከድር ኩሊባሊ – ሰለሞን ሐብቴ
የአብስራ ተስፋዬ – አስራት መገርሳ – አቤል እንዳለ
አቤል ያለው – ጌታነህ ከበደ – ሽመክት ጉግሳ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
ሀሪሰን ሔሱ
ትዕግስቱ አበራ – ኤፍሬም ወንደሰን – ወንድይፍራው ጌታሁን – አስናቀ ሞገስ
ኤልያስ ማሞ – መስዑድ መሀመድ – ሳምሶን ጥላሁን
እያሱ ታምሩ – ሳሙኤል ሳኑሚ – አስቻለው ግርማ