በጉጉት የተጠበቀው የደደቢት እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ተስተናግዶበት በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ጎል ሲደመደም ደደቢት ከስድስተኛው ሳምንት ጀምሮ የተያያዘውን የአሸናፊነት ጉዞ በመቀጠል መሪነቱን አጠናክሯል።
የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ከሰሞኑ ተቃውሞ በኃላ ተበራክተው ወደ ስታድየም በተመለሱበት በዚህ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተሸነፈበት ጨዋታ የበርካታ ተጨዋቾች እና የአሰላለፍ ለውጥ አድርጎ ገብቷል። በ4-2-3-1 አሰላለፍ ጨዋታውን የጀመሩት ቡናዎች ከጉዳት የተመለሱትን ሳሙኤል ሳኑሚን በብቸኛ አጥቂነት እንዲሁም ሳምሶን ጥላሁንን ከአክሊሉ ዋለልኝ ጎን በአማካይ መስመር ላይ አጣምረዋል። የአለማየው ሙለታን ጉዳት ተከትሎ የቋሚነት ዕድል ያገኘው ትዕግስቱ አበራ በመሀል ተከላካይነት ጨዋታውን ሲጀምር የአለማየው የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ በአስራት ቱንጆ ተሸፍኗል። ከተጋጣሚያቸው በተቃራኒ በተከታታይ ሲያሸንፍ የቆየውን ቡድናቸውን በ4-3-3 አሰላለፍ ያለ ብዙ ለውጥ ይዘው የገቡት ደደቢቶች ኢትዮ ኤሌክትሪክን ባሸነፉበት ወቅት ከጉዳት መልስ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታውን የጀመረውን አቤል እንዳለን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል።
የተሻለ ሊባል በሚችል የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ጨዋታውን የጀመሩት ደደቢቶች አማካይ ክፍል ላይ የተወሰደባቸው የቁጥር ብልጫ የኳስ ምስረታቸው ከሁለተኛው የሜዳው አጋማሽ እምብዛም ያለፈ እንዳይሆን አድርጓቸዋል። የመስመር አጥቂዎቹ አቤል ያለው እና ሽመክት ጉግሳም በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ብዙ ሰዐት ማሳለፋቸው የኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካዮን አፍኖ በማስቀረቱ በኩል ትልቅ ሚና የነበረው ቢሆንም ከማጥቃት አማካዮቹ ጋር የነበራቸውን የቅብብል መስመር በቀላሉ የሚቆራረጥ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከጨዋታ እንቅስቃሴ ዕድሎችን መፍጠር የከበዳቸው ደደቢቶች የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት 29ኛው ደቂቃ ላይ ከጌታነህ ከበደ የግራ መስመር ቅጣት ምት ነበር። ከዚህ ሙከራ ሶስት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ ሽመክት ከትዕግስቱ ኳስ ነጥቆ ለጌታነህ አቀብሎት ጌታነህ ከሳጥን ውስጥ ሲሞክር ሀሪሰን ያደነበት ሙከራ ደደቢት በእንቅስቃሴ ያገኘው የተሻለው ሙከራ ነበር። በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ወደፊት ሲሄዱ አንፃራዊ አስፈሪነት የነበራቸው ቡናዎች በደደቢት ሜዳ ላይ ኳስ ይዘው በመገኘት የተሻሉ ነበሩ። የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ በደደቢት የመከላከል ሽግግር ላይ ለአስራት መገርሳ የሚሰጡት ሽፋን