-ክፍል 1-

ክለቦች ለተጫዋቾች የሚያወጡት ወጪ መጠን እጅግ በተጋነነ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከ20 አመታት በፊት ከተመልካች ጭብጨባ የዘለለ የረባ ክፍያ የማያገኙት ተጫዋቾች አሁን አሁን ለ2 አመት በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጣ ኮንትራት መፈረማቸው እየተለመደ መጥቷል፡፡ እግርኳሳችን በውጤታማነት ፣ በእግርኳስ ስርአት እና በክለቦች ትርፋማነት ካለፉት አመታት የተለየ ለውጥ ባያስመዘግብም ለተጫዋቾች የሚወጣው ገንዘብ ግን የፍጥነት መጠኑ በእጅጉ አድጓል፡፡ የሶከር ኢትዮጵያው አብርሃም ገ/ማርያም በክፍል አንድ ጥንቅሩ ባለፉት 10 አመታት የተጫዋቾች የፊርማ ክፍያ (አሁን በደሞዝ መልክ እንዲሰጥ ደንብ ወጥቶለታል) ምንያህል እንዳደገና የእድገቱ መንስኤዎች ናቸው ያላቸውን በግርድፉ ያሳየናል፡፡

ከምንም ወደ ፊርማ ክፍያ…

የመድኑ ኮከብ ፋሲል አብርሃ የፊርማ ክፍያ በመቀበል ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በ1986 መድንን ለቆ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲቀላቀል ለፊርማ የተከፈለው 1000 ብር በወቅቱ ሃብታሙ የሃገራችን ተጫዋች አድርጎት ነበር፡፡ ሆኖም እግርኳስ ተጫዋችነት እንደ ስራ ተቆጥሮ ገንዘብ የሚገኝበት ዘርፍ ለመሆን በቅቷል ለማለት አመታት ወስዷል፡፡ ለዚህ እንደ አብነት የምንወስደውም በወቅቱ ‹‹ከፍተኛ ገንዘብ›› ቅዱስ ጊዮርጊስን የተላቀለው ፋሲል አብርሃ ለኢንተርናሽናል ውድድር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ወደ ሞሪሸስ ተጉዞ በዛው ለመጥፋት ያደረገው ሙከራ ይታወሳል፡፡

ከፕሪሚር ሊጉ ውልደት በኋላ የተጫዋቾች ህይወት ወደ መልካም መንገድ ሲያዘግም የሃገሪቱ እግርኳስ ደግሞ ወደ አዘቅት እየወረደ መጣ፡፡ በወቅቱ አለምን ያነጋገረው የቦስማን ህግን የተከተለ በሚመስል መልኩም ለተጫዋቾቻችን ፀሃይ ወጣላቸው፡፡ ተጫዋቾች ለፊርማ የሚቀበሉት ገንዘብም ቀስ በቀስ በአዝጋሚ ሁኔታ እየጨመረ መጣ፡፡ ለአብነትም በ1990 ቅዱስ ጊዮርጊስ ቴዎድሮስ በቀለ ‹‹ቦካንዴ››ን (15ሺህ) ፣ ሰይፈ ውብሸት (10ሺህ) እና አንተነህ ፈለቀን (10ሺህ) ለማስፈረም የከፈለውን የገንዘብ መጠን ከ5 አመት በፊት ካለው ሲነፃፀር ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል፡፡

በ1991 አንዋር ያሲን ለኢትዮጵያ ቡና ሲፈርም የተቀበለው 20ሺህ ብር የተጫዋቾች የማስፈረምያ ገንዘብ በየአመቱ ሪኮርድ እየበጠሰ እንደሚጓዝ ፍንጭ የሰጠ ዝውውር ነበር፡፡ በ1992 ደግሞ ከሱዳኑ ሂላል የተመለሰው አንተነህ አላምረው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመመለስ 30 ሺህ ብር ተቀበለ፡፡ በዚህ ወቅት ኤልያስ ከመድን ወደ ባንክ ሲዘዋወር 45ሺህ ብር እንደወጣበትም ይነገራል፡፡ በቀጣዩ አመት ከአየር መንገድ ወደ ጊዮርጊስ የተዛወረው ዳዊት መብራህቱ 60ሺህ ብር እንደወጣበትም ይታመናል፡፡

