በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታ ወልዲያ በሜዳው አርባምንጭ ከተማን አስተናግዶ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡
ቀን 9:00 ላይ በወልዲያ ሼህ ሙሀመድ አሊ አላሙዲን ስቴዲየም በጀመረው ጨዋታ ወልዲያ ከሽንፈት መልስ ፣ አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ ከአሰልጣኙ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ስንብት ማግስት ተገናኝተዋል። በ32ኛው ደቂቃ ፍፁም ገ/ማርያም አክርሮ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው አንተነህ መሳ ሲተፋት ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አንዷለም ንጉሴ አስቆጥሮ ወልዲያን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ በ56ኛው ደቂቃ ፍፁም ገ/ማርያም ላይ የአርባምንጭ ከተማው ግብ ጠባቂ አንተነህ መሳ በተሰራበት ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ፍፁም አስቆጥሮ የወልዲያን መሪነት አስተማማኝ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው 68ኛው ደቂቃ ላይ ላኪ ሰኒን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው የአርባምንጩ አጥቂ ገ/ሚካኤል ያዕቆብ ምንያህል ተሾመን በቡጢ መተሀል በሚል የዕለቱ ዳኛ አሰፋ ደቦጭ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል፡፡ ጨዋታውም በወልዲያ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አርባምንጭ ከተማዎች በእለቱ ዳኛ አሰፋ ደቦጭ ደስተኛ ባለመሆናቸው ሁለት ጊዜ ክስ አስይዘዋል፡፡
ከጨዋታው በኃላ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ወልዲያ
” ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። በሜዳችን ተከታታይ ጨዋታዎች አለማድረጋችን እና የፕሮግራሙ መቆራረጥ በአቋማችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው። በተለይ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደርግነው ጨዋታ በጣም ጥሩ ነበርን። ከዛ በኃላ በሜዳችን የምናደርገው ጨዋታ ሳይካሄድ ቀረ። እንደዛም ሆኖ ግን ዛሬ የነበረው እንቅስቃሴ በተለይ ደጋፊው እጅግ ጥሩ ድጋፍ ነበረው። ከነሱ ተሽለን ነበር የተንቀሳቀስነው በትክክልም በጥሩ ሁኔታ ነበር የተጫወትነው። ጨዋታው ላይ ካደረግነው እንቅስቃሴ አንፃር ውጤቱ ይገባናል። የእነሱ እንቅስቃሴ ግን መከላከል ይሁን ማጥቃት አላወቅኩም። ቅንጅት አልነበራቸውም። ያም ለኛ ጥሩ አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል። ”
ጊዜያዊ አሰልጣኝ በረከት ደሙ – አርባምንጭ ከተማ
“በቅድሚያ ውጤቱ ጨዋታውን የሚገልፅ አይደለም። እኛ የመጀመያዎቹን 15 ደቂቃዎች ጥንቃቄን መርጠን ነበር የተጫወትነው። በዛን ሰአት ትንሽ ወደ ኃላ አፈግፍገን ነበር። ከ15 ደቂቃ በኃላ ባሉት ግን ሙሉ ለሙሉ አጥቅተን ተጫውተናል። ዳኛው በጣም ተጭኖን ነበር። ክስ ለማስያዝ ስንሞክርም ሲከለክለን ነበር። እንደዛም ሆኖ ብዙ ዕድሎችን ሞክረን ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጭ ነው ብለው በተዘናጉት ኳስ የመጀመሪያ ግብ ተቆጠረብን። ሁለተኛው አጋማሽ ግን የአጥቂ ቁጥር ጨምረን በከፍተኛ ሁኔታ ተጫውተናል። እያጠቃን እያለ የማያሰጥ ፍፁም ቅጣት ምት ተቆጠረብን። ተጫዋቾቼም ሰሜታዊ ነበሩ። የገ/ሚካኤል ቀይ ግን በቢጫ የሚታለፍ ነበር እንደ እኔ እይታ። ዛሬ ዳኛው በጣም በድሎናል። ውሳኔ እንኳን ሲወስን ከ 20 እና 30 ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ነው። የአካል ብቃቱም ጥሩ አልነበረም። ብቻ ሁለት ጊዜ ክስ አስይዘናል። በተጨማሪነትም ለፌድሬሽኑ አመልክተናል። በአጠቃላይ ግን ዛሬ በሚገባ የተሻሻልንበት ጨዋታ ነበር። “