አናሳ መሆን እና ከላይ የተጠቀሰው የመስመር አጥቂዎች እንቅስቃሴ ከሳኑሚ ጀርባ የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ሶስቱ አማካዮች የተሻለ ነፃነትን ከማግኘት ባለፈ አደገኛ ዞኖች ላይ ኳስ የመቀማት ዕድልንም አጎንፅፏቸዋል። ይህን ተከትሎም በመከላከል ወቅት ኤልያስ ማሞን በመያዝ ከተጠመደው አስራት መገርሳ 14ኛው እና 25ኛው ደቂቃ ላይ የተቀሙ ኳሶች በአክሊሉ ዋለልኝ እና አማኑኤል ዮሀንስ ተሞክረው በዕለቱ ድንቅ በነበረው ክሌመንት አዞንቶ አማካይነት ግብ ከመሆን ድነዋል። በእነዚህ ሙከራዎች ወቅት ሁለቱም የደደቢት የመስመር ተከላካዮች አስፍተው ኳስ ለመቀበል ወደ መሀል ሜዳ የተጠጋ አቋቋም ላይ የነበሩ በመሆኑ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለቱም አጋጣሚዎች ከደደቢት ተከላካዮች በቁጥር በርክተው ነበር ዕድሎቹን ያገኙት። ከእነዚህ ሁለት ንፁህ ዕድሎች በተጨማሪ ሳሙኤል ሳኑሚ 8ኛው እና 35ኛው ደቂቃ ላይ ከደደቢት ሳጥን አቅራቢያ ያደረጋቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን ባይጠብቁም የተጨዋቹ የግል ጥረት የተንፀባረቀባቸው ሙከራዎች ነበሩ። በዚህ መልኩ ጥሩ ፉክክርን ያስተናገደው የመጀመሪያ አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ደደቢቶች ጨዋታውን ያሸነፉበትን ጎል ማግኘት ችለዋል። 28ኛው ደቂቃ ላይ ከሰለሞን ሐብቴ የቅጣት ምት በግንባሩ ሞክሮ የሳተው ጌታነህ ከበደ 45ኛው ደቂቃ ላይ ከአቤል እንዳለ የተነሳ ማጥቃት ሽመክት ጉግሳ በግራ መስመር ይዞ ከገባ በኃላ ወደኃላ ሲያሳልፍለት በመቀበል ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ በቀጥታ በመታት ነበር ያስቆጠረው።
ሁለተኛው አጋማሽ በብዛት በደደቢት ሜዳ ላይ በኢትዮጵያ ቡና የበላይነት የተደረገ ነበር። ሆኖም ቡናዎች የአቸነቷን ግብ ከማግኘት ባለፈ ጨዋታውን አሸንፎ የመውጣት ጫፍ ላይ ቢደርሱም የክሌመንት አዞንቶ ልዩ ብቃት ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈት እንዲገጥማቸው አድርጓል። ክሌመንት በመጀመሪያው አጋማሽ ካዳናቸው ሁለት ኳሶች በተጨማሪ ከቅርብ ርቀቶች የተሞከሩበትን በእጅጉ ለጎል የቀረቡ አምስት ሙከራዎችን ማምከን ችሏል። ደደቢቶች ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ሽመክትን ወደ ግራ መስመር በማውጣት የአብስራን እና አቤል እንዳለን ደግሞ ወደ ኃላ በመግፋት ወደ 4-4-2 የቀረበ ቅርፅ መጥተዋል። ቡድኑ አማካዮቹን እምብዛም ከራሱ ሜዳ እንዳይወጡ በማድረግ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን በመፍጠር ላይ ተመስርቶ ነበር ሁለተኛውን አጋማሽ ያሳለፈው። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ መስዑድ መሀመድን ፣ አስቻለው ግርማን እና ማናዬ ፋንቱን በተለያዩ ደቂቃዎች ቀይሮ በማስገባት በቀደመው የ 4-3-3 ቅርፅ ጫና ፈጥሮ ተጫውቷል። የደደቢትን ለውጥ ተከትሎም ነፃነት ያገኙት የቡና የመስመር ተከላካዮች በተሻለ የማጥቃት ሂደቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ። ከእረፍት መልስ ጨዋታው በጀመረባቸው አምስት ደቂቃዎች በእያሱ ታምሩ ፣ ሳሙኤል ሳኑሚ እና ሳምሶን ጥላሁን አማካይነት ሶስት ሙከራዎችን ያደረጉት ቡናማዎቹ በተለይ ከሰባኛው ደቂቃ በኃላ ጫናቸው በእጅጉ በርትቶ ታይቷል። በተለይ 70ኛው ደቂቃ ላይ ሳኑሚ ከኤልያስ ተቀብሎ ከሳጥኑ ጫፍ ላይ በቀትታ የመታው ፣ 73ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ከቀኝ መስመር አሻምቶለት አስቻለው በግንባር የሞከረው እንዲሁም 79ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ከአስራት ቱንጆ የተላከለትን ኳስ ከግማሽ ጨረቃው ላይ በቀጥታ የሞከሯቸው ሙከራዎች በጣሙን ለጎል የቀረቡ እና ኢላማቸውን ጠብቀው በክሌመንት የተመለሱ ነበሩ።
በአንፃሩ ወደ መሀል ሜዳ የቀረበውን የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር ሲፈትን ያመሸው የአቤል ያለው እና የጌታነህ ከበደ ጥምረት 60ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስገኘት ተቃርቦ የነበረ ሲሆን ፈጣኑ አጥቂ አቤል ያለው 62ኛው ደቂቃ ላይ በተከታታይ ቅፅበቶች መጀመሪያ ከስዩም ተስፋዬ ቀጥሎም ከጌታነህ ባገኛቸው ኳሶች ከሀሪሰን ሄሱ ጋር ቢገናኝም ቤኒናዊው ግብጠባቂ ከክልሉ በቅልጥፋና በመውጣት አምክኖበታል። ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው አቤል 83ኛው ደቂቃ ላይም ከቀኝ መስመር ጠባብ አንግል ላይ ያደረገው ሙከራም እንዲሁ በአደገኝነቱ የሚጠቀስ ነበር። ጨዋታው እሰከመጨረሻው ደቂቃ በሜዳ ላይ ውጥረት እና ከሁለቱም ቡድኖች በተሰሙ የፍፁም ቅጣት ምት ይገባኛል ጥያቄዎች ቀጥሎ እንደታዩት በርካታ ሙከራዎች ሌላ ግብ ሳይታይበት ፍፃሜውን አግኝቷል። ደደቢት ድሉን ተከትሎ ከተከታዩ ጅማ አባጅፋር ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ሲያሰፋ ኢትዮጵያ ቡና በ11 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣን ንጉሴ ደስታ- ደደቢት
” ኢትዮጵያ ቡና አሁን ካለበት ወቅታዊ ችግር የተነሳ ጨዋታውን አሸንፈን እንደምንወጣ እናቅ ነበር፡፡ ከሰሞኑ እንደተመለከትነው የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር እጅግ ተዳክሞ ተመልክተነዋል ፤ በዚህም የተነሳ ከጨዋታው መጀመሪያ አንስቶ በፍጥነት ማጥቃትን መርጠን ነበር የገባነው። ይህም ከተጨዋቾቼ አስደናቂ ጥረት ጋር ታክሎ ለድል አብቅቶናል፡፡”
አሰልጣኝ ዲዲየ ጎሚስ- ኢትዮጵያ ቡና
“ከሰሞኑ ጨዋታዎች በተሻለ በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል ፤ በጣም በርካታ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ቡና ባህል የሆነውን አጨዋወት ለመመለስ ጥረት አድርገናል፡፡በርካታ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ብናገኝም በጨዋታው ድንቅ የነበረው የደደቢቱ ግብጠባቂ ሊያመክንብን ችሏል፡፡በውጤቱ ባዝንም በጨዋታው ባየሁት ነገር ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ደጋፊዎቻችን እጅግ አስገራሚ ነበሩ ቡድኑን ወደነበረበት ለመመለስ የዛሬው አይነት ድባብ በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡”