በርካታ ጎሎች ባስተናገደው የከፍተኛ ሊግ 7ኛ ሳምንት የምድብ ለ መሪው ዲላ ከተማ ነጥብ ሲጥል ጅማ አባ ቡና ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ በጎል ተንበሻብሸዋል።
ቅዳሜ ጅማ ላይ ስልጤ ወራቤን ያስተናገደው ጅማ አባ ቡና 4-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ በፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ምክንያት ቀደም ብሎ የተጀመረው የሁለቱ ጨዋታ ግብ መስተናገድ የተጀመረው ገና ከ2ኛው ደቂቃ ብዙዓየው እንደሻው ያሻገረውን ኳስ ቴድዎሮስ ታደሰ ወደ ጎልነት በለወጣት አማካኝነት ነበር።
በፈጣን እንቅስቃሴ ሲያጠቁ የነበሩት ጅማ አባ ቡናዋች በብዙአየው እንዳሸው አማካይነት 8ኛው፣ 28ኛው እና 40ኛው ደቂቃ ላይ ባገባቸው ግቦች ስልጤ ወራቤን 4-0 በሆነ ውጤት መምራት ችለዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ወራቤዋች የጎላ እንቅስቃሴ ሳያሳዩ ወደ መልበሻ ከፍል ያመሩ ሲሆን ከዕረፍት መልስ የማታ ማታ በተስፈኛወረ ገብረመስቀል ዱባለ የ90ኛው ደቂቃ ጎል በባዶ ከመሸነፍ ድነዋል።
እሁድ እለት በተደረጉ ጨዋታዎች በፈኬዴሬሽኑ በተላለፈበት ቅጣት መሰረት ቡታጅራ ላይ የተጫወተው ወልቂጤ ከተማ መቂ ከተማን 5-1 በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፏል፡፡ ድሬዳዋ ላይ ናሽናል ሴሜንት ካፋ ቡናን 2-0 ሲረታ ሀላባ ከተማ ነገሌ ቦረናን በአቦነህ ገነቱ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፎ መውጣት ችሏል፡፡ ወደ ሻሸመኔ ያቀናው ደቡብ ፖሊስ በበኃይሉ ወገኔ ግብ 1-0 ሻሸመኔ ከተማን አሸንፏል፡፡
ሆሳዕና ላይ ቡታጅራ ከተማን ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል። መለሰ ትዕዛዙ 7 እና 21ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ በ2-0 መሪነት እረፍት ሲወጡ ኢብሳ በፍቃዱ 60 እና 83ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳመይ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል።
የምድቡ መሪ ዲላ ከተማ ወደ ሚዛን አምርቶ ከቤንች ማጂ ቡና ያደረገውን ጨዋታ 1-1 አቻ ውጤት አጠናቋል።