በ1990ዎቹ አጋማሽ ከ5ሺህ – 20ሺህ ፤ ከፍ ያለ ስም ለነበራቸው ደግሞ እስከ 30ሺህ ብር እየወጣበት የነበረው የተጫዋቾች የፊርማ ክፍያ በፍጥነት ሊያድግ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠው የቀድሞው የኤሌክትሪክ ድንቅ አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ ነው፡፡ ተጫዋቹ በኤሌክትሪክ ኮንትራቱ ባለመጠናቀቁ ቡና ኮንትራቱን አፍርሶ ተጫዋቹን ለማዘዋወር 35ሺህ ብር ከመክፈሉ በተጨማሪ ለዮርዳኖስ የ1 አመት አገልግሎት 30ሺህ ብር ማውጣቱ ይነገራል፡፡

ከ1990ዎቹ አጋማሽ እስከ አዲሱ ሚሌንየም መጀመርያ ድረስም የተጫዋቾች የፊርማ ክፍያ ጣርያ አንድ ጊዜ ከፍ አንድ ጊዜ ዝቅ ሲል በአዝጋሚ ሁኔታ እየጨመረ እስከ 70ሺህ ብር ደርሶ ነበር፡፡

1990-1999_____________________________________________________________

Chart 1 – ክለቦች ለአንድ ተጫዋች የሚያወጡት ገንዘብ ጣርያ ከ1990-1999

-በቻርቱ ላይ የተጠቀሱት አንዳንድ ወጪዎች ውል ማፍረሻን ጨምሮ ነው፡፡

-የገንዘብ መጠኖቹ ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥናት መሰረት የተገኘ በመሆኑ ይፋዊ ቁጥሮች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡

______________________________________________________________

የተጫዋችን ህይወት የቀየረው አዲሱ ሚሌንየም

የኢትዮጵያ ተጫዋቾች የፊርማ ክፍያ እስከ 1990ዎቹ መባቻ ድረስ ያን ያህል የተጋነነ ግሽበት ባለማሳየቱ የክለቦችን የአመት በጀት እስከማናጋት የሚያደርስ አልነበረም፡፡ እስከ አሮጌው ሚሌንየም መባቻ ድረስም የክለቦች ከ4 ሚልዮን ብር አይበልጥም ነበር፡፡ የተጫዋቾች የፊርማ ክፍያ በየአመቱ የሚያሳየው ልዩነት ምንም አልያም ቢበዛ እንኳን ከ10ሺህ ብር አይዘልም ነበር፡፡ ከአዲሱ ሚሌንየም በኋላ ግን ነገሮች በድንገት መቀያየር ጀመሩ፡፡ በሃገሪቱ ላይ የተከሰተው የሸቀጦች የዋጋ ንረትን የተከተለ በሚመስል መልኩ በየአመቱ ቢያንስ የ100ሺህ ብር ጭማሪ እያሳየ መጓዝ ጀምሯል፡፡ በዚሁ ሂደት ቀጥሎም በዘንድሮው ክረምት ክለቦች ለአንድ ተጫዋች እስከ 1.5 ሚልዮን ማውጣት ጀምረዋል፡፡

2000-2007_____________________________________________________________

Chart 2 – ክለቦች ለአንድ ተጫዋች የሚያወጡት ገንዘብ ጣርያ ከ2000-2007

-በቻርቱ ላይ የተጠቀሱት አንዳንድ ወጪዎች ውል ማፍረሻን ጨምሮ ነው፡፡

-የገንዘብ መጠኖቹ ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥናት መሰረት የተገኘ በመሆኑ ይፋዊ ቁጥሮች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡

_____________________________________________________________

የግሽበቱ ምክንያት ምን ይሆን?

የተንዛዛ አሰራር

በኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ የንግድ እቅስቃሴ የተንዛዛ ነው፡፡ አንድ ምርት ከተመረተበት ቦታ እስከ ተጠቃሚው ድረስ ምንም እሴት ሳይጨመርበት በተንዛዛ ሰንሰለት ውስጥ የሚያልፍ በመሆኑ ብቻ ዋጋው ይንራል፡፡ የተጫዋቾች የዝውውር እንቅስቃሴም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ክለቦች ተጫዋቾችን የሚያስፈርሙበት መንገድ ቀጥተኛ (ከክለብ ክለብ) ባለመሆኑ ተጫዋቹ ከኮንትራት ነፃ እስኪሆን ጠብቆ ከክለቦች ጋር ይደራደራል፡፡ ተጫዋቹ ጥቅሙን የሚያስከብርለት ህጋዊ ወኪል የሌለው በመሆኑ ክለቦችም ግንኙነት የሚፈጥሩት ከህጋዊ ወኪሎች ጋር ባለመሆኑ ተጫዋቹ ራሱ ከክለቡ ጋር ይደራደራል፡፡ በዝውውር ሰንሰለቱ ውስጥ ደላሎች (ህጋዊ ያልሆኑ) ፣ አሰልጣኞች እና በየደረጃው የሚገኙ የክለብ ኃላፊዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ እንደሸቀጦቹ ሁሉ የተጫዋቾቹም ዋጋ ይንራል፡፡

 

ክለቦች ከተጫዋቾቹ ደረጃ ይልቅ ወቅታዊውን ገበያ ይከተላሉ

በኢትዮጵያ እግርኳስ የተለመደው የገንዘብ አወጣጥ ስርአት ወቅታዊነቱ ያመዝናል፡፡ በአንድ ክረምት ላይ አንዱ ክለብ የሚያስፈርምበት ዋጋ ለሌሎቹም ክለቦች እንደ መለኪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ለአብነት በ1995 የነበረውን የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ስንመለከት ዮርዳኖስ አባይ በ1995 አጋማሽ በ30ሺህ ብር የፊርማ ክፍያ (ለአንድ አመት) ቡናን ሲቀላቀል በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻ ሰአት ካገኘው የሊግ ድሉ በኋላ ላስፈረማቸው ተጫዋቾች ላወጣው ተመሳሳይ ዋጋ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ዳንኤል ሃብታሙ ፣ ደብሮም ሃጎስ ፣ ኤርሚያስ ኪዳኑ ፣ ደያስ አዱኛ እና ሀይደር መንሱርን ለማስፈረም ክለቡ ለሁሉም 30ሺህ ብር ወጪ እንዲያደርግ ያስገደደው ከ6 ወር በፊት በዮርዳኖስ አባይ ላይ በወጣው ወጪ ተፅእኖ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ ሀይሉ አድማሱን እና ዮናስ ገ/ሚካኤልን ለማስፈረም 20ሺህ ብር አውጥቷል፡፡ ሀዋሳ ከነማ ዮሴፍ ተስፋዬ ፣ ዘላለም አልጣህ እና ሰለሞን ከበደን ለማዘዋወር ያወጡት ተመሳሳይ የሆነ ገንዘብ (15ሺህ) ነበር፡፡

ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሱት ማሳያዎች በወቅቱ ከፍተኛ ቢሆኑም እሁን አሁን ከሚታየው ‹የወቅታዊ ገበያ መሪነት›› በብዙ መልኩ የተሻለ ነበር፡፡ በወቅቱ ክለቦች ለሚያስፈርሙት ተጫዋች ተመሳሳይ ገንዘብ ቢያወጡም የክለቦቹን ደረጃ በሚያሳይ መልኩ ነበር፡፡ መካከለኞቹ (ሀዋሳ ከነማ) ከነ ቅዱስ ጊዮርጊስ በግማሽ ያነሰ ገንዘብ ሲያወጡ ከነሀዋሳ በታች ያሉትም ከዛም ባነሰ ዋጋ ያስፈርሙ ነበር፡፡

10 አመት ወደ ፊት አድርገን ያለፉትን 2 አመታት የተጫዋች ፊርማ ገበያን ስንመለከት ደግሞ በሁሉ ረገድ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ ኤሌክትሪክ ፣ ደደቢት ፣ ቡና ፣ ባንክ ፣ መከላከያ ፣ ሀዋሳ ከነማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዳማ ከነማ እና ሲዳማ ቡና ውል ላደሱላቸው እና አዳዲስ ላስፈረሟቸው ተጫዋቾች ያወጡት ገንዘብ በአመዛኙ ተመሳሳይ ነው፡፡ ክለቦች ያስፈረሟቸው ተጫዋቾች የብቃት ደረጃ ፣ እድሜ እና ልምድ የተለያየ ቢሆንም ለ2 አመት የሚከፍሏቸው የገንዘብ መጠን ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙት አስቻለው ታመነ ፣ አብዱልከሪም መሃመድ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና የመሳሰሉት ከአንጋፋ እና ባለፈው አመት አሳማኝ ብቃት ካላሳዩ ተጫዋቾች ጋር የሚቀራረብ ክፍያ አግኝተዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት መረጃዎች እንደሚያሳዩን የተጫዋቾችን የፊርማ ገንዘብ የሚወስነው የተጫዋቹ ደረጃ ሳይሆን ወቅታዊው ገበያ መሆኑ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ከመካከለኛ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አሳልፈው መኮንን ውሉን ሲያድስ የሚከፈለውና በሊጉ ከሚገኙ ምርጥ አማካዮች አንዱ የሆነውና ለብሄራዊ ቡድን ቋሚ ተሰላፊነት መፎካከር የጀመረው ብሩክ ቃልቦሬ ለአዳማ ሲፈርም የተስማማበት ዋጋ እኩል የሆነበት ምክንያትም ‹‹ወቅታዊው ገበያ›› ተመሳሳይ ገንዘብ እንዲያወጡ የሚፈቅድ በመሆኑ ነው፡፡ በጨዋታ ዘመኑ መጨረሻ ላይ የሚገኝ ተጫዋች በብቃቱ ጣርያ ላይ ከሚገኝ ተጫዋች እኩል ዋጋ የሚያወጣውም በዚሁ ወቅታዊ ገበያ መሰረት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የገንዘብ አወጣጥ ስርአት እስካልተሸሻለ ድረስ አንድ ተጫዋች ቀድሞ በአንድ ጊዜ ይሰጠው የነበረው የነበረው ገንዘብ በወራት ተከፋፍሎ ቢሰጠውም ለውጥ ማምጣቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የቡድኑ ኮከብ የሚከፈለው ወርሃዊ ደሞዝ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ከተቀመጡት የማይለይ ከሆነ ተጫዋቹን ሊያነሳሳው የሚችለው ምክንያት አይኖርም፡፡

በአንድ ወቅት የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ ኃላፊ አቶ ነዋይ በየነ ለኢትዮ-ስፖርት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተጫዋቾች የሚከፈላቸው ገንዘብ ተመሳሳይ የሚሆንበትን ምክንያት ለመጥቀስ ሞክረዋል፡፡ ‹‹ ለተጫዋቾች በአብዛኛው የምንከፍለው እኩል መሆኑ ትክክለኛ አይደለም፡፡ ተጫዋቹ በግሉ ተደራድሮ በሚያበረክተው አስተዋፅኦ መጠን ሊከፈለው ይገባል፡፡ የክፍያው አንድ አይነት መሆን ‹‹ እኔ ባላቀብው ኖሮ እሱ ያገባ ነበር›› በሚል ሊነሳ የሚችልን ጥያቄ በመፍራት ነው፡፡ ›› ይላሉ፡፡

በአጠቃላይ የዚህ ርእስ ሀሳብ አጭር ነው፡፡ አንድ ተጫዋች በከፍተኛ ገንዘብ ይፈርማል፡፡ ሌሎቹም ክለቦች ተከትለው ከከፍተኛው ጋር በሚቀራረብ ዋጋ ያስፈርማሉ፡፡ በዛውም የፊርማ ክፍያው በሃገሪቱ ደረጃ ያድጋል፡፡ በቀጣዩ አመት አንድ ክለብ በመቶ ሺህዎች አሻሽሎ እንድ ተጫዋች ሲያመጣም ሌሎቹ ክለቦችም ተቀራራቢውን ይከፍላሉ፡፡ ‹‹ለሱ እንዲህ ተከፍሎት ለኔ የማይከፈለኝ ምክንያት ምንድነው? ›› የምትለዋ ጥያቄም ሚዛን ትደፋለች፡፡

 

‹‹አዳዲሶቹ ክለቦች›› ተፅእኖ

በሌሎች ሃገራት ክለቦች ላይ እንደሚታየው በውጤታማነት ከዚህ በፊት የማናውቃቸው ቡድኖች ለዋንጫ ለመፎካከር የሚያስችላቸውን ተጫዋች ለማግኘት የውጤታማነት ሪኮርድ እና ሳቢነት ስለማይኖራቸው ሌሎች ክለቦች ከሚያቀርቡት በላይ እጅግ የተጋነነ ገንዘብ በማቅረብ ተጫዋቾችን የግላቸው ያደርጋሉ፡፡ ይህም በሃገሪቱ እግርኳስ ላይ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ መጠን እንዲጨምር ያደርጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ የታየውም ይህ ነው፡፡

ሰበታ ከነማ በ2001 ወደ ፕሪሚየር ሊግ ባደገበት አመት የተጫዋች ስብስቡ የሃገሪቱ መነጋገርያ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ ሰበታ ከነማ የሊጉን ታላላቅ ተጫዋቾች ለማማለል ከፍተኛ ገንዘብን ጨምሮ የመሬት ስጦታን ተጠቅሟል፡፡ አንዱአለም ንጉሴ ፣ ሙሉአለም ረጋሳ ፣ ዳዊት መብራህቱ ፣ ታምራት አበበ ፣ ሃብታሙ መንገሻ ፣ ብርሃኔ አንለይ እና ቢንያም አሰፋን ጨምሮ ቡድኑን በሃገሪቱ ከዋክብት ለመሙላት በመቶ ሺህዎች አፍስሷል፡፡ የሰበታ ሞዴልም በሁሉም ክለቦች ላይ ተፅእኖ ማድረጉ አልቀረም፡፡ ተጫዋቾች ከአቻዎቻቸው ጋር የተመጣጠነ ክፍያ የሚፈልጉ በመሆናቸው አጠቃላዩ የፊርማ ክፍያም ማሻቀብ ጀመረ፡፡ በቀጣዩ አመት ወደ ከፍተኛው ሊግ ያደገው ደደቢት የሰበታ ከነማን ፍጥነት ጨምሮ መምጣቱ ደግሞ የተጫዋቾች የፊርማ ክፍያን ይበልጥ አንሮታል፡፡

በ2002 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያደረገው ደደቢት የተጫዋቾችን የገንዘብ መጠን ጣርያ በመስቀል ሌላ አዲስ ምእራፍ ከፍቷል፡፡ በጊዜው ሙሉጌታ ምህረትን ለ2 አመት ለማስፈረም 110ሺህ ብር የከፈለው ደደቢት ቀድሞ ከፍተኛ ሲባል የነበረው የየበረከት አዲሱን የ100ሺህ ብር ሪኮርድ አሻሻለው፡፡ ክለቡ ጌታነህ ከበደ ፣ በኃይሉ አሰፋ ፣ ምንያህል ተሾመ ፣ ሲሳይ ባንጫ ፣ ፊሊፕ ዳውዚ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ ዳዊት ፍቃዱ እና አዲስ ህንፃን በተከታታይ አመታት ሲያስፈርም ተቀናቃኝ አልባ የነበረው በሚያወጣው የተጋነነ ገንዘብ መነሻነት ነበር፡፡ ክለቡ ዋንጫ እስካነሳበት 2005 ድረስም የዝውውር መስኮቱ ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ሌሎች ክለቦችም የተሻሉ ተጫዋቾችን ለማግኘት የግድ ከደደቢት ጋር የሚመጣጠን ክፍያ የመፈፀም ግዴታ ውስጥ ገቡ፡፡

የደደቢትን መቀዛቀዝ ተከትሎ ወደ ሊጉ ያደገው ዳሽን ቢራ ደግሞ የተጫዋቾችን የፊርማ ክፍያ እጅጉን በማናር ወደ ሚልዮን አሳደገው፡፡ በ2005 ዳሽን ቢራ ለአይናለም 1.1 ሚልዮን ብር ፣ ለአስራት መገርሳ ደግሞ 800ሺህ ብር በማውጣት የድራማው ዋና ተዋናይ ሆነ፡፡ በቀጣዩ ክረምት ሌሎች ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን ለማቆየት አልያም ለማስፈረም ቢያንስ ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ እንዲያወጡ የተገደዱት በድንገተኛው የዳሽን ቢራ የገንዘብ አወጣጥ ነው፡፡

