በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ሶዶ ላይ በተካሄደ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ኤሌክትሪክን 2-0 በማሸነፍ በሜዳው የውድድር አመቱን የመጀመርያ 3 ነጥብ አሳክቷል።
ወላይታ ድቻ ከተመሰረተበት 2001 አንስቶ ያለፉትን ለዘጠኝ አመታት ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ያገለገሉት መሳይ ተፈሪን ባሰናበተ ማግስት የቀድሞ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እና ከ17 አመት በታች የድቻ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ዘነበ ፍስሀ ቡድኑን በጊዜያዊነት ተረክቦ የመጀመርያ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩን የተኩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድኑን በዛሬው ጨዋታ ይመራሉ ተብሎ ቢጠበቅም ወደ ወላይታ ሶዶ ከቡድኑ ጋር ካቀኑ በኋላ ያላለቀ የወረቀት ጉዳይ አለ በሚል ምክንያት በስታድየሙ ጥላ ፎቅ አካባቢ ከተመልካች ጋር አብረው ተቀምጠው መመልከት ችለናል። የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ የሆኑት ቅጣው ሙሉ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ቡድኑን መምራት ችለዋል።
ወላይታ ድቻ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች በመሸነፍ በሊግ ታሪኩ መጥፎው ደረጃ ላይ ተቀምጦ ጨዋታውን ሲጀምር ኢትዮ ኤሌትሪክ ከሦስት ጨዋታ ሽንፈት በኋላ በተስተካካይ ጨዋታ ኢትዮዽያ ቡናን 2 – 1 በማሸነፍ በጥሩ በራስ መተማመን ሆኖ ነበር ወደ ሜዳ የገባው።
በዛብህ መለዮ በጉዳት ምክንያት ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ የዘንድሮ አመት የመጀመርያ ጨዋታውን ማድረግ የቻለ ሲሆን ለድቻ ማሸነፍ ትልቁን ሚና መወጣት ችሏል። ኢትዮ ኤሌትሪክ በአንፃሩ ረቡዕ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ከነበራቸው ጨዋታ ስብስብ ውስጥ አወት ገ/ሚካኤል ፣ ዘካርያስ ቱጂ ፣ ቢንያም አሰፋ እና ኃይሌ እሸቱ በጉዳት አለመኖራቸው በቡድኑ የጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ ክፍተት ሲፈጥር ታይቷል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው የመሩት ጨዋታ ብዙ ሳቢ ያልነበረ ሲሆን ሦስት የቀይ ካርድ የተስተናገደበት እና አነጋጋሪ የዳኝነት ውሳኔ የተመለከትንበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ከወላይታ ድቻ ተስፋ ኤልያስ እና ከኢትዮ ኤሌትሪክ በኃይሉ ተሻገር በኳስ ንክኪ ሁለቱም መሬት ቢወድቁም እዛው መሬት ላይ ግብግብ ሲገጥሙ የተመለከቱት ረዳት ዳኛው ለዋና ዳኘው ጥቆማ ሰጥተው ዳዊት አሳምነው ሁለቱንም በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግደዋቸዋል። በዚህ መንፈስ የቀጠለው ጨዋታ በሁለቱም በኩል ይህ ነው የሚባል የረባ የጎል ሙከራም ሆነ የተደራጀ እንቅስቃሴ ሳንመለከት 35ኛው ደቂቃ ላይ ሲሴይ ሀሰን በበዛብህ መለዮ ላይ በሰራው ጥፋት የሰጡትን ፍ/ቅ/ምት ጃኮ አራፍት ወደ ጎልነት ቀይሯት ድቻዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ በኋላም የኤሌክትሪክ ቡድን አባላት የዳኝነት ውሳኔው ተገቢ አይደለም በማለት የዕለቱ ዳኛ ላይ ከፍተኛ ተቋሟሞ አሰምተዋል።
ጨዋታው ከቀረበው ተቃውሞ በኋላ ቀጥሎ 40ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ መላኩ በዛብህ መለዮ ላይ ጥፈት በመፈፀሙ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ላይ አብዱልሰመድ አሊ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ድቻን በሁለት ጎል ልዩነት መሪ የምታደርግ ጎል አስቆጥሮ የመጀመርያው አጋማሽ በወላይታ ድቻ 2-0 መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም የጎል ሙከራ ያልተስተዋለ ሲሆን የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋቾች በተወሰደባቸው የቁጥር ብልጫ የጨዋታ ፍላጎታቸው ሲቀዘቅዝ በአንፃሩ ድቻዎች እንደወሰዱት የቁጥር ብልጫ እና በሁለት ጎል ልዩነት እንደመምራታቸው ኳሱን ከማንሸራሸር ባለፈ የጎል እድል ለመፍጠር ተቸግረው ታይተዋል። በመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች ከወላይታ ድቻ በኩል አብዱልሰመድ አሊ ፣ ከኤሌክትሪክ ደግሞ ተክሉ ተስፋዬ ተቀይሮ ገብቶ የሞከረው ኳስ ተጠቃሽ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ ድቻ የመጨረሻውን ደረጃ ለአርባምንጭ አስረክቦ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኤሌክትሪክ ተመልሶ ወደ ወራጅ ቀጠናው አሽቆልቁሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዘነበ ፍስሃ – ወላይታ ድቻ
” ጨዋታው ጥሩ ነበር። ቡድኑን እየመራው የመጀመርያ ጨዋታዬን በማሸነፌ ደስተኛ ነኝ። ወላይታ ድቻን ማሰልጠን የዘመናት ምኞቴ ነበር። ይህ በመሳካቱም ደስ ብሎኛል። ተጫዋቾቼ የነገርኳቸውን በሙሉ ፈፅመውልኛል። የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈን መውጣታችን ለቀጣይ ጨዋታ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ቡድኑ ብዙ መሰረታዊ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ በቀጣይ ከጨዋታ ጨዋታ አስተካክለን እንመጣለን። የተጫዋቾች ዝውውር ላይ ተሳትፈን ቡድኑን እናጠናክራለን። ”
ቅጣው ሙሉ – ኤሌክትሪክ
” ከጨዋታው አስቀድሞ ቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ላይ የዳኝነት ችግር ሊኖር እንደሚችል ተናግሬ ነበር። ጨዋታ ላይም የምንፈልገውን ታክቲክ ሜዳ ላይ እንዳንተገብር የሚወስነው ውሳኔ ጫና አድርጎናል። ይህ ዳኛ እንዴት ብሎ ኩፐር ቴስቱን አልፎ ኢንተርናሽናል ዳኛ እንደሆነ አላውቅም። በጣም ያሳዝናል። የልጆቻችን የመጫወት መንፈስ ለውጦታል። የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት በምን ምክንያት እንደሆነ አልገባኝም።