ቀድሞ የሚከፈላቸው ገንዘብ ዝቅተኛ ነበር

በሃገሪቱ ገቢ የማይገኝባቸው ተብለው የሚታሰቡት ዘርፎች ባለፉት 10 አመታት ጉልህ የሚባል ለውጥ ታይቶባቸዋል፡፡ በተለይም በሙዚቃ ፣ በፊልም እና እግርኳሱ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች የክፍያ መጠን ከዚህ ቀደም እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ አሁን የሚከፈለው ገንዘብ እንደካሳ ሊቆጠር ይገባል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በእነዚህ የመዝናኛ ዘርፎች ውስጥ ያሉ ሙያተኞች የሚከፈላቸው ገንዘብ ለስራቸው የማይመጥን ከመሆኑ የተነሳ የመደበኛ ዜጋ ኑሮ እንዲኖሩ እንኳን የማያስችል ነበር፡፡ ሙያተኞቹ ለሙያቸው በትክክል እየተከፈላቸው የሚገኘው አሁን ነው የሚለው ሃሳብ የሚነሳውም ለዚህ ነው፡፡

በደርግ ዘመን በነበረው የ ‹‹50 ክለቦች›› ምክንያት ተጫዋቾች ከእግርኳስ ጫዋችነት በተጓዳኝ በፋብሪካዎች ውስጥ ቀጥረው የሚሰሩበት እድል ነበራቸው፡፡ ከ80ዎቹ አጋማሽ በኋላ ግን ተጫዋቾች እህል ውሃቸው የተሳሰረው በኳስ ተጫዋችነት ከሚያገኙት ደሞዝ ጋር በመሆኑ ከኳሱ መጠቀም እንዳለባቸው ይከራከራሉ፡፡

 

የብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ

ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፋቸው የብሄራዊ ቡድኑን ተጫዋቾች ዋጋ ጣርያ ካስነኩት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያሳለፉት ተጫዋቾች ለፊርማ የሚጠይቁት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ክለቦች የግድ ከፍተኛ ገንዘብ ለማውጣት ተገደዋል፡፡ የኋላ የኋላ የብሄራዊ ቡድኑን ማልያ ላለበሱትም ጭምር ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉ ተለምዷል፡፡

 

የተጫዋቹ ደረጃ ፣ እድሜ ፣ በቡድኑ ውስጥ ያለው አስፈላጊነት ፣ ከአሰልጣኙ አጨዋወት ጋር ሊኖረው የሚችለው መግባባት ፣ ያለፈ የውድድር ዘመን አቋሙ እና የመሳሰሉት ዋና ዋና ነጥቦች ከግምት ሳይገቡ ክለቦች በዘፈቀደ ገንዘብ ገንዘብ እየረጩ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ሰአት እየታየ ያለው የ1 ተጫዋች የፊርማ ክፍያ መጠን ከአስር አመት በፊት ሀዋሳ ከነማ የ1996 ቻምፒዮን ሲሆን ለውድድር ዘመኑ የመደበው በጀት ነበር ቢባል ማን ያምናል፡፡ የአንድ ተጫዋች ከፍተኛ የፊርማ ክፍያ በ1997 ከነበረበት 45ሺህ ብር በአስር አመት ውስጥ ብቻ ወደ 1.5 ሚልዮን ብር የማሻቀቡ ምስጢር በእርግጥም ሊመረመር ይገባዋል፡፡

ተጫዋቾች ለሚያሳዩት አቋምና ለክለቡ ለሚሰጡት ግልጋሎት ተገቢው ገንዘብ ሊከፈላቸው ግድ የማለቱን ያህል ክለቦች ፣ ፌዴሬሽኑ እና ባለድርሻ አካላት የተጫዋቾች ክፍያ መጠን በየአመቱ በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምርበት ምክንያት እንዲሁም ጥቅም እና ጉዳቱን በጥናት ተደግፈው ሊመረምሩት ይገባል፡፡

ይህ ካልሆነ ግን የሚጎዱት በድርጅቶችና የከተማ አስተዳደሮች መልካም ፍቃድ የሚተነፍሱ ክለቦች ናቸው፡፡ ክለቦች በወጪ ብዛት ሲፈርሱና ሲዳከሙም የሚጎዱት ተጫዋቾቹ ናቸው፡፡ በተጫዋቾች አለመኖርም ብሄራዊ ቡድኑ ይጎዳል፡፡ በእግርኳሱ ሰንሰለት የተሳሰሩት ባለድርሻ አካላት ቅጥ እያጣ የመጣውን የገንዘብ አወጣጥ ካልመረመሩ እንደ ሃገር መጎዳታችን አይቀሬ ነው፡፡

{ክፍል 2 ይቀጥላል}

 

ያጋሩ